የዜግነት ኀላፊነታችንን አጥብቀን እንያዝ፤ ስለ ራሳችን ራሳችን እንወስን!

የሚበዛው የፖለቲካ ታሪካችን እንደሚያሳየው ኢትዮጵያዊያን ለሥልጣን ያለን አተያይ መስመር የሳተ ነው፡፡ ከሥርዓትና ተቋም ግንባታ ይልቅ ግለሰቦቸን እናመልካለን፤ በግለሰቦች ዙሪያ መኮልኮልን እንመርጣለን፡፡ በአገራችን መንግሥት የሁሉም ነገሮች (የጥሩም የመጥፎም) ምንጭ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡ ኅብረተሰቡ ራሱን በራሱ በየደረጃው እያደራጀ የራሱን ጉዳይ የሚፈታበት ባህል በጣም ደካማ ነው፡፡  በዚህ ምክንያት ጠንካራ ሲቪክ ማኅበረሰብ ኖሮን አያውቅም፡፡  ጠንካራ ሲቪክ ማኀብረሰብ አለመኖሩ ደግሞ በሥልጣን ላይ ልጓም ለማበጀትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ጎድቶታትል፡፡

አሁንም እዚያው ነን፡፡ በየደረጃው ራሳችንን በራሳችን እያደራጀን የራሳችንና የአገራችንን ጉዳይ መልክ ለማስያዝ የምናደረግው ጥረት ኢምንት ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ አንዱን ጨቋኝ ቡድን በሌላ ቡድን ለመተካት በመረባረብ ላይ ነን፡፡ ሥርዓታትና ተቋማት ስለሚጠናከሩበት ሁኔታ በሙያ ማኅበርም ይሁን በሲቪክ ማኅበራት ተደራጅተን እየታገልን አይደለም፡፡ ስለ ዴሞክራሲ እየተሰበከ ሁሉም ሚዲያ ስለ ዶ/ር ዐቢይና የእሳቸው ደጋፊ ናቸው ስለሚባሉ የተወሰኑ የመንግሥት አመራሮች ነው የሚያወራው፤ ስለ ለውጥ እየተነገረ ከሥርዓትና አስተሳሰብ ለውጥ ይልቅ በግልጽ የሚታየው የገዥ ለውጥ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ዕጣ-ፋንታ በእያንዳንዱ ዜጋ ንቁ ተሳትፎ በእነ ዶ/ር ዐቢይ መልካም ፈቃድ ይወሰን ይመስልን ሁሉም ነገር ለአዲሱ አመራር ተትቷል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከሚያደርጓቸው ንግግሮችና ከሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ተነስተን ብናየው፣ እየተደረገ ያለውን የተክለ-ሰብዕና ግንባታ አዝማሚያ ይፈልጉታል ማለት ያስቸግራል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ከዚህ በአንድ ግለሰብና ቡድን ዙሪያ የመኮልኮል ባህላችን እስካልወጣንና በራሳችን የዜግነት ኀላፊነት እና አቅም ላይ እስካልተማመንን ድረስ የምንፈልገውን ዴሞክራሲያዊና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መገንባት አንችልም፡፡

በጣም ብዙ የቤት ሥራዎች ያሉብን ሕዝብ ነን፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች መወጣት የምንችውል ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ዴሞክራሲ አማራጭ የለውም፡፡ ዴሞክራሲ ደግሞ በእያንዳንዱ ዜጋ ንቁና የተደራጀ ተሳትፎ አማካይነት የሚገነባ ሥርዓት ነው፡፡ አንድን ግለሰብና ቡድን ማምለክ የአምባገነናዊ ሥርዓት ልዩ መገለጫ ነው፡፡ ንቁና የተደራጀ ሕዝብ ሁልጊዜም በባሥልጣናት ላይ ልጓም ማበጀት ይችላል፡፡ ከትናንት እስከዛሬ ደረስ የአገራችን ትልቅ ችግር ሆኖ የቀጠለው ችግር ደግሞ በሥልጣን ላይ ልጓም ያለማበጀት ችግር ነው፡፡ ትልቁ ችግራችን በግለሰቦች ወይም በቡድኖች እንደፈለገው የማይዘወሩ፣ ሕዝብ በሙሉ ልቡ የሚያምንባቸው ገለልተኛና ጠንካራ አገራዊ ተቋማት አለመገንባታችን ነው፡፡ በዚህ ላይ እንረባረብ፡፡ ሌላው ሁሉ አላፊ ጠፊ ነው፤ አይጠቅመንም፡፡ሥርዓት በማቆምና ተቋማትን በመገንባት ላይ እናተኩር!

የሕወሓት ግፈኛ ቡድን የበላይነት ተነኮታኮተ፣ በኢትዮጵያችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባበት ዕድል ተፈጠረ በሚል እምነት በርካታ የሀገራችን ዜጎች ትልቅ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ አሁን የሚታየው አሠራር ሕዝብ ተስፋ ካደረገውና ኢትዮጵያ አጥብቃ ከምትፈልገው ፍፁም ተጻራሪ ነው፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የአንድ አናሳ ቡድን ፍፁም ዘረኛ የአፈና አገዛዝ በሀገርና በወገን ላይ ምን ያህል ውድመት እንዳደረሰ ኢትዮጵያዊያን ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያን ያህል ድጋፍ ያገኘው፣ ሀገራችን ከእንዲህ ዓይነቱ ግፈኛ አገዛዝ ተገላግላ ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ልትሆን የምትችልበትን ዕድል ይፈጠራል በሚል ተስፋ ቢሆንም፣ በግልጽ የሚታየው አንዱን ቡድን በሌላ የመተካት አካሄድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር ዳር የደገፋቸው ወገኖች ያለ ሃፍረት ሕወሓት የሄደበትን የጥፋት ጎዳና ተያይዘውታል፡፡ ብሔር ተኮር የሆነውን የሕዝብ ማፈናቀልም፣ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችን ከላይ እስከታች መቆጣጠሩንም በስፋት እየሄዱበት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እጅግ አደገኛ አዝማሚያ በፍጥነት እንዲታረም ኢትዮጵያዊያን መታገል ይገባናል፡፡ ሁላችንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ካልሆነች ማናችንም ነጻ አንወጣም፡፡

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*