በተገንጣዮቹ የተወጠረው “ለውጥ” – ጌታቸው ሺፈራው

ኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ካፈራቸው ቡድኖች መካከል አሁንም ድረስ የቀጠሉት፣ የተማሪው እንቅስቃሴ በስፋት ከሚነገርት ዓላማ ያፈነገጡት ቡድኖች ናቸው:: ከእነ ችግራቸው የኢትዮጵያን ዓላማ አንግበውና የተማሪው እንቅስቃሴ ዓላማ ነበር የሚባልለትን የያዙት ብዙም ሳይጓዙ በተገንጣዮቹ ተጠልፈዋል:: በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያን ጉዳይ እናስቀድማለን ያሉ ቡድኖች ተውጠው የቀሩት እንደ ህወሓትና ኦነግ ባሉ ተገንጣዮች ነበር:: ሁለቱ ቡድኖች ፀረ ኢትዮጵያ በሆኑ የውጭ ኃይሎች ድጋፍ፣ ኢትዮጵያዊነትን እናራምዳለን የሚሉ ቡድኖችን አዳክመዋል:: ህወሓትና ኦነግ ከነበራቸው ተመሳሳይ የመገንጠል ዓላማ ባሻገር በኢትዮጵያዊ ኃይሎች፣ እንዲሁም እንደ ሕዝብ በአማራው ላይ በነበራቸው የጋራ አቋም የአብዮቱን ዘመን ተሻግረው አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ለመግባት ደርሰዋል::

ኢትዮጵያን ሲያወግዙ የነበሩት ሁለቱ ተገንጣይ ቡድኖች የራሳቸውን ዓላማ የሚያሳኩበት የሽግግር ቻርተር፣ ብሎም አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ሌንጮ ለታ ያረቀቁት ‹‹ሕገ መንግስት›› ሲያወግዟት ለነሩት ሀገር በሰነድነት አቅርበዋል:: አንድ ላይ ተሰልፈው ወደ ቤተ መንግስት የገቡት ኦነግና ህወሓት በሽግግር መንግስቱ ወቅት ስልጣን ተከፋፍለዋል:: ያገዟቸው ኃይሎች እንገነጣጥላታለን ባሏት ሀገር ስልጣን ላይ እንዲቀመጡ ቢያደርጉም፣ ያላሰቡትን ስልጣን በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም:: አንደኛው ሌላኛውን አልፎ ለመሄድ ሲጣጣሩ ኦነግ ተሸንፎ ከሀገር ወጣ::

‹‹አሸባሪው ኦነግ››

የህዳጣን ወኪል ሆኖ ኢትዮጵያን ማስተዳደር እንደማይችል ያወቀው ህወሓት፣ ለኢትዮጵያ ባለው አተያይ እኩያው ከሆነውና ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ ይወክላል ከተባለው ኦነግ ጋር ተባብሮ ስልጣኑን ማደላደል ነበረበት:: ከወከለው ሕዝብ ቁጥር አንፃር ኢትዮጵያን ለማስተዳደር እንደሚከብደው የማይስተው ህወሓት በ17 ዓመታት ትግሉ ሲመካ፣ ኦነግ በበኩሉ ወክየዋለሁ በሚለው ሕዝብ ቁጥር ለህወሓት ፈርጣማ ጡንቻ እንዳለው ለማሳየት ሲጥር እንደነበር ይነገራል:: የኢትዮጵያን ፖለቲካ መቆጣጠር የፈለጉት የውጭ ኃይሎች ወቅታዊ ድጋፍና የተገንጣይ ቡድኖቹ ያላሰቡትን ስልጣን ለየራሳቸው ለመጠቅለል የነበራቸው ስግብግብነት ኦነግን ተባራሪ አድርጎታል:: የ17 ዓመታቱ ትግሉን ጀብድ ተሸክሞ አራት ኪሎ የገባው ህወሓት፣ ኦነግ የሚያሳየውን እኩያነት ሲውል ሲያድር ስልጣን እንደሚያሳጣው በማሰብ በቁጥር በርከት ያለውን የኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚያስቀምጠው ኦህዴድ የተባለ ከደርግ ከተማረኩ ወታደሮችና ከኢህዴን ታጋዮች መልምሎ መመስረቱ የሁለቱን ተገንጣዮች ፍትጊያ አባብሶታል::

ባለፉት 27 ዓመታት ህወሓት ኦህዴድን በመጠቀም፣ ኦነግን ከኦሮሚያ ለማስወጣት ጥሯል:: በዚህ ሂደት ኦነግ ከወሰዳቸው እርምጃዎች ባሻገር እወክለዋለሁ በሚለው የኦሮሞ ሕዝብ ጭምር ለማስጠላት ህወሓት ይሸርባቸው በነበሩ ሴራዎችና በኦነግ አልሞት ባይ ተጋዳይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ፍንዳታዎች ደርሰዋል:: በዚህ ሰበብ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ታስረዋል፣ ተሰቃይተዋል:: ህወሓትና ኦነግ ሲሰሯቸው የነበሩ ተግባራት ተደምረውም ህወሓት በበላይነት በሚመራው ፓርላማ ኦነግ በአሸባሪነት ተፈርጆ ቆይቷል:: በሽግግር መንግስቱ ወቅት በነበረ የስልጣን ሽሚያ ከህወሓት ጋር የተጋጨው ኦነግ ወታደሮቹን ሰብስቦ ካስረከበ በኋላ አመራሮቹ ተሰድደው ቆይተዋል:: ከህወሓትና ከኦህዴድ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ እርስ በእርሱ መስማማት ያልቻለው ኦነግ ሕዝብ በውል ወደማያውቃቸው ቡድኖች እንደተከፋፈሉ በስሙ ወደሀገር ቤት የሚገቡትን አካላት ማየት በቂ ነው::

‹‹ለውጥ›› እና የሁለቱ ቡድኖች አባዜ

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሽብር የተፈረጁ ቡድኖች ፍረጃቸው ተነስቶ ወደ ሀገር እንዲገቡ ሲወሰን ሁለቱ ተገንጣይ ቡድኖች መካከል የተለያዩ አቋሞች እንደነበሩ ግልፅ ነው:: ህወሓት ራሱ ያባረራቸውና የፈረጃቸው ቡድኖች ‹‹ምህረት ይደረግላቸው›› ሲባል የሕገ መንግስት ጥሰት ነው ሲል ሽንጡን ገትሮ ተከራክሯል:: በአንፃሩ አሳዛኝ ተሸናፊ ሆኖ ከኢትዮጵያ የተባረረው ኦነግ በተለያዩ ቡድኖቹ ‹‹ለውጡን እደግፋለሁ›› ብሎ ወደሀገር ቤት አቅንቷል:: እየቆየ ግን ከለውጡ እጠቀማለሁ ብሎ ሮጦ የመጣው ኦነግ እና ለውጡ እንደሚያጠፋው የሰጋው ሕወሓት በጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዝ ጀምረዋል:: ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ታጣቂ ኃይሎች በሁመራ በኩል ምንም አይነት አቀባበል ሳይደረግላቸው ሲያልፉ የኦነግ ሰራዊት መቀሌ ላይ የህወሓት መስራቾች የኦነግን አርማ ይዘው ግብዣ አድርገው ሸጥተውታል::

ህወሓት ለኦነግ ታጣቂዎች ደማቅ አቀባበል ሲያደርግ ኦነግ ቂሙን ይረሳል ብሎ አይደለም:: ኦነግም ታጣቂዎቹን በመቀሌ በኩል ሲያሳልፍ ህወሓት የፈፀመበትን ዘንግቶት አይደለም:: ሮጦ ለማለፍ መሽቀዳደምን የለመዱት ሁለቱም ቡድኖች ካፈው ፍትጊያቸው ይልቅ የወደፊት ዕጣቸውን በማሰብ እንደሆነ ግልፅ ነው:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ የሚመራው ‹‹ለውጥ›› ህወሓትን ስደተኛ፣ ስደተኛ የነበረውን ኦነግን የክብር እንግዳ ቢያደርገውም ቅሉ ሁለቱም በዓይን ጥቅሻ የሚስማሙበት አጀንዳ ግን አላጡም:: ዐቢይ ስለኢትዮጵያዊነት ሲሰብኩ ሕወሓትንና ኦነግ ኢትዮጵያ ላይ የነበራቸውን ትርክት የሚያፈርስ ነበር:: ሁለቱ ቡድኖች በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ላይ የተመሰረቱ እንደመሆናቸው ስለ ኢትዮጵያዊነት በአዲስ መልክ የተደረገው ትርክት ባለፈው ታሪካቸውን የሚያጋልጥ፣ የወደፊት ተስፋቸውን የሚያጨልም ስለመሆኑ ተገንዘበውታል:: ሁለቱ ተገንጣዮች በትግሉ ወቅት አንድ ያደረጋቸው በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አሉታዊ አቋም፣ በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ እንደመሆኑ፣ በጠ/ሚ/ር ዐቢይ መንግስት ሕዝብን የሰበኩበት መንገድም የትናንት ፍትጊያቸውን አስረስቶ የሚያጨባብጣቸው አጋጣሚ ነበር::

በሌላ በኩል፣ ህወሓት ኦነግን ለማባረር የፈጠረው እና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያስቀመጠው ኦህዴድ ውስጥ የመጡ ‹‹የለውጥ ኃይሎች›› ስልጣኑን እንደሚሳጡት ስጋቱ ቢሆንም፣ በሚንቀው ኃይል የደረሰበትን ሽንፈት ለመቀበል ፈቀደኛ አልሆነም:: በተመሳሳይ ኦነግም እንደ ኦሮሞ በማያየውና የኦሮሞን ሕዝብ ሲያስገዛ የነበረ ጠላት ነው የሚለውን ኦህዴድን አምኖ መቀበል አልቻለም:: ህወሓት እንደ አሽከር፣ ኦነግ እንደ ተላላኪና የሕዝብ ጠላት አድርጎ ሲዘምትበት የኖረውን ኦህዴድን አምኖ አለመቀበል ቢያንስ ለጊዜው ሮጠው ለማለፍ ላሰቡት ጉዟቸው ‹‹ለውጡን›› ተቃርኖ በመቆምና የጠ/ሚ/ር ዐቢይን መንግስት በማባከን እንዲሰማሩ አድርጓቸዋል::

ህወሓትና ለውጡ

ዐቢይ ጠ/ሚ/ር በሆኑ ማግስት በተደጋጋሚ ሲያሰሙት በነበረው መልካም ንግግር ከተሸፈኑ በርካታ ጉዳዮች መካከል ለኦነግና ህወሓት ላይ ያሳዩት መለሳለስ ነው:: ዐቢይ ስልጣን ከያዙ በኋላ በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ኃላፊዎች ከተደረገ ጥቃት ጀምሮ እስከ ሰኔ 16 የፈንጅ ፍንዳታ፣ ከጅግጅጋው ሰቆቃ እስከ ቤንሻንጉሉ አረመኔያዊ ተግባር ብዙ ሴራዎችና ወንጀሎች ተፈፅመዋል:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በተደጋጋሚ ‹‹የቀን ጅቦች ተግባር ነው›› ከማለት አልፈው የማን እጅ እንዳለበት እስከመጠቆም ቢደርሱም፣ ለረዥም ጊዜ እርምጃ ሲወስዱ አልታዩም:: ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላም በቀጥታ ካመሩባቸው መካከልም ህወሓት በተዘዋዋሪ ሲያሾረው ወደነበረው ጅግጅጋ እና መቀሌ አቅንተው ከስልጣን ከተባረሩት ጉምቱ የህወሓት ባለስልጣናት ባሻገር ያለውን የህወሓት ካድሬና ሕዝብ ሲማፀኑ ታይተዋል::

ህወሓትን ለማባበል ባደረጉት ጥረትም ባለፉት 27 ዓመታት በግልፅ የዘር ማጥፋት የተፈፀመበትን ወልቃይት የመልካም አስተዳደር እንጅ ሌላ ችግር የለበትም እስከማለት ደርሰዋል:: ይህን መለሳለሳቸውን የተመለከተው ህወሓት በመላ ሀገሪቱ ትርምስ ከመፍጠር ባሻገር ትግራይ ውስጥ የጠ/ሚ/ር ዐቢይ ስም በበጎ እንዳይነሳ አድርጓል:: በተለይም፣ ከኦነግ ጋር ባረቀቀው የሽግግር ቻርተር ከአማራው የነጠቃቸው ወልቃይትና ራያ ‹‹ለውጡን እንደግፋለን›› ያሉ ለእስር፣ እንግልት፣ ብሎም የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል:: ዐቢይ በማባበል የጀመሩት መንገድ ህይወታቸውን እስከማሳጣት እንዳደረሳቸው ሲያውቁ፣ ህወሓት የተቆጣጠረውን የደሕንነት መስርያ ቤትና የጦር ኃይሉ ላይ ለውጥ ከማድረግ ባለፈ እንዳላዩ ያልፏቸዋል የተባሉትን ግለሰቦች በሕግ እስከመጠየቅ ደርሰዋል:: ይህም ሆኖ መቀሌ ላይ የመሸገው ህወሓት አሁንም ድረስ፣ የመንግስትን ስልጣን እንደማይቀበል በየጊዜው በሚያወጣቸው ይፋዊ መግለጫዎች እያሳወቀ ነው:: ፍርድ ቤት የያዘውን ጉዳይ በመቃወም ሰልፍ በመጥራት የዐቢይን መንግስት አውግዟል::

ከዚህም ሲያልፍ በወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን አሳልፎ እንደማይሰጥ በይፋ እየገለፀ ይገኛል:: ባለፈው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ውስጥ ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰትና ዘረፋ የፈፀሙት እንዳይጠየቁ ከለላ ከመስጠት ባሻገር፣ ጠ/ሚ/ሩን በመኮነን ላይ ይገኛል:: ይህን ከፌደራል መንግስቱ ያፈነገጠ የህወሓት ተግባር መንግስትም ሳያፍር ለሕዝብ እየገለፀ ነው:: የመንግስት ተግባር ሕግ ማስከበር ሆኖ እያለ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ሲባል ትግራይ ውስጥ ተደብቋል ያለውን አቶ ጌታቸው አሰፋ ከመያዝ ስለመቆጠቡ ለሕዝብ ተናግሯል:: ትግራይ የነበረው ሰራዊት ወደሌላ ቦታ ይዛወር ሲባል ሕወሓት ‹‹አስፓልት ላይ ተኝታችሁ ታንክ ረግጧችሁ ይለፍ እንጅ ሰራዊቱን እንዳታሳልፉ›› ብሎ እንደመከረ ይነገራል:: በዚህም ምክንያት ሰራዊቱ በሕዝብ ታግዶ ይገኛል:: ተጠርጣሪዎችን ከመያዝ ባሻገር ሰራዊቱን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ያልቻለው የፌደራል መንግስቱ አቅመ ቢስነትና የህወሓት አልሞት ባይ ተጋዳይነት ጦርነት ይቀሰቅሳል የሚል ስጋትን ደቅኗል::

‹‹መሳርያ አላወርድም›› ያለው ኦነግ

መስከረም 6/2011 ዓ.ም. ከእነ ሌንጮ ለታና ጀኔራል ከማል ገልቹ በኋላ የገባው የዳውድ ኢብሳው የኦነግ ክንፍ አዲስ አበባ ላይ አቀባበል የተደረገለት ቀን ነው:: አቶ ዳውድ ኢብሳ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ሲባል የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የኦነግ ሰንደቅ አላማ ቀለም ተቀቡ:: ከዚህም ሲብስ ዱላ የያዙ ወጣቶች የዐጤ ምኒልክን ሀውልት እናፈርሳለን ብለው ምኒልክ አደባባይ አካባቢ ሲያንዣብቡ ዋሉ:: መሃል ከተማ ላይ ይህን ተግባር የፈፀሙ ወጣቶች በሕግ አልተጠየቁም:: የአቶ ዳውድ ኢብሳ አቀባበል በተደረገ በማግስቱ ቡራዩ ላይ መንግስት እንዳይነገር የሸሸፋፈነው አረመኔያዊ ተግባር ተፈፀመ:: ለዚህ መሸፋፈኛ ይሆን ዘንድ የዳውድ ደጋፊዎች መንገድ ሲቀቡና መሃል ከተማ ያለውን ሀውል ካላፈረስን እያሉ ሲገለገሉ በትግስት ያያው የአዲስ አበባ ወጣት በጅምላ ታስሮ ወደወታደራዊ ካምፕ ተላከ:: ከጅምሩ ‹‹ተው›› ያልተባለውና በመንግስት ማበረታቻ ያገኘው ፅንፈኛ ኃይል አዲስ አበባምና ኦሮሚያ ላይ ያሻውን ሲያደርግ መንግስት እንዳላየ አለፈው::

የዳውድ ኦነግ ከጅምሩም ከሌሎች ታጣቂ ቡድኖች የተለየ ክብር ተሰጥቶታል:: አርበኞች ግንቦት 7፣ አዲኃን፣ ደምኢት፣ የመሳሰሉ ቡድኖች ጋር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደረጃ ድርድር አልተደረገም:: በአንፃሩ ለኦነግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ተመላልሰዋል:: ከድርድሩ ባሻገር ሌሎች ቡድኖች መሳርያ ፈትተው ሲገቡ ኬንያ እንደነበር የሚነገርለት የኦነግ ጦር ክንፍ ከእነ መሳርያው እየታጀበ ገብቷል:: መንግስት ታጣቂ ኃይሎች መሳርያቸውን እንዲያወርዱ ባወጀበት ወቅት ኦነግ በይፋ መሳርያ ይዞ ሲንቀሳቀስ እንዲሁ ታልፏል:: ይህ የታጠቀ ኃይል ከቤንሻንጉል ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ የነበሩ የቤንሻንጉል ጉምዝ አመራሮች ላይ ባደረሰው ጥቃት ቤንሻንጉል የሚኖሩ 92 ሺህ በላይ አማራና ኦሮሞዎች ኦነግ ለፈፀመው የአጸፋ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል::

የኦነግ ታጣቂ ኃይል ኦሮሚያ፣ በተለይም በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች ላይ በደል ሲፈፅም ኦነግ ለምን መሳርያ አያወርድም የሚለው ሕዝብ ላይ ግርታ ፈጥሯል:: መንግስት ታጣቂ ኃይሎች መሳርያ ማውረድ አለባቸው ባለው መሰረት ይህ የመንግስት አቋምና ስምምነትን ለምን እንደማያከብሩ የተጠየቁት የኦነጉ መሪ ‹‹ማን ፈች፣ ማን አስፈች ይሆናል›› ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል:: ኦነግና ህወሓትን በማባበል ላይ የተጠመደው የጠ/ሚ/ር ዐቢይ መንግስትም ይህን የኦነግ ጠንካራ ምላሽ ሲሰሙ ‹‹የአፍ ወለምታ ይሆናል›› ሲሉ ለኦነጉ መሪ መግለጫ መሸፋፈኛ ሰጥተውላቸዋል:: ይህ የጠ/ሚ/ር ዐቢይ መንግስት ለኦነግ ያሳየው መለሳለስም የታጠቀው የኦነግ ኃይል የበለጠ አድማሱን እያሰፋ፣ የመንግስት ተቋማትን እየዘጋ፣ ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩት ሌሎች ሕዝቦች በተለይ አማራውን ቀረጥ እያስከፈለና እያፈናቀለ ቀጥሏል::

በተጨማሪም፣ የክልሉ መንግስት ተቋማትና ባለስልጣናትን ማጥቃቱንና በተለይ በክልሉ መንግስት ገዥ ፓርቲና ኦነግ መካከል የነበረው ፍትጊያ ሀገር ሊያፈርስ እንደሚችልም ራሱ መንግስት ያመነው ጉዳይ ሆኗል:: የመንግስት ተቋማት ተዘግተው፣ ዜጎች እየተሰቃዩ፣ የኦነግ ጦር በአንድ በኩል መከላከያ ሰራዊት በሌላ በኩል ጦርነት በገጠሙበት ወቅት እነ ዐቢይ በአንድ በኩል መግለጫ ሲሰጡ የኦነጉ መሪ ዳውድ ኢብሳ የኦነግን ጦር ወክሎ ከዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ሚዲያዎችን ሰብስቦ መግለጫ የሰጠበት መንገድ ሕዝብን ግር አሰኝቷል:: መሳርያ አወርዳለሁ ብሎ የገባው ኦነግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መሳርያ አወርዳለሁ ብሎ ገብቶ ከጦር ሰራዊቱ ጋር እየገጠመ ያለውን ኦነግን የሚያባብለው መንግስት ሁኔታ ሁለት መንግስት አለ ከማሰኘቱ ባሻገር የሀገር ሁኔታ ወደየት እያቀና ነው የሚለው አሳሳቢ መሆኑ የታየበት ነው::

ለውጡ ወዴት?

በማባበል ላይ ያተኮረው ኦዴፓ መራሹ መንግስት ከጀርባው ያሰለፈው የድሮውን ብአዴን፣ የአሁኑን አዴፓ እንዲሁም ከዚህም ከዛም የተሰባሰበው የ‹‹የአንድነት ኃይሉ››ን ነው:: እነዚህ ሁለት ኃይሎች ከህወሓት ጫና እና አገዛዝ ለመውጣት የራሳቸውን ጉዳይ ወደጎን ብለው ስለ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ሲያዘምሩ የሚውሉ ሆነዋል:: የህወሓት ተላላኪ የነበረው አዴፓ የኦህዴድ/ኦዴፓ ተላላኪ፣ እንዲሁም ብዙ መሞገት የነበረበት የአንድነት ኃይሉ የጠ/ሚ/ር ዐቢይ የድጋፍ ሰልፍ አስተባባሪና አዝማሪ እስኪመስል ስራውን ዘንግቶ የ‹‹ለውጡ›› ኃይል ላይ መለጠፉ የሁለቱ ተገንጣዮች ጥያቄ በሌላኛው የሀገሪቱ ፖለቲካ ሚዛን ላይ የተቀመጠ እንዲሆን አድርጓል::

በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ከፍተኛ ድፈቃ የደረሰበት የአንድነት ኃይሉ በጠ/ሚ/ር ዐቢይ በቃል ደረጃም ሆነ በአንዳንድ ጉዳዮች የሚታዩትን ትግበራዎች ለማስፋት አልቻለም:: በተጨማሪም፣ የአንድነት ኃይሉ ከመደፈቁም ባሻገር ከሌሎች አካላት ጋር ላይ ታች ሲል የአማራው ጥያቄ ለማንሳት ፍላጎት በማጣቱ ዋነኛ መንቀሳቀሻው እንዲያጣ ሆኗል:: በሁለቱ ተገንጣዮች ተፈርዶበት የነበረው አማራው በቅርቡ የራሱን ድርጅት አቋቁማል:: በተመሰረተ በወራት ውስጥ ፈጣን እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኝ የትኛውም የፖለቲካ ቡድን በተሻለ ህወሓትና ኦነግ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ሲያነሳ ይስተዋላል:: አብን፣ ህወሓት አይነኬ ይለው የነበረውን የወልቃይትና የራያን ጥያቄ በድፍረት በማንሳት ብአዴን/አዴፓ ተገድዶ እንዲይዘው ማድረግ ችሏል:: በተጨማሪም፣ ኦነግና ህወሓት በአማራው ላይ ያላቸውን ትርክትና የፈፀሙትን በደል ፊት ለፊት በመናገርም የአብንን ያህል የደፈረ የለም:: በሁለቱ ተገንጣይ ቡድኖች የተወጠሩት ጠ/ሚ/ር ዐቢይም ከሳምንታት በፊት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን አመራሮችን ቤተ መንግስት አስጠርተው ያነጋገሩት አብን ከአንድነት ኃይሉም ሆነ ከመንግስት በተሻለ ሁለቱን ተገንጣይ ኃይሎች ያለ ርህራሄ ስለሚተች ይመስላል::

የአንድነት ኃይሉ ‹‹የለውጡ ኃይል›› ሕዝብን እየሰበከበት ያለውን ኢትዮጵያዊነት ከአሁን ቀደም ያልተነገረና ያልደከመበት እስኪመስል በማጨብጨብ ላይ ብቻ ማተኮሩና ሕፀፆችን እንዳላየ ማለፉ የ‹‹ለውጥ ኃይሉ›› እና ከተገጣዮቹ ውጭ ያለው (በተለይም የአንድነት ኃይሉ) መካከል ያለው ረድፍ እንዲፋለስ አድርጓል:: መንግስት የቦዘነውን የአንድነት ኃይልና ከተገንጣዮቹ ውጭ ያለውን የፖለቲካ ኃይል በመዘንጋት የተገንጣዮቹን እሽቅድምድም በማባበል ለመግታት ያደረገው ጥረትም ሁለቱም በየፊናቸው ከመንግስት አሰራር ውጭ ሰራዊት እንዲያደራጁ እድል ሰጥቷቸዋል:: ህወሓት እስካሁን ባልተለመደ መልኩ የአካባቢውን ሚሊሻ ሳይቀር የመከላከያ ሰራዊቱ ክፍሎች የማይዙትን የቡድን መሳርያ ሲያስታጥቅ ቆይቷል:: መንግስት የሚወስናቸውን ውሳኔዎችና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመቃወም ባሻገር የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ እንዳይቀየር እንቀፋት ፈጥሯል:: የመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያለውን የበላነት ተጠቅሞ አሁንም ድረስ ክልሎቹን ሲያበጣብጥ የፌደራል መንግስቱ ይህ ነው የሚባል እርምጃ እየወሰደ አይደለም:: በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በኋላ የጥምቀት በዓል ማይጨው ላይ የተገኙት የትግራይ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደብረፅዮን መንግስት ላይ ጠንከር ያለ ትችት አቅርበዋል:: በሕገ መንግስቱና በትግራይ ላይ ያነጣጠረ ሴራ እንዳለ የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ሥልጣን ላይ ያሉ አካላት የትግራይን ሕዝብ ማንበርከክ ይፈልጋሉ ሲሉ ገልፀዋል:: በተመሳሳይ የሕወሓት ካድሬዎች ኢህአዴግ ያወጣውን መግለጫ ሕወሓት ያልተስማማበት መሆኑን ሲገልፁ ሰንብተዋል:: ባለስልጣናት ይፅፉባቸዋል በሚባሉ የፌስቡክ ገፆች ሳይቀር በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት ላይ ውርጅብኝ ሲወርድ ሰንብቷል:: ይህም በስብሰባው መጀመርያ ላይ ‹‹ለውጡን ይቀበላል›› ተብሎ የተጣለው ትንሽ ተስፋ መና ሆኖ በግልፅ ወደነበረው የ‹‹ፀረ ለውጥ›› አቋሙ ተመልሷል::

በተመሳሳይ፣ መሳርያ አወርዳለሁ ብሎ ተደራድሮ የገባው ኦነግ ‹‹አሁን ያለው የኢህአዴግና የኦነግ ጦር ነው›› የሚል መግለጫን በይፋ ሲሰጥ ከህወሓት ባሻገር ሁለት መንግስት፣ ሁለት የመንግስት ጦር እንዳለ አምኗል:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ የሚመራው መንግስት የሚያሳየው ከልክ ያለፈ ማባበል የፈጠራቸው ሁለቱን ኃይሎች ከተመለከትን ኢትዮጵያ ውስጥ ሶስት መንግስት መኖሩን መካድ አይቻልም:: አሁን ‹‹ለውጡን›› እየመራ ነው የሚባልለት ኦዴፓ እንዲሁም በአጋዥነት ላይ የሚገኘው አዴፓ ህወሓት የፈጠራቸው ድርጅቶች እንደመሆናቸው በሁለቱ ተገንጣይ ኃይሎች በንቀት የሚታዩ ናቸው:: በተመሳሳይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተስፋና በተመልካችነት ከማየት ውጭ ንቁ ተሳታፊ ያልሆነው የአንድነት ኃይል በሁለቱም ተገንጣይ ኃይሎች እንደጠላት የተቆጠረ ነው::

ተገንጣዮቹ ሁለቱንም ኃይል ያለፈውን ታሪካቸውን እየነቀሰ የሚያኮሰምን፣ ቀጣይ ጥሎ ማፋቸው ላይም እንቅፋት መሆኑን በማመን የቻሉትን ሁሉ ከማድረግ ውጭ የሚታረቅ አቋም ያራምዳሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል:: በተለይ፣ የጠ/ሚ/ር ዐቢይ መንግስት ርባና ያለውን የኢትዮጵያውያን ጥያቄ ሊያነሳ የሚችለው ኃይል በመቦዘኑ ምክንያት ይህን ተመልካች ኃይል ከኋላው ትቶ ወደ ተገንጣዮችም በማባበል ላይ ያተኮረበት ፖለቲካ ሁለቱን ተገንጣዮች ጥሎ ማለፉን እስኪያሸንፉ ድረስ፣ እንዲተባበሩ እድል የሚሰጥና ለጊዜው የተከፈተውን የፖለቲካ ምህዳር ተጠቅመው የጠ/ሚ/ር ዐቢይ መንግስት፣ በኦነግና ትህነግ እንዲወጠር ብሎም ወደሚፈራው ጦርነት የሚከት እንዳይሆን ያሰጋል::

ምንም እንኳ የኦነግ ተዋጊ ቅርንጫፍ ነበሩ የተባሉ ቡድኖች በእርቅ ወደካምፕ ገብተዋል ቢባልም በማባበል የፈረጠመው የኦነግ ኃይል ፖለቲካውን ለመረበሽ ትልቅ አቅም እንዳለው መካድ አይቻልም:: በሌላ በኩል የአማራን ክልል ለማበጣበጥ የተነሳው ህወሓት በርዕሰ መስተዳደሩ ደብረፅዮን በኩል ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጋር ታርቀናል ሲሉ በሚዲያ አስነግረዋል:: ይሁንና አሁንም ድረስ ህወሓት አለበት የሚባለው ግጭት እንደቀጠለ ነው:: የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት ኦነግ በጊዜያዊነት የሚያሳየውን አቋም ላይ እየተወሰነ በለስላሳነቱ ከቀጠለ፣ እንዲሁም አዴፓ በህወሓት መግዢያ የሚታለል መሆኑን ሲገመት የሁለቱ ተገንጣዮች ጠንቅ ቡግ እልም እያለ ‹‹ለውጡ›› ከሚባልለትና ከሚጠበቀው በተቃራኒ ሊመራው የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን መዘንጋት አይገባም::

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*