የሚበጀው የህዝብን ጥያቄ መመለስ ብቻ ነው!

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለበርካታ ዓመታት የአለቃና ምንዝር
ግንኙነት እንደነበራቸው አይካድም:: ከበርሃ የመሳሪያ ትግል ጀምሮ፣ ህወሓት ከፍ ሲል የአለቃነት፣ ዝቅ ሲል የረጂነት
ሚና ይዞ ከቀድሞው ኢህዴን፣ የአሁኑ ብአዴን/አዴፓ ጋር ግንኙነቱን ለዓመታት አቆይቷል:: በዚህ የህወሓት የበላይነት
ባየለበት የሁለቱ ድርጅቶች ግንኙነት ምክንያት፣ ህወሓት በዋናነት ከሚመራው የትግራይ ክልል ውጭ ሳይቀር የአሻውን
እያደረገ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ዘልቋል::
ዛሬ ህወሓት በትናንት ጉልበቱ የለም:: በተለይ፣ ከመሪው መለስ ዜናዊ ሞት ወዲህ፣ ህወሓት የነበረ የበላይነቱን
አስጠብቆ ለመቀጠል አልቻለም:: በነዚህ ጥቂት ዓመታት ኢህአዴግ ውስጥ ባሉ አባል ድርጅቶች መካከል ሽኩቻ
ተፈጥሯል:: በተለይ፣ በህወሓት እና በብአዴን መካከል የተፈጠረው ሽኩቻ ከሌሎችም የባሰ ሆኖ ታይቷል:: ለዚህም
መሠረታዊ ምክንያቶች ነበሯቸው፤ አሏቸውም::
አሁን በሥራ ላይ ያለውን የፌድራል አወቃቀር ህወሓት በበላይነት የተከለው ለመሆኑ ጥርጥር የለውም:: አወቃቀሩ
ተግባራዊ ሲደረግ፣ የፌደሬሽኑ አባላት ሆነው የተዋቀሩት ክልሎች ጉዳይ ብዙ መሠረታዊ ጥያቄዎች ያሉበት ሆኗል::
በተለይ፣ ህወሓት በብቸኝነት የሚያስተዳድረው የትግራይ ክልል ከአጎራባች ክልሎች ነጥቆ ወደ ግዛቱ ያካለላቸው
አካባቢዎች ጉዳይ ህዝባዊ ጥያቄ ያለበት እንደሆነ ከመጀመሪያው ጀምሮ ግልጽ ነበር::
ህወሓት በወቅቱ የፈለገውን የማድረግ ኃይሉ እንደነበረው አሌ አይባልም:: ያን የኃይል የበላይነቱን ተጠቅሞ፣ በተለይ
እንደ ጨቋኝ በሚቆጥረው የአማራ ህዝብ ጥቅም ላይ ያሻውን ለማድረግ ወደ ኋላ የሚል አልነበረም:: በመሆኑም፣
ወልቃይት እና ራያ አካባቢዎችን ያለምንም የህዝብ ፍቃድና ፍላጎት ወደ ትግራይ አካልሏል:: ያ በማናለብኝነት
የወሰነው ውሳኔ ቀስ በቀስ እየተብላላ ቀጥሎ፣ ዛሬ ላይ ለዓመታት ታዛዡ በነበረው ብአዴን/አዴፓ ሳይቀር ጥያቄ ሆኖ
መጥቶበታል:: ብአዴን/አዴፓ ዘግይቶም ቢሆን፣ የህወሓት የበላይነት መቀጠል እንደሌለበት ተገንዝቧል::
በአሁኑ ወቅት ህወሓት እና አዴፓ ጫማ ተለካክተዋል:: የወሰን ጉዳዮች እንደ ዋና ምክንያት ይወሰዱ እንጂ፣
የሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች ከዚህም ባለፈ ተቃቅረዋል:: በዚህም፣ በተለይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በህወሓት እንደ ቁጥር አንድ ጠላት ሆነው ተቆጠረዋል:: አቶ ገዱ ከቀድሞው የትግራይ ክልል
ፕሬዚደንት አቶ ዓባይ ወልዱ፣ እንዲሁም ከወቅቱ አስተዳዳሪ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጋር እሰጣገባ ውስጥ
ሲገቡ ታይተዋል:: በሌሎች የድርጅቶቹ አመራሮች ደረጃም ተመሳሳይ አለመግባባቶች አሉ::
ይህን አለመግባባት ተከትሎ ጥር 03/2011 ዓ.ም. የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
እና ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሃይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በአዲስ አበባ ለመሸማገል
ተቀምጠው ነበር:: ሁለቱ ርዕሳነ መስተዳድሮች በምን በምን ጉዳዮች እንደተሸማገሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ባይገልጹም፣
በጥቅሉ ግን ስለ ሰላም እንደሚሰሩ ሲገለጽ ተሰምቷል::
ይህ የሽምግልና ጉዳይ አሁን የጀመሩት አይደለም:: ያሰቡትን ውጤት አላመጣላቸውም እንጂ፣ ሀገሪቱ በህዝባዊ
ተቃውሞዎች በምትናጥበት ጊዜም አንዴ በመቀሌ፣ በምላሹ ደግሞ በጎንደር ‹‹የሽማግሌዎች ኮንፈረስ›› አድርገዋል::
በተለይ፣ በመቀሌው ኮንፈረንስ አቶ ገዱ፣ ‹‹ጥላቻን እየዘሩ የፍቅር አዝመራን በምላሹ ማግኘት አይቻልም፤›› ሲሉ
ሽምግልናው ከልብ እንዳልተያዘ ጠቆም አድርገዋል:: እንደ ሽምግልና የሚቆጠር ነገር አለ ቢባል እንኳ፣ የአሁኑም ከልብ
ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም::
በእርግጥም፣ አቶ ገዱ እና ደብረፅዮን ተሸማገሉ ከሚባል ተሸናገሉ ቢባል ይቀላል:: የሚሸማገሉበት ጉዳይም
አይኖርም:: የግል ጸባቸውን በሀገር ወግ በሽምግልና ለመፍታት ከሆነ መልካም ነው:: ሆኖም፣ ራሳቸውን በመንግስትነት
አስቀምጠው በህዝብ ጥያቄዎች፣ በተለይም የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች በሆኑ የወልቃይትና ራያ ጉዳዮች አንዳች ለውጥ
በሽምግልና እናመጣለን ብለው ካሰቡ ሽንገላው የጎላ ይሆናል:: እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች ሽምግልና ሳይሆን፣
የፖለቲካ ውሳኔ የሚፈታቸው ናቸው:: ትናንት ወደ ትግራይ ሲካለሉ በፖለቲካ ውሳኔና በኃይል እንደተፈጸመ ሁሉ፣
የተዛባውን አስተካክሎ ወደ ነበሩበት ለመመለስም ፖለቲካዊ ውሳኔና የኃይል ሚዛን ለውጥ ነው የሚያስፈልገው::
በሌላ በኩል፣ የሁለቱ ርዕሳነ መስተዳድሮች መሸማገል በምን ደረጃ እንደሆነም ግልጽ ሊደረግ ይገባ ነበር:: በግል
የሚያደርጉት ሽምግልና ነው? በፖለቲካ ድርጅቶቻቸው ደረጃ ነው? ወይስ ሁለቱን ክልሎች ወክለው? ሁለቱን ክልሎች
ወክለው ከሆነ ነገሩን የበለጠ የፌዝ ጨዋታ የሚያደርገው ይሆናል:: በየትኛውም ሁኔታ፣ ሁለቱ የክልል አስተዳዳሪዎች
የሚሸማገሉበት የህዝብ ጥያቄ እንደማይኖር ሊታወቅ ይገባል:: ትናንት የችግሩ መንስኤ የሆኑ ሰዎች፣ ዛሬ መልሰው
ሊሸማገሉ የሚችሉበት የህዝብ ጉዳይ አይኖርም:: ይህ ከሆነም መሸማገል ሳይሆን መሸናገል ነው የሚሆነው:: የሚበጀው
ደግሞ መሸናገል አይደለም:: የሚበጀው የህዝብን ጥያቄ መመለስ ብቻ ነው::

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*