ልጥ ፓርቲ አማን ነው ወይ?

ሰላም ወዳጄ! አማን ነው ወይ? እኔ ደህና ነኝ::

ታስታውሳለህ ወዳጄ? አንድ ሰሞን አቀባበል የሚባል ወጀብ ናላችንን አዙሮን ነበር:: የባነሩ ዝግጅት፣ የሚዲያው ጋጋታ፣ የደጋፊዎች ፉክክር፣ የታይታ ሸመታ፣…ነገሩ ሁሉ ጥድፊያ የበዛበት ሆኖ የምንይዝ የምንጨብጠውን አጥተን ሰነበትን:: ወገኖቻችን ነበሩና ወደ ሀገር የሚመለሱት ወገባችንን ሸብ አድርገን መቀበላችን የወግ የባህላችን ነው:: አንዳንዴ ግን ማሸርገድ አብዝተን ነበር ልበል? ግን ግን፣ ስንትና ስንት ግለሰቦችና ልጥ ፓርቲዎችን ድምቅ አድርገን ተቀብለን ይሆን? ደሞ፣ ልጥ ፓርቲዎች እነማን ናቸው ትለኝ ይሆናልኮ ወዳጄ:: ይሄንማ በአዲስ መስመር እናብራራለን!

ይኸውልህ ወዳጄ…ልጥ ፓርቲ ሊቀመንበር አለው፤ ሦስት ታጋዮች ደግሞ ትጥቃቸውን ፈትተው፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ሀገር ውስጥ የሚገቡ ስለመሆናቸው በሊቀመንበሩ ተነግሮላቸዋል:: ታዲያ ሊቀመንበሩ በጣም ገራሚ ናቸው! እንዴት አትለኝም ወዳጄ? አዎ፣ የልጥ ፓርቲ ሊቀመንበር ከየመን ከሚገቡ ሦስቱ አባላቱ ጋር ከውጭ እንደተመለሱ ሆነው አብረው አቀባበል የሚደረግላቸው ናቸው:: ይህን ለምን ልታዘዝ ደንበኞች በኩራት ተናግረዋል:: ስለ ምን ልታዘዝ ከታች እንግርሃለሁ:: ሄሄ፣ የልጥ ሊቀመንበር ታዲያ ገራሚ አይደሉ? እናማ፣ እንዲህ ላሉት ልጦች ሁሉ ነው ለአቀባበል ስናሸረግድ የባጀነው፣ ወዳጄ:: ይሁን፣ ለወገን ያልሆነ ማሸርገድ፣ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ሊባል ይችላል::

ወዳጄ፣ ልጥ ፓርቲ በእውን ህልውና ያለው እንዳይመስልህ ደሞ! ቴሌቪዥን ታያለህ? ቢያንስ አልፎ አልፎ? በቃ አታስብ፣ ካላየህ ስለ ልጥ ትንሽ እገልጥልሃለሁ:: ‹‹ምን ልታዘዝ?›› የሚል አንድ የቴሌቪዥን ተከታታይ ሲትኮም ድራማ አለ:: እዚያ ድራማ ላይ የልጥ ፓርቲ ሊቀመንበር ነኝ የሚሉ ገጸ ባህሪ አሉ:: ጉደኛ ናቸው! እንግሊዝኛ መናገር ያበዘሉ:: ያው፣ አዋቂ ነኝ ለማለት ፈልገው ነው እንግሊዝኛ የሚያበዙት:: ሄሄ፣ ጉደኛ ናቸው ስልህ!

የልጥ ሊቀመንበር እቅድ የላቸውም፤ በእጃቸው ባልያዙት ጉዳይ ‹‹እንዲህ አደርጋለሁ፣ እንዲያ አደርጋለሁ›› ይላሉ:: ግን ምንም አቅም የላቸውም:: የልጥ ሊቀመንበር የምርጫ ምልክት እንኳ ፈልገው በማጣት ሲቸገሩ ይታያሉ:: ‹‹ምልክቱ ሁሉ ተያዘ፣ ምልክት የት ይገኝ?›› ባይ ናቸው የልጥ ፓርቲ ሊቀመንበር:: ድሮስ ልጥ! ሄሄ፣ ልጥ ምርጫ ምልክት ፈልጎ ሲያጣ፣ መፍትሄ የሚሰጠው ማን መሰለህ? አያልቅበት የሚባለው በቅርብ በለውጡ ምክንያት ወንበሩን የተቀማው አያልቅበት ነው አጋዡ:: እንዴ! በነገርህ ላይ አያልቅበት ሌላው ገራሚ ሰው ናቸው:: ወደ ወንበራቸው ለመመለስ የማያደርጉት ነገር የለም! ሚዲያ ፈልጉልኝ ልናገር ይላሉ፤ መጽሐፍ ጽፌያለሁ ይላሉ፤ የካፌው አስተዳዳሪ ነበሩ:: ምን ዋጋ አለው…ለውጡ ወንበራቸውን አሳጣቸው! ታዲያ፣ ወደ ወንበር ለመመለስ፣ ወንበር የቀማቸውን መረበሽ እንደ ስልት ይዘውት ነበር:: ለዚህ ዓላማቸው ማንን ሲጠቀሙ ቢታዩ ጥሩ ነው? ልጥ ፓርቲዎችን ነዋ! ሄሄ፣ ድሮስ ልጥን ማን ፈጠራቸው? እነ አያልቅበት አልነበሩምን?!

ጦቢያ ልጥ ፓርቲዎች ሞልተዋታል:: ከ80 ይበልጣሉ:: አንዳንዶች፣ ውጭ ሀገር ነበርን ይላሉ፤ ቀሪዎቹ እዚሁ ሀገር ቤት ‹‹እልህ አስጨራሽ ትግል ላይ ነበርን›› የሚሉ ናቸው:: ነጻነትንኮ የሚያውቁት አይመስሉም:: ምን ሆነ መሰለህ ወዳጄ? አዎ፣ ድንገት ሳያስቡት ልጥ ፓርቲዎችን ህዝብ ታግሎ ነጻ አወጣቸው:: ሊያታግሉ ነበርኮ የተመሰረቱት! እናማ አልሁህ፣ ልጥ ፓርቲዎች ባዶ ጀብደኞች ናቸው::

በቀደም ምን ሆነልህ መሰለህ? የ‹‹ምን ልታዘዝ›› ልጥ ፓርቲ ሊቀመንበር ካፌ ውስጥ ማስታወቂያ ለመለጠፍ ትብብር ይጠይቃሉ:: ሆኖም፣ ካፌው ትብብር ይነፍጋቸዋል:: ጓድ የልጥ ሊቀመንበር በእንግሊዝኛ ተንጣጡ አልሁህ! ‹‹I will exercise my rights›› አሉ:: በካፌው ላይኮ ነው ይህን የሚደነፉት! ወዳጄ፣ ቀጥለው ምን ቢሉ ጥሩ ነው? ‹‹ችግሩን በራሴ መንገድ እፈታዋለሁ›› አላሉም!? ማን ነበር በቀደም ‹‹እንተናን እጠራብሃለሁ›› ያለው? በቃ እንዲህ ሆነን አርፈነዋል፤ ማንም ተነስቶ፣ ‹‹ጦሬን አዘምታለሁ! ፊትህን ቀለም እቀባሃለሁ!›› ምናምን ይልሃል! ምንም ሠራዊት የሌለው ቱሪናፋ ሁሉኮ ነው የሚደነፋብህ! ሄሄ፣ አይ ልጥነት…!

ደግነቱ ምን መሰለህ ወዳጄ? ሄሄ፣ ልጥ ፓርቲዎችን ህዝብ አንጠርጥሮ ያውቃቸዋል:: እናማ፣ በሌላቸው አቅም ሲንጠራሩ ሲያይ ይዝናናባቸዋል:: የ‹‹ምን ልታዘዝ›› ልጥ ፓርቲ ሊቀመንበር ካፌውን ትብብር በጠየቁ ጊዜ፣ አንዲት የካፌው መስተንግዶ ሰራተኛ፣ ‹‹ይሄ ጥያቄ የመዝናኛ ጥያቄ ነው›› ብላ ወደመዝናኛ ክፍል ትመራቸዋለች:: የመዝናኛ ክፍል ኃላፊዋ ግን ጥያቄው ፖለቲካዊ ነው ብላ ትመልሳለች:: ይህኔ ጓድ ሊቀመንበር በእንግሊዝኛ ተንጣጡዋ! ‹‹Yes, this is politics. Politics is my life. ካፌው ትብብር የማያደርግልኝ ከሆነ፣ ችግሩን በራሴ መንገድ እፈታዋለሁ›› አሉልሃ:: ‹‹ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አዝናኝ ነገር አለ?›› ስትል ጠየቀች መስተንግዶ ሰራተኛዋ ሁኔታቸውን አይታ:: እንዲህ ነው ልጥነት::

ወዳጄ፣ አንድ ነጥብ ረሳሁ፤ አንዳንዶች ልጥ ፓርቲዎች ሌሎችን በመውቀስ፣ በሀሰት ስም ማጥፋት የተካኑ ናቸው:: እዚህ ሀገር ቤት የከረሙት ልጦች ሀቀኞችን እየተከታተሉ ለወያኔ ሲመርጁ የቆዩ ናቸው:: ደሞ ይሄን እንዴት አወቅህ ብለህ እንዳትጠይቀኝ:: ‹‹ጫሚሶን ያዬ በአዎሉ አይጫወትም›› አሉ የአራት ኪሎዋ እማማ ደስታ!

ደሞ አሉልሃ ‹‹በረሃ ነበርን›› የሚሉ ልጦች:: ያው፣ እንደ ‹‹ምን ልታዘዝ›› ልጥ ሊቀመንበር፣ ሦስት ‹‹ታጋዮችን›› ከየመን ተቀበሉልን ሲሉን የነበሩትኮ ናቸው:: አይ የአቀባበል ሰሞን ግርግር! ይምጣብኝ…ቀውጢ አድርገነው ነበርኮ! ሄሄ፣ ስንቶቹ በግርግር ሀብታም ሆኑ መሰለህ? ቲሸርት ህትመቱ፣ ባነሩ፣ ሰንደቅ አላማው… ገበያው ደርቶ ነበር:: በዚህ ሁኔታ ተቀብለን ስናያቸው፣ ብዙዎቹ ልጥ ሆነው አርፈውታል:: አንድ ተስፋ ብቻ ይታየናል፤ ልጥ ፓርቲ ይዋጥ ይሆናል! ካልተዋጡስ? ህዝብ እየተዝናና ይተፋቸዋላ! ለመሆኑ ልጥ ፓርቲዎች ተመዘገቡ ይሆን? አንድ ሊቀመንበር ከሦስት አባላት ጋር ፓርቲ ነን ብለው መመዝገብ ‹ሼም› ነው አይደል? ለነገሩ፣ ‹ሼም› ሲኖራቸውኮ ነው!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*