ድንበር ከመክፈት ባሻገር ቀጣይነቱ ሊታሰብበት ይገባል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለሃያ ዓመታት ገደማ ተቋርጦ የነበረው ግንኙነታቸውን እንደገና ከጀመሩ
ወራት አልፈዋል:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ እንደገና የተጀመረው
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ መልካም የሚባሉ እንቅስቃሴዎችን እያየንበት
እንገኛለን:: በዚህም፣ ለሁለት አስርት ዓመታት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተሰቦች ተገናኝተዋል::
በተለይ፣ 2011 አዲስ ዓመት መግቢያ ዕለት በጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ እና በኤርትራው ፕሬዚደንት
ኢሳያስ አፈወርቂ በይፋ ከተከፈተው የዛላምበሳ መስመር ወዲህ፣ የሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች
ግንኙነታቸው በተለያዩ ዘርፎች ጨምሯል:: በዚያ የአዲስ ዓመት መግቢያ ዕለት፣ ከዓመታት በፊት
በነበረው የወንድማማቾች ጦርነት ሺዎች በረገፉበት የቡሬ ግንባር፣ ሁለቱን መሪዎች ጨምሮ የኢትዮጵያ
እና ኤርትራ መከላከያ ሰራዊት አባላት በጋራ በዓሉን ማሳለፋቸው ለበርካቶች ትልቅ እርምጃ ተደርጎ
ተወስዷል::
ከዛላምበሳ መስመር በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች ታኅሣሥ 29/2011 ዓ.ም፣
በኢትዮጵያ በኩል የሁመራ-ኡምናሀጅር፣ እንዲሁም በኤርትራ በኩል በተሰንኤና ጋርሴት የሚያገናኘውን
ድንበር በይፋ ከፍተዋል:: በሥነ ስርዓቱ ላይ የአማራ እና ትግራይ ክልላዊ መስተዳደሮች ፕሬዚደንቶች
የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ተገኝተዋል::
ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የሚያገናኙ ድንበሮች መከፈታቸው፣ ድሮውንም ወንድማማች ለሆነው የሁለቱ
ሀገራት ህዝብ በእጅጉ መልካም የሚባል ነው:: የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝብ አንድነታቸው ሁለንተናዊ
ነው:: በባህል፣ በሐይማኖት፣ በቋንቋ እና በሌሎችም በርካታ ነገሮች የተሳሰሩ መሆናቸው ከማንም የተደበቀ
አይደለም:: ከሃያ ዓመታት በፊት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ጦርነት የህዝብ ፍላጎት ያልነበረበት፣
ይልቁንም የህወሓት እና ሻዕቢያ ጥል እንደነበር ግልጽ ሆኗል:: ሆኖም፣ ጥሉ በሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች
መካከል የነበር ይሁን እንጂ፣ የጦርነቱ ተጎጂዎች ግን ንጹሃን ሲቪሎችና ተራ የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች
ነበሩ:: በዚህም፣ ጦርነቱ በወንድማማቾች መካከል የተደረገ አስከፊና አሰቃቂ ብቻ ሳይሆን፣ ከጅምሩም
መሆን ያልነበረበት ሆኖ አልፏል::
በዚያ አስከፊ ጦርነት ምክንያት የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት ተቋርጦ ቆይቶ፣ አሁን ላይ
እንደገና መጀመሩ ለሚሊዮኖች ደስታን ያጫረ ነው:: ቀደም ሲል በአየር ትራንስፖርት የተጀመረው
ግንኙነት፣ አሁን ላይ በድንበር አገናኝ መንገዶች መከፈት ምክንያት በየብስም መገናኘት ተችሏል:: በዚህም
ታኅሣሥ 29/2011 ዓ.ም የጎንደር-ሁመራ-ኡምናሃጅር-ተሰንዔ መስመር በይፋ ተከፍቷል::
ሆኖም፣ ከመንገዶች መከፈት ባሻገር በርካታ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ መጠቆም
እንወዳለን:: መስከረም 01/2011 ዓ.ም. ተከፍቶ የነበረው የዛላምበሳ መንገድ ብዙም ሳይቆይ ከሳምንታት
በፊት እንደገና መዘጋቱን አንዘነጋውም:: ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ቀድሞውንም መንገዱ ሲከፈት
ቅድሚያ መከናወን የሚገባቸው ተግባራት ሳይከናወኑ መቅረታቸው ነው:: በዚህም፣ የመንገዱ መከፈት
ጊዜያዊ ደስታ የፈጠረና የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች በሰፊው ያገናኘ ቢሆንም፣ ግንኙነቱ ግን መደበኛ
አሰራሮችንና ህጎችን ያላገናዘበ እንደነበር አመላካች ሆኗል:: ድንበር አካባቢ የጉምሩክ ቁጥጥር ጉድለት
በግልጽ ታይቷል:: ይህን ተከትሎ፣ ላልተወሰነ ጊዜ ድንበሩ በድጋሜ ሊዘጋ ችሏል::
አሁንም ቢሆን፣ በሁመራ-ኡምናሃጅር-ተሰንዔ ድንበር አካባቢ ተመሳሳይ ችግሮች ላለመከሰታቸውና፣
ድንበሩ ድጋሜ ላለመዘጋቱ ዋስትና የለም:: በሁመራና መተማ መስመር የህወሓት እጅ እንዳለበት የሚገለፅ
የደሕንነት ችግር መኖሩ ይታወቃል:: ህወሓት ከአማራ ክልል አስተዳደርና ከኤርትራ መንግስት ጋር ካለው
ቁርሾ በተጨማሪ፣ የመከላከያ ሰራዊቱ ስራውን በሚገባ እያከናወነ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ የሰው ህይወት
እየጠፋና ንብረት እየወደመ ይገኛል::
በመሆኑም፣ በተለይ አካባቢው የጦር መሳሪያን ጨምሮ በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚታዩበት
ከመሆኑ ጋር ተገናዝቦ፣ ከድንበሩ መከፈት ባሻገር ህግና ሥርዓትን የተከተሉና ዘላቂ ግንኙነትን ለማድረግ
የሚያስችሉ ጉዳዮች በአግባቡ ሊታዩ ይገባቸዋል:: ከጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ የተጀመረውን ግንኙነት
ሊያደናቅፉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ለማስቀረትም፣ የሁለቱ ሀገራት ግልጽና ዓለም አቀፍ ግንኙነትን
መሠረት ያደረገ ስምምነት ሊኖራቸው ይገባል:: የተደረሱ ስምምነቶች ካሉም፣ ሁለቱ ወገኖች በጊዜ ለህዝብ
ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*