አማራ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሸፍጥ እንዳይሰራበት ጥንቃቄ ያስፈልጋል!

የብሔራዊ ፕላንና ልማት ኮሚሽን አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ከመጋቢት 29/2011 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት
ተከታታይ ቀናት እንደሚከናወን ጥር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታውቋል:: ይህ አራተኛው ዙር ቆጠራ መካሄድ የነበረበት
በ2010 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ‹‹በሀገሪቱ በተከሰቱ አለመረጋጋቶችና ጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ…›› ተብሎ ተራዝሞ ቆይቷል::
የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ፣ ‹‹ቆጠራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚደገፍ
ሲሆን፣ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጉበታልም፤›› ሲሉ ተደምጠዋል:: እዚህ ላይ ኤጀንሲው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ
ታግዞ ቆጠራው ይደረጋል ሲል፣ የቴክኖሎጂው አቅራቢ በሕወሓት ሰዎች የበላይነት ሲመራ የቆየው የኢንፎርሜሽን
መረብ ደሕንነት ኤጀንሲ የተሰኘው ተቋም መሆኑን ልብ ማለት ይገባል::
ከዚህ ቀደም በነበሩት ህዝብና ቤት ቆጠራዎች፣ በተለይ በሦስተኛው ቆጠራ ወቅት በርካታ ፖለቲካዊ ደባዎችና
ስልታዊ ውሳኔዎች ተላልፈዋል:: በዚህም፣ በተለይ በአማራ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የቁጥር ቅነሳ ተደርጓል:: ይህም በፓርላማ
የታመነ ነው:: የቁጥር ቅነሳው እንዲሁ በስህተት ወይም በአቅም ማነስ የሆነ አልነበረም፤ ታቅዶበት ስልታዊ በሆነ መንገድ
የተፈጸመ እንጂ:: ለዚህም፣ በወቅቱ ‹‹የአማራ ህዝብ ቁጥር ለምን ቀነሰ?›› የሚል ጥያቄ ሲነሳ የተሰጡትን መልሶች
ማስታወስ ይቻላል:: ባለጊዜዎቹ ጥያቄውን ሲመልሱ አንዴ፣ ‹‹ጠፋ!›› ሲሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹በኤድስ በሽታ አልቋል››
በማለት ተሳልቀዋል::
ያሉትን ካሉ በኋላ ከቀነሱት ብዙ ሚሊዮን ህዝብ ቁጥር ላይ ‹‹በፍለጋ የተገኘ›› ብለው ይፋ ካደረጉት ቁጥር ትንሽ
መጨመራቸውም የምንዘነጋው አይደለም:: ህወሓት መራሹ ሥርዓት አማራን አምርሮ ከመጥላት በላይ፣ በይፋ በጠላትነት
ፈርጆ ‹‹ጨቋኟን የአማራ ብሔር ሕብረተሰባዊ እረፍት እንነሳታለን›› ብሎ በማኒፌስቶው ማስፈሩ ሀቅ ነው:: ለዚህም ነው
የሥርዓቱ ሰዎች ጠላት ብለው የፈረጁትን ህዝብ ቁጥር መቀነሳቸው ስልታዊና ሥርዓታዊ የሚሆነው::
ሥርዓቱ የአማራን ህዝብ ቁጥር በብሄራዊ ህዝብና ቤት ቆጠራ ሰበብ መቀነሱን እንደ ጉልህ ችግርና ሴራ የማይመለከት
ሰው አይጠፋም:: ሆኖም፣ በዚህ ብሔርን መሠረት ባደረገ ሥርዓት የፖለቲካ ውክልና የሚሰራውና የበጀት ቀመር
የሚዘጋጀው የህዝብ ቁጥር እየታየ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል:: በዚህም፣ ‹‹ክልል›› ተብሎ ከተወሰነበት አካባቢ
የሚኖረው የአማራ ህዝብ ተገቢውን ውክልና ካለማግኘቱም በላይ፣ ከ‹‹ክልሉ›› ውጭ የሚኖረውም ያለምንም ውክልና
እንዲባዝን ተፈርዶበታል:: ከዚህም በላይ ትክክለኛውን የህዝብ ቁጥር ባገናዘበ መልኩ በማይሰሩ የጤና እና ሌሎች
አገልግሎቶች የአማራ ህዝብ፣ በተለይ ህጻናትና እናቶች ዘርፈ ብዙ ለሆነ ችግር ተዳርገዋል:: በዚህም፣ በመንግስትና
በዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ይፋ እንደሚያደርጉት ህጻናት ቀንጭረዋል፤ እናቶች ከየትኛውም አካባቢ በላይ ሞታቸው የበዛ
ሆኗል:: ይህ ሁሉ ህዝብና ቤት ቆጠራ በሚል ሰበብ በተሰራው ስልታዊ መገለልና አድሎ የመጣ ነው::
አሁን መንግስት ለአራተኛው ህዝብና ቤት ቆጠራ እየተዘጋጀ ነው:: የአማራ ህዝብ እንደትናንቱ ያለ ሸፍጥና ስልታዊ
መገፋት እንዳይደርስበት ከወዲሁ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ:: ምንም እንኳ ዛሬም የትናንቱ ኢህአዴግ መራሽ
መንግስት በስልጣን እንዳለ ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት ቆጠራው ሲራዘም የተሰጠው ‹‹በሀገሪቱ በተከሰቱ አለመረጋጋቶችና
ጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ…›› የተባለው በዚህ ወቅትስ ችግሩ ተቀርፏል ወይ ቢባል መልሱ አጠያያቂ ነው:: ዛሬም
እዚህም እዚያም ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እንዳለ ነው:: በርካቶች ለዓመታት ከኖሩበት እየተፈናቀሉ ናቸው::
አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ሰዎች ራሳቸውን በነጻነት ለመግለጽ የማያስችሉ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳሉ ናቸው::
ወልቃይት እና ራያ ዛሬም በህወሓት መዳፍ ሥር ናቸው፤ በእነዚህ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ትክክለኛ ማንነታቸውንና
ፍላጎታቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ የሚያግድ ሥርዓት ሥር ናቸው:: በተለይ፣ በእነዚህ አካባቢዎች ከሚነሱ የአማራ
ማንነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ፣ ህወሓት ከሚፈልገው ውጭ ራስን መግልጽ አዳጋች ነው::
በተመሳሳይ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚኖሩ አማራዎች ከሚደርስባቸው መንግስታዊ ጫና
አንጻር፣ ራሳቸውን በነጻነት ገልጸው በህዝብና ቤት ቆጠራው ያስመዘግባሉ ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል:: አማራዎች
በሰበብ አስባቡ ከመኖሪያ ቀያቸው ከሚፈናቀሉባቸው እነዚህ አካባቢዎች፣ ህዝብና ቤት ቆጠራው ሲደረግ ትክክለኛ
ማንነታቸው የተገለጸበትን እውነታ ማግኘት ከባድ ይሆናል:: በሀረሪ ክልል እና በድሬዳዋ አስተዳደር ያለውም ተመሳሳይ
ነው:: በደቡብ ክልል፣ በተለይም ሚዛን እና ቴፒ አካባቢዎች፣ እንዲሁም ሀዋሳ እና አካባቢው ካለው ወቅታዊ ሁኔታ
አንጻር ሰዎች በነጻነት በህዝብና ቤት ቆጠራው ይሳተፋሉ ለማለት አዳጋች ነው::
በመሆኑም፣ ታቅዶበትና ስልታዊ በሆነ መልኩ ከሚፈጸመው የህዝብ ቁጥር ቅነሳ በተጨማሪ፣ ሰዎች በነጻነት
በቆጠራው እንዳይሳተፉ የሚያደርጉ ችግሮች ትክክለኛ ውጤትን እንደማያስገኙ ታውቆ ከወዲሁ ሊታሰብባቸው ይገባል::
በተለይ፣ ቀደም ባሉት ህዝብና ቤት ቆጠራዎች ከፍተኛ የፖለቲካ ሸፍጥ ሰለባ የሆነው የአማራ ህዝብ፣ እንዳለፈው ያለ
ስታቲስቲክሳዊ ደባ እንዳይሰራበት ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*