የህወሓት ነገር – ግመል ሰርቆ አጎንብሶ!

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ታኅሣሥ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በህዝብ ተወካዮች
ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል:: በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከማንነትና ከወሰን ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ለሚነሱ
ጥያቄዎች በጥናት ላይ በተመረኮዘ ግኝት የመፍትሄ ሀሳብ የማቅረብ ሚና ይኖረዋል የተባለው ኮሚሽኑ፣ ህግና ታሪክን
መሠረት ባደረገ መልኩ በሚሰሩ ሥራዎች ለጥያቄዎቹ ‹የማያዳግም› ምላሽ ይሰጣል በሚል ታምኖበታል::
በሌላ በኩል፣ ባሳለፍነው ሣምንት የትግራይ ክልል ምክር ቤት ይህን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን
የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የሚቃወም የውሳኔ ሀሳብ አስተላልፏል:: የክልሉ
ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት የህወሓት ካድሬዎች አዋጁን ሲያጣጥሉ ሰንብተዋል:: በህዝብ ተወካዮች
ምክር ቤት ሲጸድቅ ጀምሮ ህወሓት አዋጁን ተቃውሞታል::
የህወሓት ካድሬዎች አዋጁን ወይም የኮሚሽኑን መመስረት የሚቃወሙት ሕገ መንግስቱ አንቀፅ 39 (የክልሎችን
የመገንጠል መብት የተመለከተውን) ይቃረናል፤ የፌድሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንም ይጋፋል በሚል እንደሆነ ሲናገሩ
ተደምጠዋል:: ሆኖም፣ ጉዳዩ በሕግ ባለሙያዎች ተፈትሾ የሚባለው ችግር እንደሌለበት ታይቷል:: ሆኖም፣ ህወሓት
አዋጁን ወይም የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን መቋቋምን የሚቃወምበት ሌላ ፍላጎት ስላለው እንደሆነ
ግልጽ ነው::
በመሠረቱ፣ ህወሓት የማዕከላዊ መንግስት ሥልጣኑን ካጣ ወዲህ የሚይዘው የሚጨብጠውን አጥቷል:: አያሌ
ዜጎች ሲገደሉ፣ ሲታፈኑ፣ ጥፍራቸው ሲነቀል፣ ደብዛቸው ሲጠፋ፣ እና መሠል ግፍ ሲፈጸምባቸው አንድም ጊዜ ‹‹ሕገ
መንግስቱ ይከበር›› የሚል ድምጽ ትንፍሽ ብሎ የማያውቀው ህወሓት፣ ዛሬ ምን ተገኜና ነው ተቃውሞ የሚያሰማው
ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ አንድ ነው፤ ይኸውም የቡድን ጥቅሙ ስለተነካበት ብቻ የሚል ይሆናል:: ትናንት ከፍተኛውን
የሀገሪቱን ሥልጣን ይዞ አድራጊ ፈጣሪ በነበረበት ጊዜ፣ ሕግ ዜጎችን ረግጦ መግዣው ነበር:: ዜጎች ተቃውሞ ሲያሰሙ
ማፈኛ መሣሪያው ነበር:: ዛሬ ከአድራጊ ፈጣሪነት ሥልጣኑ በህዝብ ኃይል ሲገፋ፣ ‹‹ሕግ ተጣሰ›› በሚል ሰበብ ጠባብ
የቡድን አጀንዳውን ያራምዳል::
መቀሌ የመሸገው ጠባብ የቡድን አጀንዳ አራማጁ ህወሓት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን
መቋቋምን ሲቃወም፣ ለዓመታት በኃይል ድምጻቸውን አፍኖ ያለፍቃዳቸውና ያለፍላጎታቸው በትግራይ ሥር የሚገዙ
ወልቃይት፣ ራያ እና ሌሎች በአፋር አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን በለመደው አፈና ይዞ ለመቀጠል ካለው ምኞት የተነሳ
መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው:: ይህ ብቻም አይደለም፤ ህወሓት ቢሳካለት ከዚህም በላይ ግዛት ነጠቃ ውስጥ በመግባት
የመስፋፋት ህልም አለው:: ስለሆነም፣ ይህን አጉል ህልሙን (ቅዠቱን) የሚገታ ማናቸውም ሕግም ሆነ አሰራር
ቢቃወም፣ ቢያጣጥል የሚገርም አይሆንም::
ህወሓት የአድራጊ ፈጣሪነት ጀምበሩ መጥለቋን ሊያውቅ ይገባዋል:: ከዚህ በኋላ ህዝብ የህወሓትን የአገዛዝ ቀንበር
ለመሸከም ትዕግስት የለውም:: ለዚህም ነው ከማዕከላዊ መንግስት ሥልጣኑ የተገፋው:: ነገ ደግሞ ከበቀለበት የትግራይ
ምድርም በህዝብ ይተፋ ይሆናል:: የጊዜ ጉዳይ ነው:: በእርግጥ፣ ህወሓት በሀገሪቱ በሚወጡ ሕጎችም ሆነ አሰራሮች
ላይ ተቃውሞ ማሰማት መብቱ ነው:: ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሞውን እስከገለጠ ድረስ መብቱ ነው፤ ትናንት
ለሚሊዮኖች የነፈገውን የመቃወም መብት ዛሬ ተከብሮለት ልዩነቱን ማየቱ መልካም ነው::
ይሁን እንጂ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሥራን የመሰሉ ጉዳዮች ላይ ህወሓት ተቃውሞ
ከማሰማት ባለፈ፣ ተግባራዊነቱን ሊያስቆመው ብቻ ሳይሆን ሊያስተጓጉለውም አይገባም፤ አይችልምም:: እንዲህ ያሉ
በፌድራሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ የጸደቁ ሕጎች ተፈጻሚነታቸው ለሁሉም እኩል ነው::
ስለሆነም፣ ህወሓት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ስም በተነሳ ጊዜ ሁሉ ወልቃይት እና ራያ በውስጡ
እየተመላለሱ ቢያቃዡትም፣ አፈናው ግን በእስካሁኑ መብቃቱ ግድ ነው::
ሕዝብ በመረጠው ቋንቋ መናገርና መማር፣ ከወደደው አካባቢና ህዝብ ጋር የመተዳደር መብቱ ሊከበርለት ግድ
ነው:: የኮሚሽኑ ዓላማ ይህ ሆኖ ማየት እንደሆነ ተቀምጧል:: ደግሞም ህወሓት ከሚመራው ትግራይ ክልል ይልቅ
እንደ ደቡብ ያሉ ክልሎች የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ብዙ ሥራ ሊያከናውንባቸው ከሚጠበቅበት
መካከል ናቸው:: ሆኖም፣ ከህወሓት በቀር ይህን የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ የተቃወመ የለም:: ይህ ሲታይ፣
የህወሓት ነገር – ግመል ሰርቆ አጎንብሶ የመሆኑ ሀቅ ይወጣል:: በወልቃይት እና ራያ የፈጸመውን ስለሚያውቅ ኮሚሽኑ
ጭንቀቱ ሆኗል:: ቢሆንም፣ ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርምና ህወሓት ለህጉ ተፈጻሚነት ተባባሪ ሆኖ የህዝብን
ፍቃድ ከማክበር ያለፈ ሚና እንደሌለው ሊያውቀው ይገባል!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*