ራስ እንጂ ጅራት መች አጣን? – ብርሃኑ … (ዶ/ር)

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ በጣም ከማከብራቸውና ከሚከብዱኝ መምህራኖቼ መካከል የአማርኛ መምህሬ ቀዳሚው ናቸው። እኒህ ሰው ባለቤትና ተሳቢ አውጡ ብለው ለመጠየቅ እንደ ምሳሌ የሚያመጧቸው ዓረፍተ ነገሮች እጅግ ጥልቅ ምስጢር ያዘሉ ቅኔዎች ነበሩ። ምን ያህሉ ሰው በዚያ መልኩ ይሰማቸው (ይረዳቸው) እንደነበር ባላውቅም በየቀኑ ለማስተማር በሚያነሷቸው ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ ወቅታዊ ጉዳይን የሚተች መልዕክት ያስተላልፉ ነበር። እርሳቸዉ የሚሉትን ከማለት ባለፈ ውስጠ ምስጢሩን እንድንረዳ ምንም ጥረት አያደርጉም። አማራጭ በሌለበት በዚያ ሁኔታ ያለችዉን አጋጣሚ ተጠቅመዉ መተንፈሳቸው፣ ሰሚ ከተገኘም መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው፣ የሚያፈራ ልብ ቢገኝ ደግሞ ዘር መዝራታቸው ነው። ለእኔ ከሰዋስው በላይ ማለት የሚፈልጉትን መልዕክት መመርመር ያስደስተኝ ነበር ሁሌም ባልረዳቸውም። ለዛሬ ርዕስ የመረጥኩባት ምሳሌያቸው “የራሱን ንቆ የሰውን የሚያደንቅ ጅራት እንጅ ራስ መሆን አይችልም፤” ትላለች። የሰው የሆነንና መደነቅ የሚገባውን ማድነቅ ተገቢ ነው። የራስ የሆነን ተወዳጅ ነገር መጥላት፣ መፍራት፣ መሸሽና ማንቋሸሽ ግን የችግር ምልክት ነው። እንዲህ ዓይነት ሥነ ልቦና ይዞ ደግሞ ራስ መሆን፣ አሻጋሪ ሐሳብ ማምጣት፣ ነገን ቀድሞ መረዳት፣ ተረድቶም ለሌላው ማሳየት አይቻልም።

ይህን እንድል ያደረገኝ ደግሞ፣ ባሳለፍነው ሳምንት የሐምሊን ሆስፒታሎች የተመሠረቱበትን ስልሳኛ ዓመት አከባበር ላይ የነበሩ ኹነቶች ናቸው።

ለኛ እንደ ሀገር የሐምሊን ሆስፒታል ፊስቱላን እየጠገነ ዛሬ ድረስ መቀጠሉ የኢሰባዊነታችንና የምናምንቴነታችን ምልክት ነው። ሊያኮራን ሳይሆን ሊያሳፍረን የሚገባ የታሪካችን አካል ነዉ። እያንዳንዷ የፊስቱላ ተጠቂ አቅም ቢኖራትና ሰሚ ብታገኝ ስለደረሰባት ችግር መንግሥትን በሕግ ተሟግታ ማሽነፍ ትችላለች። ፊስቱላ የሚከሰተው መንግስት የመንግሥትነቱን ትንሹን ድርሻ መሠረታዊ የጤና እንክብካቤን መስጠት ሲሳነው ነውና። ለሐምሊን ቤተሰቦች ደግሞ በዛ ዘመን የተመቸ ኑሯቸውን ትተው ይህን ተቋም መመሥረታቸውና በብዙ መከራና ፈተና እያለፉ ለዚህ ደረጃ ማድረሳቸው የትልቅ ስብዕናቸው፣ የታታሪነትታቸዉና የቁርጠኝነታቸው አስረጅ ነውና ሊኮሩበት ይገባል። ይህን ነገር ለመጀመር ካነሳሳቸው ደግነት ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን የመሰለ ተቋም እዚህ ለመድረስ ያለፉበት ፅናት ይደንቀኛል።

ዶ/ር ካትሪንና ባለቤታቸዉ ይህን ሥራ በሚጀምሩበት ወቅት ነገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ አልነበሩም። በማኅበረሰቡ ሆነ በመንግሥት ለችግሩ ተገቢው ዕውቀትና ትኩረት አልነበረም፤ ከዓለም ዐቀፍ ለጋሾችም ይሰጥ የነበረው ድጋፍም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስለዚህም ብዙውን ነገር በራሳቸው ወጭ በብዙ ድካም ይከውኑት ነበር። ባለቤታቸው በዚያ ዘመን አውቶብስ ተራ ድረስ በመሔድ ቀጠሮ ያልያዙላትን የፊስቱላ ተጠቂ ይጠብቁ ነበር ይባላል። ለቀናት በብዙ ስቃይና ድካም ተጉዘዉ አዲስ አበባ የደረሱ ግፉአንን አፈላልገዉ በማግኘት በመኪናቸው ወስደው በነጻ አክመው የተሰበረ ቅስማቸውን ይጠግኑላቸዋል የጨለመ ነጋቸውን ያበሩላቸዋል። ከሕመምተኛነት አውጥተው ከማኅበረሰባቸው መቀላቀል ብቻ አይደለም በፍቅር አቅርበው ዓለም የሚዘምርላቸው ፊስቱላ ጠጋኞች ያደርጓቸዋል። (ማን ነበር ኢትዮጵያ ዉስጥ ሀኪምም ሕክምናም የለም ያለዉ ፊደል ያልቆጠሩት ፊስቱላ ጠጋኞች ማሚቴና ጓደኞቿ ይፋረዱሃል በሉት) በእርግጥ የነዚህን ምስኪኖች ሕመም መጋራት ብሎም መፍታት መቻል በራሱ ኅሊና ላለው የፅናትም የደስታም ምንጭ ይሆንለታል። ግን እንዴት ሙስናውን ቢሮክራሲውን መጠላለፉን ሁሉ አለፉት? ነው እንዲህ ያለው ውጣ ውረድ ነቢይ በሀገሩ አይወደድም እንዲሉ ለሀገሬው ጀግና እንጅ ከሰው ሀገር ለሚመጡት የለባቸዉም?

ዛሬ በብዙ ምክንያት ነገሮች ተቀይረዋል። በሀገራችን አራቱም አቅጣጫዎች የፊስቱላ ሕክምና ማዕከላት ተከፍተዋል፤ ለሕክምና አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ያጋጥም የነበረዉ ስቃይ በጥቂቱም ቢሆን ቀንሷል፤ በቂም ባይሆን ባሉት አንድ አንድ ጥረቶች የፊስቱላ ሰለባዎች ቁጥር እየቀነሰ ነዉ። በዚህ ላይ በአሁኑ ጊዜ የፊስቱላ ተጠቂን እናት ፎቶ ይዞ ፓሪስና ዲሲ ሎንደንና ሲድኒ አደባባይ ላይ መገኘት፣ የባለፀጎችንና የታዋቂዎችን በር ማንኳኳት አዋጭ የገቢ ምንጭ ሆኗልና ሰብአዊነቱ የሌለባቸው ሆዳሞች ሳይቀር በዚህ ተግባር ተሰማርተውበታል። ሥራ ሠርቶ ገንዘብ ማግኘቱ ነውር ባይሆንም ሰብዓዊነታቸዉን ስተው ምስኪን በሽተኞችን እንደ ሸቀጥ የሚቆጥሩ፣ ስቃያቸውንም መተዳደርያ የሚያደርጉ “ምሁራን”፣ ባለሥልጣናትና ተቋማት (መንግሥታዊዎችንም፣ የእርዳታ ድርጅቶችንም ያካታል) በፈሉበት በዚህ ዘመን መጥተው ቢሆን ባልገረመን፤ አልያም በጠረጠርናቸው ነበር። የሐምሊን ቤተሰቦች ግን ማንም ባልነበረበት ወቅት የተገኙ፣ ተስፉ ባልነበረበት ዘመን ተስፋን የዘሩ ልዩ ስጦታዎቻችን ናቸው። ለዚህም ጋዎናቸው ንጹሕ ስለሆነ ሳይሆን በንፁህ ልብ ለሠሩት የሰብአዊነት ማሳያ ስለሆነው ሥራቸው በሁላችን መወደድ መወደስ ይገባቸዋል። የሐምሊን ቤተሰቦች አርኣያ ሊሆኑ ይገባቸዋል። አርኣያነታቸውም ምንም በሌለበት ሁኔታ ለኔ ማለትን ትተዉ ምቾት ሳያሸንፋቸዉ ችግርን ሁሉ ተጋፍጠው ለዓለም ሁሉ ምሳሌ የሆነ ተቋም በመፍጠራቸው ነው። ሐውልት ቢቆምላቸውም በብዙዎች ልብ ከተከሉት ፍቅር ጋር አይስተካከልም እንጅ ይገባቸዋል።

ግን እነኝህ ሰዎች ኢትዮጵያዊያን ቢሆኑና ይህን ለማድረግ አቅሙ ፍላጎቱ ቢኖራቸው የፈጠርነው ሥርዓተ ማኅበር ይህን ያህል እንዲሄዱ ይፈቅድላቸዉ ነበር ወይ? በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ሆነው በሀገራቸው ላይ ብዙ የሚታይ ሥራ የሠሩና እየሠሩ ያሉ ጥቂት ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል። ግን ያ በር ለሁሉም ሀገሬን ልርዳ ለሚል ወገን ክፍት ነውን? ሕገ-ወጥ የሆነ መለያ (ማቅረቢያም ማራቂያም) መስፈርት የለምን?

ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ ፍቅሩን፣ ጉልበቱን ይዞ የመጣን ሀገር ወዳድ ዜጋ ሴራ ጎንጉነን አንጠልፈውም ነበር? በመልካም አስተዳደር እጦት አንገቱን አናስደፋውም ነበር ወይ? በመርዘኝ መዋቅሮቻችን መርዘን አንገለዉም ነበር ወይ? በሀገር ዉስጥም ከሀገር ዉጭም ያሉ ብዙ ሀገር ወዳዶች ለሀገር በመቆማቸዉ ወገኔን በማለታቸዉ ምን ደረሰባቸው? ማክበሩ ቀርቶ ያሳደዳቸው፣ ማንገሱ ቀርቶ ወደ ግዞት ያወረዳቸው፣ ሐውልት ማቆሙ ቀርቶ መቆምያ የነሳቸው ማን ነው? ሀገሬውን በሐሰት ውንጀላና በፈጠራ ታሪክ አናክሶ የጎሪጥ የሚተያይባት በተቃራኒዉ የውጭ ሀገር ዜጋ ያለ በቂ ትምህርት ዝግጅት ያለአስተማማኝ ክህሎት በሕገ-ወጥ መረጃ ያለከልካይ ገብቶ ሀገርን ትዉልድን የሚገድልበት ለእኛ ቀጋ ለሌሎች አልጋ የሆነን አሠራር ማን ፈጠረው? አላወቀችበትም እንጂ ይህች ሀገር እኮ በየአጋጣሚው የምታቃልለውን በየምክንያቱ የምትገፋውን ዜጋ የሚያክል ሀብት አልነበራትም። ግን ምን ይሁን ጅራቶች ራስ የሆኑባት ሀገር ሆነችና ለመጣው ሁሉ እያቆለቡ ፍርፋሪ ለጣለላቸው ሁሉ እየተቆሉ ጉዟችን ሁሉ ቁልቁል ሆነ። የጥራዝ ነጠቅ አስተሳሰብ ዉጤት የሆነው የመጠፋፋት የመጠላላት ፖለቲካችን ባለ ሀገሮችን በሀገራችን እርስ በርስ የምንፈራራ ሀገር አልባ አድርጎ መጻተኞች ደግሞ በነጻነት ከጫፍ ጫፍ የሚምነሸነሹባት የባዶዎች ርስት የሆነች ባዶ ሀገር ሰጠን። ይህ ሁሉ የደረሰበትን የግፉ ሰለባና ዉጤት የሆነውን ምስኪን ለፍቶ አዳሪ ዜጋ መካስ ባይቻል ተወቃሽ አድርጎ ማቅረቡ ፋይዳው ምንድን ነው? ሀገራችን በምትናጥበት በዚህ ከፋፋይ አስተሳሰብ ወላ

ጆች ተጠምቆ፣ የእነርሱን መርዛማ ትምህርት እንደ ወተት እየተጋተ አድጎ፣ ለዘመናት ከዳሚያቸውና ጉዳይ ገዳያቸው ሆኖ፣ ይህም ሁሉ ሳይበቃው ዛሬም የዛው ሥርዓት ጧሪና ተጠሪ የሆነ አካል በላቡ አዳሪውን መንደርተኛ አርጎ መሳል ራስ ገርፎ እራስ መጮህ ነው። የራስን እንቁ እያናናቁ ፍትሐዊ ጥያቄን ለጊዜዉ ማፈን የዋሃንን ለጊዜው ማታለል ይቻላል ግን ዘላቂ መፍትሔ አይደለም። እንዲህ እያደረጉም ራስ መሆን አይቻልም ኢትዮጵያ ደግሞ ከመቸዉም ጊዜ በላይ ዛሬ በብሩህ ሐሳብ የሚመራ ሐሳብን የማይፈራ ራስ ትሻለች።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*