ሰዎች ስለ ሕገ-መንግሥቱ ምን ያስባሉ? –  በላይነው አሻግሬ (ጠበቃና የሕግ አማካሪ)

በ1987 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ያወጀው ሕገ መንግሥት አሁን ሀገሪቱ ላለችበት ውጥንቅጡ የወጣ ሂደት ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ኢሕአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን በእጁ ካስገባ ወዲህ ታስቦ የተረቀቀ ሳይሆን ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ በተለይም በአማራው ሕዝብ ላይ የተለያየ የጥላቻ ስሜቶችን አዝለው ሲዋጉ የነበሩ ቡድኖች ትክክለኛ ስሜት የተንጸባረቀበት ሰነድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ኢሕአዴግ ላወጀው ሕገ-መንግሥት ሕዝቡ ሆነ የተለያዩ ቡድኖች አንድ ዓይነት እሳቤ የላቸውም፡፡ በርግጥም ከመቶ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ባለባት ሀገር ሁሉም አንድ ዓይነት ስሜት ይኖረዋል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ ስለሆነም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለ ሕገ-መንግሥቱ የተለያየ አስተሳሰብ አላቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ቢያንስ ሁለት የተለያዩ ዕይታዎችን እንመለከታለን፡፡

“ተራው ሕዝብ”

ተራው ሕዝብ ማለቴ ከሕግና አስተዳደር ሥርዓት ራቅ ያለው ሕዝብ ለማለት ነው፡፡ ፊደል የቆጠረም ያልቆጠረም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል አብዛኛውን የሕዝብ ቁጥር የሚይዝ ነው፡፡ መደበኛ የሆነ ጥናት ተጠንቶ ባያውቅም፣ ከበርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሕግ እና በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ የመወያየት እና የመነጋገር አጋጣሚውን ያገኘ ሰው ሕዝብ አጠቃላይ ስለ ሕገ-መንግሥት ምን ያስባል የሚለውን በመጠኑ የመገንዘብ ዕድል ይኖረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ቃሊቲ ካለው የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ጣቢያ ወርጄ ወደ ቃሊቲ መናኸሪያ ለመሄድ የከተማ አውቶቡስ ውስጥ ገባሁ፡፡ አውቶቡሱ ውስጥ ብዙ ክፍት ወንበሮች ቢኖሩም የመጨረሻው ወንበር የግራ ጥግ ላይ ቁጭ አልኩኝ፡፡ የሳምንቱን በረራ ጋዜጣ በቦርሳዬ ይዤ ስለነበር አወጣሁን ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ከስተቀኜ የተቀመጠው በዕድሜ ከኔ የሚቀርብ ወጣት ልጅ የማነበውን ጋዜጣ አልፎ አልፎ ይመለከታል፡፡ በተለይ በጋዜጣው የመጨረሻ ገጽ ስለ አዲስ አበባ ጉዳይ የተጻፈውን በደንብ ሳያነበው አልቀረም፡፡

ቃሊቲ መናኸሪያ ልንደርስ ጥቂት ሲቀረን ከፊት ያሉት ተሳፋሪዎች እየተንጠባጠቡ መውረድ ጀመሩ፡፡ ከመጨረሻው የአውቶቡሱ መቆሚያ ደርሰን ልንወርድ ስንዘጋጅ ከጎኔ የተቀመጠው ወጣት ባለቀ ሰዓት “እንዴት ነው የአዲስ አበባ ጉዳይ” በማለት ከሕገ-መንግሥቱ በመነሳት ወግ ጀመረ፡፡ የጋዜጣውን ጽሑፍ ባይጨርሰውም እንዳነበበው ስለተረዳሁ “ያው እንዳነበብከው አንዳንድ እሰጣ-ገባ አለ” አልኩት፡፡

ወጣቱ ልጅ የወጋችንን ሂደት ሳይጠብቅ “ሕገ-መንግሥቱን ግን መቃወም አይቻልም አይደል?” አለኝ፡፡ ወጣቱ ለምን እንደዚህ እንዳለ ለመረዳት አልተሳነኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ልጁ ጥሩ የሕግ ግንዛቤ እንደሌለው ተረድቼዋለሁ፡፡ በመቀጠል ግን እንዲህ ዓይነት አስተሳሰቦች የኢሕአዴግ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት በሕዝብ ዘንድ ሲረጨው የነበረው ፕሮፓጋንዳ ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡

የኢህአዴግ አገዛዝ ሕገ-መንግሥቱን በሕዝቡ ልቦና ልእልና ያለው፣ የማይደፈር እና መቃወም ወንጀል እንደሆነ አድርጎ እንዲስለውና እንዲያምን ሲሠራ ነው የኖረው፡፡ “ሕገ-መንግሥቱን መቀበል አለብህ/ሽ”፣ “እገሌ ሕገ-መንግሥቱን በሃይል ለመናድ በማሰብ ተከሰሰ ወይም ታሰረ”፣ “ሕገ-መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦች ዋስትና” ወዘተ. የሚሉት ስብከቶች በሕዝቡ ልቦና ውስጥ ሰርጸው ገብተዋል ማለት ይቻላል፡፡ የተለያዩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች፣ ሕገ-መንግሥቱን በሃይል ለመናድ ሲሉ ተይዘው ተከሰሱ፣ እስር ተፈረደባቸው ሲባል ሕዝቡ ይሰማል፡፡ ዳኞች ከሹመታቸው ተነስተዋል፤ ሠራተኞች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፡፡ አገዛዙ እንዲህ ዓይነት ዜናዎችን ነጋ ጠባ ራሱ በተቆጣጠራቸው ብዙኃን መገናኛዎችና በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ሳይቀር በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጥ ነበር፡፡

ብቻ እንደዚህ ዓይነት ስብከቶች በብዙኃኑ የኅብረተሰብ ክፍል አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደራቸው የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሕገ-መንግሥቱን ማክበር ወይም መከተል ብቻ እንጅ መቃወም የሚቻል አይመስለውም፡፡ የመንግሥት ሹመኞችና የካቢኔ አባላት ሳይቀር ሕገ-መንግሥት ሲተች ሲሰሙ እጅግ ይከፋቸዋል፡፡ ይከፋቸዋል ብቻ ሳይሆን ሕገ-መንግሥቱን የሚተች ሰው ሲያጋጥማቸው ትልቅ ጥፋት እንደፈጸመ ሁሉ ያስጠነቅቁታል፡፡

እነዚህን ነገሮች በውስጤ እያብሰለሰልኩ ወጣቱ ልጅ በቀላሉ በሚገባው አገላለጽ እንዲህ ብዬ መለስኩለት፡፡ “ሕገ-መንግሥት በርግጥ ትልቅ ሕግ ነው፡፡ ሌሎቹ ሕጎች ሕገ-መንግሥቱን ተከትለው እንዲወጡ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ሕገ-መንግሥት በጊዜው ሥልጣን የያዙ ቡድኖች ተሰብስበው ያወጡት ሕግ ነው፡፡ ስለዚህ ሕገ-መንግሥቱ ከፍ ያለ ደረጃ ቢኖረውም ነገር ግን እንደ ሌላው ሕግ ነው የሚቆጠረው ነው፡፡ አንድን ሕግ ትክክል አይደለም ብለን እንደምንቃወመው ሁሉ ሕገ-መንግሥቱ ትክክል ያልሆነ ክፍል ካለው ይህንኑ ክፍል መቃወም እንችላለን” አልኩት፡፡

እሱም በመገረም “ታዲያ ሕገ-መንግሥቱን መቃወም ይቻላል ነው የምትለኝ?” አለ፡፡ አከታትሎ የአንዳንድ ፖለቲከኞችን ስም እየጠቀሰ “እነሱ እኮ የታሰሩት ሕገ-መንግሥቱን ያፈርሳሉ ነው ይንዳሉ ተብለው ነው፤” በማለት የተሳሳትኩ መስሎት ሊያርመኝ ሞከረ፡፡

እኔም ከላይ ያብራራሁለትን በድጋሜ አረጋገጥኩለት፡፡

“እና ሕገ-መንግሥቱን ከተቃወምን እንዴት ይሆናል…” አለ አሁንም መገረም ባልተለየው ገጽታ፡፡

“ብዙ አያስደንቅም፤ እንግዲህ ሕገ-መንግሥት ሕግ ነው ብየሃለሁ አይደል?” አልኩት ሐሳቤን ሳስረግጥ በደንብ ይረዳኛል በማለት፡፡ “ስለዚህ ሕግ እንደመሆኑ ሊሻሻል ወይም ሊለወጥ …” ብዬ ሳልጨርስ…

“ይሻሻላል!” ብሎ በመጠራጠርና በመገረም በሚመስል ሁኔታ ተመለከተኝ፡፡

እኔም አያስገርምም ተረጋጋ በሚል እይታ ፈገግ አልኩና “ሕገ-መንግሥት ሊሻሻል ወይም ሊለወጥ ይችላል ስላልኩህ አትደነቅ፤ አይደለም መሻሻል ይቅርና ሊሻር ወይም ሊታገድ ይችላል” ብዬ የሕግጋት የሕይወት ፍጻሜ የሆነውን ነገርኩት፡፡ የሰጠሁት ማብራሪያ ምን ያክል እንደሚረዳው ባላውቅም፣ ብዙኃን የኅብረተሰብ ክፍል የዚህን ወጣት የተዛባ አስተሳሰብ እንደሚጋራው መናገር ይቻላል፡፡ በርግጥ የዚህ ወጣት ልጅ አስተሳሰብ የሁሉንም ተራ ዜጋ አስተሳሰብ ይወክላል ለማለት አይቻልም፡፡

 

የተማረው ሕዝብ

ከዚህ ላይ የተማረው ማለቴ ፊደል ቆጥሮ፣ ከሕጉም ከአስተዳደሩም፣ ከሀገራዊ ጉዳዩም ቅርበት ያለውን ሕዝብ ለማለት ነው፡፡ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕገ-መንግሥቱን የሚረዱበት አግባብ ከራሳቸው ወይም ወጥተንበታል ከሚሉት ብሔር ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱንም የሚያስቡትና የሚመዝኑት እነርሱ ለወጡበት ክልል ከሰጠው ጥቅም አንጻር ነው፡፡ የኢሕአዴግ አገዛዝ ለሚመራበት ሕገ-መንግሥት ያላቸው ዕይታ ከክልላቸው ጥቅም አንጻር ብቻ የታጠረ እንጅ ከመሠረታዊ የሕገ-መንግሥት ፍልስፍናና መርህ ጋር የተናበበ አይደለም፡፡

አጠር ባለ መልኩ ሕገ-መንግሥቱን “መነካት” የለበትም ብለው ነው የሚያስቡት፡፡ አስተሳሰቡ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ከተራው ሕዝብ አስተሳሰብ ጋር ተቀራራቢ ሲሆን ነገር ግን ሕገ-መንግሥቱን ጥሩ በሚባል ደረጃ የተረዱት ናቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ሕገ-መንግሥቱን መነካካት (ማሻሻል) የሚለውን ሐሳብ በፍጹም መስማት አይፈልጉም፡፡ ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል ማለት ሰውን የሚያፈርስ፣ ለሃገር መገነጣጠል ምክንያት ይሆናል ብለው የተለመደ ስብከት ያሰማሉ፡፡

በርግጥም እነዚህ ቡድኖች ሕገ-መንግሥቱ ያመቻቸላቸውን የጸጋ ብዛት ሲያጤኑት የሕገ-መንግሥት መነካካት/መሻሻል ጉዳይ ሲነሳ ሃገር ይፈርሳል፣ ሰማይ ይደረመሳል ከሚል ዛቻ ባይወጡ ነው የሚያስገርመው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ ያወጀው ሕገ-መንግሥት ለአንዳንዶቹ ብሔሮችና የፖሊተካ ቡድኖች ያጎናጸፋቸው መብት ከህልማቸው እና ከአቅማቸው በላይ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በልቦናቸው ሲመኙት የነበረውን ሕልማቸውን በእጃቸው ላይ አስቀምጦላቸዋልና ከአሁኑ ሕገ-መንግሥት ዝቅ የሚል ነገር ካለ እንፈርጣለን፣ ወይም እናፈርጣለን ይላሉ፡፡

ለአብነት ያክል፣ ለኦሮሞ ፖለቲከኞች ኦሮሚያ የሚባል ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የተዘረጋ፣ ወደ ታች ወደ ደቡብ እስከ ኬንያ የሚደርስ መሬት እነሆ ብሏቸዋል፡፡ በክልላቸው ሌሎች ብሔሮች ቢኖሩም ቅሉ ነገር ግን ተገቢውን የፖለቲካ ቦታ አልሰጡም፤ ለመስጠትም አይፈልጉም፡፡ እነርሱ ሕገ-መንግሥቱ ካስቀመጠው ውጭ፣ ግን ደግሞ የሕገ-መንግሥቱን መንፈስ በመታከክ፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በሐረሪ ክልል ከሌላው ሕዝብ በተለየ ተጨማሪ ባለመብቶች ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ደግሞ “ልዩ ጥቅም” የሚባል ሌላ ተጨማሪ ጉርሻ እንዲሆን ተብሎ በሕገ-መንግሥት እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ እንደ ትግራይ ያሉት ደግሞ አሁን ከያዙት መልክዐ-ምድራዊ ወሰን ለማስጠበቅ ከማሰብ አንጻር ሕገ-መንግሥቱን መመከቻ/መከላከያ እድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ በዚያ ክልላችን ብለው ባጠሩት ክፍል ራስን በራስ ማስተዳደር የሚለውን የጨዋ ደንብ/መብት አልፎ “የግለኝነት” ወይም “እኛ/የኛ ብቻ” የሚባል ሌላ ጣዕም ፈጥሮላቸዋል፡፡

ለእነዚህ ቡድኖች እና በነዚህ ቡድኖች ውስጥ ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕገ-መንግሥቱ የሞት ሽረት ጉዳይ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ለድርድር አናቀርበውም፤ የሚነቀንቀውም የለም ይላሉ፡፡ በይፋ ነው የሚናገሩት፡፡ (ባለፈው ሳምንት ኦዴፓ “በፌዴራሊዝሙ ላይ አንደራደርም” የሚለውን መግለጫውን ያስታውሷል፡፡ የሕወሓት አቋምም ተመሳሳይ ነው፡፡) ምክንያቱም የሕገ-መንግሥት ነገር ሲነሳ ከላይ በመጠኑ የተጠቆሙት “ጸጋዎች” ናቸው ወደ ኅሊናቸው ቀድሞ የሚመጣላቸው፡፡

እነዚህ ቡድኖችና የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደ ማር የሚያጣጥሙትን ይህን ሁሉ ጥቅም አንዳንዱን ሕገ-መንግሥትን ተገን በማድረግ፣ አንዳንዱን ደግሞ ከሕገ-መንግሥት ውጭ በጉልበት/በሥልጣን ያገኙት መሆኑን ግን ማሰብ አይፈልጉም፡፡ ምናልባትም ላያውቁት ወይም ላይረዱት ይችላሉ፡፡ ብቻ ዘላለማዊ ሆኖ የሚኖርላቸው ይመስላቸዋል፤ ወይም ደግሞ ዘላለማዊ ሆኖ እንዲኖርላቸው ይመኛሉ፡፡

እንግዲህ ከላይ ሁለት አካላት በሕገ-መንግሥቱ ላይ ያላቸው አስተሳሰብ ምን እንደሚመስል ለማብራራት ተሞክሯል፡፡ የመጀመሪያዎቹ (ተራው ሕዝብ) በሕገ-መንግሥቱ ላይ ያላቸው ሃሳብ የመንግሥት የሃሰት ስብከት ውጤት ሲሆን በሁለተኛው ምድብ ላይ ያሉት ግን ያለውን ጥቅም በተግባር የሚያውቁት “ልሂቃን” ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ተራው ሕዝብ ለሕገ-መንግሥት ያለውን አስተሳሰብ ጊዜ ቢወስድም እንኳ ወደ ትክክለኛው መስመር ማቃናት ይቻላል፡፡

የኋላኞቹ ምድቦች (ልሂቃን) ራሳቸውን የሕገ-መንግሥቱ ዝግጁ ዘቦች አድርገው ይሰይማሉ፤ የሕገ-መንግሥቱ አስጠባቂ ዝግጁ ዘቦች እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ የእነሱ የሕገ-መንግሥት አስተሳሰብ ግን ለሌላው በርካታ ሕዝብ እና የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ በቀላሉ የሚዋጥ አይደለም፡፡ “ጸጋ” ሳይሆን ፍዳን፣ መገለልን፣ ምሬትን አፍርቶላቸዋል፡፡ በመሆኑም ሕገ-መንግሥት መሻሻል አለበት ብለው ቢያነሱ በቂ የሆነ ምክንያት አላቸው፡፡ ከዚያ አልፎም ሕገ-መንግሥቱ መሻር ወይም መታገድ አለበት የሚል ሃሳብ ቢነሳ እንኳ በመርህ ደረጃ የሚያስነቅፍ ነገር የለበትም፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ጫፎች ወደ መሃል እየተጠጉ በእኩል መድረክ ሊቀርቡ የሚችሉ ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

በቅድሚያ ሕገ-መንግሥት የሕግጋት ሁሉ የበላይ ነው እንደሚባለው ሁሉ፣ ሕግ እንደመሆኑ ደግሞ እንደ ሌሎቹ ሕግጋት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊሻሻል፣ ሊሻር፣ ወይም ሊታገድ እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ በተለይ ደግሞ ለተወሰኑ ቡድኖችና ብሔሮች ከሌላው ሕዝብ በተለየ ሁኔታ ጥቅም አጎናጽፎ፣ ሌሎችን ደግሞ ካላቸው በታች ያደረገ ሕገ-መንግሥት ሳይነካ የሚቀመጥ ሕግ አይደለም፡፡ ሕዝብም ሕገ-መንግሥት ጥቅሙን እንዲያስጠብቅለት በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጡትን ጉዳዮች በሙሉ ወይም በከፊል እንደገና ለድርድር ማቅረብ እንደሚችል ሊያውቀው ይገባል፡፡ ሕግን መሠረት አድርጎ የጠፋውን በሕግ መፈለግ፣ በሕግ የተበላሸውንም በሕግ ማቃናት እንደሚቻል መገንዘብ ይገባል፡፡ “እሾህን በእሾህ” የሚባለውን አባባል “ሕግን በሕግ” ብለን ልንተካው እንችላለን፡፡ በመጨረሻም ሕገ-መንግሥት የማይሻሻል፣ የማይነካ፣ ተቃውሞ የማይቀርብበት ነው የሚለው አመለካከትም ትክክል ስላልሆነ ሊወገድ ይገባል፡፡

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*