በንጹሃን ላይ የሚተኩስ ሠራዊት በታሪክም በሕግም ተጠያቂ ነው!

ኢህአዴግ 1983 ዓ.ም. በመሳሪያ ታግዞ ስልጣን ላይ ሲወጣ፣ ኢትዮጵያ የነበራትን የጦር ኃይል በትኗል፡፡ በምትኩም
ለራሱ ታማኝ የሆነ አዲስ ጦር አዋቅሯል፡፡ ኢህአዴግ ይህን ጦር ነው ‹የሀገር መከላከያ ሠራዊት› ብሎ የሚጠራው፡፡
የአንድ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወገንተኝነት የራቀ ሆኖ፣ ዋና ዋና ተልዕኮዎቹ የሀገርን ዳር
ድንበር (ሉዓላዊነት) ማስከበር፣ እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋን ጨምሮ ህዝብን አደጋ ውስጥ የሚከት ችግር ሲኖር ፈጥኖ
መድረስና የመታደግ ሥራ ማከናወን ናቸው፡፡
ሆኖም፣ ኢህአዴግ እንደ አዲስ ያዋቀረው ሠራዊት ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከመሠረታዊ ግዴታዎቹ ባፈነገጠ
መልኩ፣ ህዝብ ላይ የሚተኩስ ሠራዊት መሆኑን ደጋግሞ አስመስክሯል፡፡ ይህን የሚያደርገው ደግሞ ለገዥው አካል
ወግኖ መሆኑ ሠራዊቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሆኗል፡፡ የ1997 ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በሌሎች በርካታ
አካባቢዎች ባዶ እጃቸውን አደባባይ በወጡ ንጹሃን ላይ የተወሰደው የኃይል እርምጃ፣ የሠራዊቱን ወገንተኝነት በግልጽ
ያሳየ ሆኖ አልፏል፡፡ ከዚያ በኋላም ሆነ በፊት፣ በተመሳሳይ ሠራዊቱ በህዝብ ላይ የኃይል እርምጃ ወስዷል፡፡
2009 ዓ.ም. በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትዕዛዝ በአማራ ‹‹ክልል›› የተለያዩ አካባቢዎች
በንጹሃን ላይ የተወሰደውን የኃይል እርምጃ መዘንጋት አይቻልም፡፡ አቶ ኃይለማርያም፣ ‹‹…ሠራዊቱ ማንኛውንም እርምጃ
እንዲወስድ…›› መታዘዙን በይፋ አስታውቀው ነበር፡፡ ይህ ትዕዛዝ የተላለፈው፣ ህዝብ ኢህአዴግ መራሹን መንግስት
በመቃወሙ የተነሳ፣ ተቃውሞውን ለማፈን በማለም ብቻ ነበር፡፡ ይህ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኃላፊነት አይደለም፡፡
ሊጠብቀው የሚገባው ህዝብ ላይ ነው እንዲተኩስ የታዘዘው፡፡
የጦሩ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ሰሞኑን፣ ‹‹የአሁኑ ሠራዊት (ለውጥ ከመጣ ወዲህ ያለው
ማለታቸው ነው) ህዝብ ላይ አይተኩስም፤ አይገድልም›› ሲሉ አድምጠናቸዋል፡፡ ጄኔራሉ ‹‹ለውጥ መጥቷል›› ከተባለ
ወዲህ፣ መስከረም 07/2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አምባሳደር አካባቢ (መከላከያ ሚኒስቴር ፊት ለፊት) አምስት ንጹሃን
ሰዎች መገደላቸውን ልናስታውሳቸው እንወዳለን፡፡ የንጹሃኑን ግድያ፣ ፖሊስ ‹‹…የማያዳግም እርምጃ ተወስዶባቸዋል››
በሚል እንዳመነውም ሊዘነጉት አይገባም፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ ጭናቅሰን፣ ወለጋ፣ ጎንደር እና በተለያዩ ሌሎች አካባቢዎች በርካታ ዜጎች ከ‹‹ለውጡ›› በኋላ ስለ
መገደላቸው ጄኔራል ብርሃኑ ማወቅ ይኖርባቸዋል፤ እያወቁም ከሆነ የሚክዱት አካሄዳቸው አያዋጣቸውም፡፡ በእርግጥ፣
ጄኔራሉ በወገንተኛው ሠራዊት ተኮትኩተው ያደጉ ብቻ ሳይሆን፣ በታዛዥነታቸው ለከፍተኛ ማዕረግ መብቃታቸውን
የሰሞኑ ድርጊታቸው ማሳያ ይሆናል፡፡ ምዕራብ ጎንደር፣ በተለይም ኮኪት እና ገንዳ ውሃ አካባቢዎች ንጹሃን ላይ ተኩሶ
ግድያ የፈጸመ ሠራዊታቸውን፣ አንድ ጊዜ ‹‹ወደ ሰማይ ነው የተኮሰው›› ሲሉ፣ ወዲያው ደግሞ፣ ‹‹ሰዎች ተገድለዋል››
በማለት እርስ በእርሱ የሚምታታ የቀጣፊ ንግግር አድርገዋል፡፡
የጄኔራሉ ንግግር በዚህ ሳያበቃ፣ ቀደም ብሎ አለቃቸው የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ የተናገሩትን በመድገም፣
የጎንደር አማራን በተመለከተ ‹‹ሽፍታ የሚበዛበት›› ሲሉ የተጣባቸውን ጥላቻ አስተጋብተዋል፡፡ በመሠረቱ፣ አማራ ጠል
የሆነው ህወሓት ኮትኩቶ ካሳደጋቸው ሰዎች ከዚህ የተለዬ ነገር መጠበቅ አይቻልም፡፡ በአማራ ጠል ሥርዓት ያለፉ
መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ ሆኖም፣ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ፣ ንጹሃን ላይ የሚተኩሱ አካላትን ለይቶ ከማጋለጥ ይልቅ፣
‹‹ሠራዊቱ አልተኮሰም›› የሚል ክህደት የትም አያደርስም፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ግድያው የተፈጸመው የአንድ
ተራ ተቋም መኪኖችን በማጀብ ሰበብ መሆኑ ነው፡፡ ለመሆኑ፣ መከላከያ ሠራዊት በምን ኃላፊነቱ ነው የግል መኪና
የሚያጅበው?
በእርግጥ፣ አሁን ያለው ሠራዊት በተለያዩ ወቅቶች የአማራ ተወላጆችን በሰበብ አስባቡ እያባረረ፣ በምትኩ የአማራ
ጠል ትርክትን የተቀበሉ ምልምሎችን ሲሰገስግ እንደዘለቀ በሂደቱ ያለፉ የሠራዊቱ የቀድሞ አባላት ምስክሮች ናቸው፡
፡ ጠያቂ አማራዎችን ከጅምሩ 1983 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የተለያዩ ስሞችን እየለጠፉ ማሸማቀቅ፣ ይህ አልበቃ ሲል ማባረርና
ማሰር፣ አለፍ ሲልም መረሸን የህወሓት/ኢህአዴግ የእጅ ሥራ የሆነው ሠራዊት መለያ ሆኖ መዝለቁ የአደባባይ ሚስጥር
ሆኗል፡፡ በዚህ መንገድ ያለፈው ሠራዊት፣ ዛሬም ድረስ በንጹሃን ዜጎች፣ በተለይም እንደ ስጋት እንዲቆጠር የተሰበከበት
አማራ ላይ መተኮሱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡
ሆኖም፣ አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ አለ፡፡ ይኸውም፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ፣ እንዲሁም ነገ በማናቸውም ሁኔታ
በንጹሃን ላይ የሚተኩስ ሠራዊት በታሪክም ሆነ በሕግ ተጠያቂ መሆኑን ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ህጻናት እና
እናቶች በተገደሉበት ሁኔታ፣ ‹‹ሠራዊቱ ወደ ሰማይ ነው የተኮሰው›› በማለት ‹‹በሰው ቁስል እንጨት መስደድ…›› ደግሞ
ሌላ ተጨማሪ በደል መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*