ኢትዮጵያ ወዴት?- ሲሳይ ታምራት (በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወቅታዊ የፖለቲካ አቋም በተመለከተ ሁለት ዓይነት አተያይ ያለ ይመስላል፡፡ የመጀመሪያው አተያይ ከቤተ መንግሥት አንስቶ እስከ ቀበሌ ድረስ በአክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ስለተጠለፈ ሁሉም ነገር ከጠቅላይ ሚነስትሩ ቁጥጥር ውጪ ሆኗል የሚል ሲሆን ሁለተኛው አተያይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ ላዩን የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ በመምሰል በተግባር ግን ከአክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ጋር በትብብር እየሠሩ ነው የሚል ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይን ከመጀሪያው አተያይ አንጻር ብንመዝናቸዉ ሊያደርጉት የሚገባዉ የአክራሪና ፍሽስታዊ ቡድኑን ተግባር (ለምሳሌ አዲስ አበባን በተመለከተና ሕግን በማስከበር ስም ኦዴፓ ሌሎች ብሔሮችን ከክልሉ ለማፅዳት የሚያደርግውን) በተመለከተ ግልጽ አቋማቸዉን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማሳወቅ ከአዴፓና ሌሎች ድርጅቶች ጋር ሆኖ ይህንን ፋሽስታዊ ተግባር በማክሸፍ ኢትዮጵያን መታደግ የሚል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሰውየው ከዚህ አንፃር እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን ስናይ፣ ዶ/ር ዐቢይ የጽንፈኛውን ወገን ደግፈዋል ወደሚለዉ አተያይ እንድንናዘነብል ይገፋናል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሁለተታ አተያይ አንፃር ሊከተሉት የሚችሉትን አካሄድ እንይ፡፡ ከዚህ አንጻር ዶ/ር ዐቢይ በበላይነት የሚዘውሩት ኦዴፓ በ“መደመር” ፍልስፍና ሌሎቹን ከማቀፍና አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ የትግል አጋሮቹን ሳይቀር ከጨዋታ ዉጪ እያደረጋቸዉ ይገኛል፡፡ ኦዴፓ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ጎትቶ ያስገባዉን አዴፓን በ“ጨዋታዉ ፈረሰ ዳቦዉ ተቆረሰ” ዓይነት የሕፃናት ጨዋታ ሕግ የአጨጫፋሪነት ሚና ብቻ እንዲጫወት የማድረጉ ሙከራ የዚህ አተያይ አንዱ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይባስ ብሎ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ተገፍትረው መቀሌ ላይ በመመሸግ በአማራ ሕዝብ ላይ የውክልና ጦርነት በመክፈት የሕዝቡን ሰቆቃ ያራዘሙትን ወንጀለኞች የዶ/ር ዐቢይ አሰተዳደር አይቶ እንዳላዩ ማለፍ እንዲሁ በድንገት የሆነ ሳይሆን የታሰበበት ይመስላል፡፡ እነ ጌታቸው አሰፋ እና ግብረ አበሮቹ ከመስከረም 16ቱ የመስቀል አደባባይ የቦምብ ጥቃት እስከ አማራ ክልል የውክልና ጦርነት በፊታዉራሪነት እየመሩት እንደሆነ እየታወቀ እነዚህን በንጹሐን ደም እጃቸዉ የተጨማለቀ ግለሰቦች ይዞ ለፍርድ አለማቅረብ የፖለቲካ ስትራቴጂ እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በየትኛዉም አገር ማንኛዉም መንግሥት ነኝ የሚል አካል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን መንግሥት ጨምሮ ተቀዳሚ ተግባሩ የሕዝብን ደህንነት እና ሰላም ማስከበር እንደመሆኑ ቀድመው የፈፀሙት ወንጀል አልበቃ ብሏቸው ዛሬም እንደትናንቱ ይህንኑ ተግባራቸውን አጠናክረዉ ሲቀጥሉ ዝም ብሎ ማየት ምን ይሉታል? ከዚህ አንፃር ዶ/ር ዐቢይ  ይህን አካሄድ እንዲከተሉ ገፋፍቷቸዋል የምላቸዉ አራት የቢሆን መላምቶችን ላስቀምጥ፡፡

አንደኛ ዋነኛ የኢትዮጵያ ጨቋኝ የነበሩትን ወንበዴወች ከመሃል አገር አባርሬ መቀሌ ዉስጥ እንዲመሽጉ አድርጌያለሁ በሚል ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት ስለሚያስችል፡፡ ትግራይ በቀል የነበሩትን የሜቴክ ወንጀለኞች ለፍርድ በማቅረብ ሌሎችን ወንጀለኞች በጉያቸዉ ውስጥ ሸሽገዉ “ፍትሕ አስፍነናል” ወይም “ፍትሕ ለማስፈን ቁርጠኞች ነን” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከራቸው ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሁለተኛ መቀሌ በሚገኘዉ በቅንጡዉ ፕላኔት ሆቴል አምስተኛ ፎቅ ላይ የመሸገዉ የእነ አቶ ጌታቸዉ አሰፋ ቡድን በቅርብ የሚዋሰነውን የአማራ ሕዝብ በውክልና ጦርነት ሰላም አልባ ለማድረግ ሌት ተቀን ሲሠራ እና አንዳንዴም ግልፅ የሆነ የጦርነት አዋጅ በደብረ ጽዮን በኩል ሲያስነግሩ የዐቢይ አሕመድ መንግሥት አይቶ እንዳላየ የሚያልፈው ሁለቱን የሰሜን መንግሥታትና ሕዝቦች እርስ ብርሳቸዉ በጊዜያዊ መቆራቆስ ራሳቸዉን በመጥመድ ከአራት ኪሎ የቤተ መንግሥት ፖለቲካ ገለል ማድረግ ስለሚቻል ይመስለኛል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የዐቢይ አስተዳደር ደስ ሲለው ከሕወሓት፣ ሲያሻው ደግሞ ከአዴፓ ጋር በመወገን ወይም እወግናለሁ በሚል ማስፈራሪያ በመጠቀም በሁለቱም ጎን እንደተሳለ (double-barrelled) ሰይፍ  በመሆን  ሁለቱ የክልል መንግሥታትን ለኦዴፓ ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ነዉ፡፡ በአራተኛ ደረጃ የማስቀምጠው የቢሆን እይታ ከሌሎች አንፃር ሲታይ የመከሰት ዕድሉ በጣም የጠበበ ይመስላል፡፡ ይህም የዶ/ር ዐቢይ ኦዴፓ አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞን ለማስደሰትና ለመምሰል ብሎም በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ በኦሮሞ ሕዝብ ተቀባይትን ለማግኘትና ለመመረጥ ያስችለኛል በማለት በአክራሪ የኦነግ ፖለቲከኞችና የሕወሓት መሪዎች ሲቀነቀን የነበረውን የአማራ “ጨቋኝነት” ትርክትን እንደገና በማስተጋባትና ጊዚያዊ የሆነ የፖለቲካ ጋብቻን በመፈፀም “ጨቋኝ” ያሉትን የአማራ ሕዝብ  ተባብረን እናጥቃዉ የሚለዉንም ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የዶ/ር ዐቢይ አስተዳደር በትግራይ ክልልና በአማራ ክልል እየታየ ያለውን አወንታዊ ያልሆነ ግንኙነት በዘላቂነት እንዲፈታና ፕላኔት ሆቴል የመሸጉት ወንጀለኞችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ፍላጎት የለውም የሚለዉን ነዉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ካለችበት መስቀለኛ መንገድ እና የጠቅላይ ሚንስትሩ አወዛጋቢ ሁኔታ ተነስተን ዶ/ር ዐቢይ የት ላይ ናቸው ብለን ለመፈለግ ብንሞክር በአክራሪዎች የፋሽስትነት አሰራር ተጠልፈው ወደ ካምፕ በመግባት የጀማሪ አክራሪነት ስልጠና እየወሰዱ ነዉ ወደሚለው ድምዳሜ እንድንደርስ እንገደዳልን፡፡

የሰላ ትችት በመስጠት የሚታወቀዉ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለዉን “ለውጥ” አምኖ ነገር ግን ከፊት ለፊት የተጋረጠባትን ችግር ሲገልፅ “ለውጡ እገደል አፋፍ የደረሰቸን አገር ከገደሉ ፈቀቅ ያደረገ ሳይሆን፣ ገደሉን ፊት ለፊት ከማየት ለገደሉ ጀርባን ሰጥቶ እዝያዉ የመቆም አይነት ነው፡፡ የአቋቋም እንጂ የቆምንበት ስፍራ ለዉጥ የለውም፡፡ ፊትን ያዞረ እንጂ እግርን ያራመደ ለዉጥ አልተመለከትንም” ነበር ያለው፡፡ በቴዎድሮስ እይታ ሙሉ በሙሉ ተስማምቼ ነገር ግን ለገደሉ ጀርባን ሰጥቶ መቆም ከገደል አፋፍ ፊትለፊት ከመቆም የባሰ አደገኛ መሆኑን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡  ምክንያቱም አንድ ጀርባውን ሰጥቶ ገደል አፋፍ ላይ የቆመ ሰዉ፣ ገደሉ በተለያዩ ምክንያቶች የመቦርቦር፣ የመሸርሸር ብሎም የመናድ አደጋ ገጠመዉ ብንል፣ ግለሰቡ ፊቱን አዙሮ በመቆሙ ይህንን አደጋ ቀድሞ ተመልክቶ በቶሎ እርምጃ ሊወስድ ወይም ሊሸሽ አይችልም፡፡ በተቃራኒዉ ይህ ሰዉ  ፊቱን ወደ ገደሉ አፋፍ ዙሮ የቆመ እንደሆነ፣ ከፊት ለፊቱ ያለዉን የገደል ሁናቴ መሸርሸር ወይም አለመሸርሸር፣ መናድ ወይም አለመናዱን አስቀድሞ ማየት ስለሚችል ወደ ኋላ ማፈግፈግ ወይም መሸሽ ይችላል፡፡

በመሆኑም አሁን ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ በምዕናብ እንጂ በተግባር መሬት ላይ ጠብ ያላለን “ለውጥ” ደጋግሞ ማስተጋባት እራስን ማታለልና የቁለቁለት መንገዱን ከማፋጠን ባለፈ ምንም አይነት ፋይዳ እንደሌለዉ ታዉቆ አፋጣኝ የሆነ እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል እላለሁ፡፡ ከላይ በተጠቀሰዉ ጽሑፋቸዉ “ለመሠረታዊ ለውጥ የበረታ ናፍቆት የነበረው በነ ዶ/ር ዐቢይ ያልታሰበ ዘወርዋራነት ተስፋ ወደ መቁረጥና ወደ ስጋት ተለወጠ፤ እምነት ተናወጠ፤” እንዳሉት ፕሮፌሰሩ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያለችበት ኹነት ሕዝቡ በመሪያቸው ላይ  ያለዉ እምነት በመሸርሸሩ እና ችግሬን ይፈታልኛል ብሎ ተስፋ ያደረገውም “ለውጥ” በአክራሪ ፖለቲከኞች አጀንዳ በመጠለፉ ኅብረተሰቡ ከፍርሃት ባሕር ውስጥ እየኖረ ስለሚገኝ የተረጋጋ ሕይወትን ለመምራትና ብሎም የወደፊቱን ሕይወት በተስፋ ለማየት ስለተቸገረ ወዳልተፈለገ ግርግርና ሽብር በቀላሉ ተጋላጭ ሆኖ እየኖረ ይገኛል፡፡ አንድ ሕዝብ ፍርሃት ዉስጥ ከተዘፈቀ መፍትሔ የሚያደርገው ከሌሎች በኀይል በልጦ መገኘትና ያጠቃኛል የሚለውን ወገን ቀድሞ በማጥቃት የራስን ፍላጎት ማስጠበቅን ትኩረት ያደርጋል እንዳለዉ እንግሊዛዊው ቶማስ ሆብስ የዚህ መፍትሔው ቶሎ ብሎ የተፈጠረውን የፍርሃት ድባብ በማጥፋት የሕግ የበላይነትን ማስፈን ይሆናል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ላለችበት መስቀለኛ መንገድ እና የጠቅላይ ሚንስትሩ አወዛጋቢ የፖለቲካ ቁመና መሰረታዊ ችግር የሚመነጨዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግልፅ የሆነ ፍኖተ ካርታ በማውጣት መርህን መሰረት ያደረገ አሠራርን ባለመከተላቸው ይመስልኛል፡፡ ጠቅላዩ አገሪቱ ልትመራበት የሚገባው ግልጽ የሆነ ፍኖተ-ካርታ ይኑራት እየተባለ ከተለያየ አቅጣጫ ግፊት ሲደረግ ሰምተዉ እንዳልሰሙ ሲያልፉትና በሌላ በኩል ሰውየው ሥልጣን ላይ ከመጡ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ትኩረት ያደረጉት በተለሳለሰ ንግግር የኢትዮያዊያንን ጆሮ ሲያደነቁሩ በተግባር ግን የአክራሪ ኦሮሞ ብሔርተኞች የስልጠና ካምፕ ዉስጥ ራሳቸዉን ያገኙት ይመስላል፡፡ በነገራችን ላይ ፍሽስታዊውና አክራሪዉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ቡድን ለኦዴፓ ያላቀበለዉ የፅንፈኝነት አስተሳሰብና ተግባር አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ አሁን ላይ የቀራቸው “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሔር ኦሮሞ ሆነው እያለ መቀመጫቸዉ ግን የምኒልክ ቤተ መንግሥት የሆነው የኦሮሞን ሕዝብ በመናቅ ነው፡፡ ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምኒልክ ቤተ መንግሥት ወጥተው አባ ገዳ አዳራሽ እንዲገቡ ኦዴፓና የኦሮሞ ሕዝብ ተግቶ ይሠራል፤” የሚል መግለጫ ማዉጣት ብቻ ነው፡፡

ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን ላይ እንደመጡ ዋና ሥራቸዉ ያደረጉት በተጠና መልኩ ቃላትን በመምረጥ ንግግራቸውን ማሳመር ላይ ማተኮር እንጂ ከተናገሩት መካከል ምን ያህሉ በተግባር ተፈፀመ ወይም አልተፈፀመም የሚለው አይደለም፡፡ በተጨማሪም ሰውየው መርህ አልባ መሆናቸዉ የሚናገሩት በተግባር ከሚሠሩት ጋር ሁሌም እንዲጣረስ አድርጎታል፡፡ መርህ አልባ መሆናቸው ሰውየውን ማንም እየተነሳ ወደሚፈልገዉ አቅጣጫ  እንደ ኳስ ስለሚጠልዛቸዉ ኑሯቸዉ በዥዋዥዌ የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በመርህ የማይመሩት ዶ/ር ዐቢይ ብዙዉን ጊዜ አንድ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በጥልቀት አስበዉ ዉሳኔ ከመወሰን ወይም መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ ጠዋት ተነስተዉ ይህንን ችግር ለመፍታት እንደዚህ የሚባል ኮሚቴ አቋቁመናል ይሉናል፡፡ በዚህ የተነሳ አገሪቱን በጥቂት ወራት ውስጥ ኮሚቴ በኮሚቴ አድርገዋታል፡፡ እስካሁን ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች ዉስጥ የትኛው ተግባር ላይ እንደገባ ለማንም ግልፅ አይደለም፡፡ በመሆኑም  ኮሚቴ ማቋቋም በራሱ ችግር ነዉ ለማለት ሳይሆን  ይልቁንም ቀድሞ የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ምንም ሥራ ሳይሠሩ ሌላ ኮሚቴ ማቋቋም የሰዉየዉን የመርህ-አልባነት ዋና ማሳይ ተደርጎ ይወሰዳል ለማለት እንጂ፡፡ “If I had an hour to solve a problem, I would spend fifty five minutes thinking about the problem and five minutes thinking about solutions” እንዳለው አልበርት አንስታይን ጠቅላዩ አሁን እየተጓዙበት ካለው የቁልቁለት መንገድ ራሳቸዉን ለመታደግ ከፈለጉ በደመ-ነፍስ አስበው ወደ ተግባር ከመግባታቸዉ በፊት ለሚወስኗቸው ውሳኔዎችና ለሚፈፅሟቸዉ ተግባራት ሰፊ ጌዜ ወስደው ማሰብና ማሰላሰል ያስፈልጋቸዋል፡፡

“አቦ ሸማኔ ፈጣን ሯጭ ነዉ ቢሉት አሳ አሙለጭላጭ እንስሳ ነዉ” ብሎ እንዳለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከፊቱ የተደቀኑትን መሰረታዊና አንገብጋቢ ችግሮች ይፈቱልኛል ብሎ ሲጠብቅ በተቃራኒ ጠቅላዩ አጀንዳ ቀይረዉ  ተራ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ተቸንክረዉ ይገኛሉ፡፡ ሲጀመር ብቃትና ችሎታን መሰረት ያደረገን ሹመት በመከተል ጠንከራና ተስፋ ሊጣልባቸዉ የሚችሉ ተቋማትን ይገነባሉ ተብሎ ሲጠበቅ በተቃራኒዉ ለባለፉት ሶስት አስርት አመታት በተለይም ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸዉ ሶስት አመታት ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ወጣት በዘመናዊ ስናይፐር መሳሪያ ደረትና ጭንቅላቱን እየተመታ ሲሞትለት የነበረዉ ጫላን በጫልቱ ወይም በለጠን በበለጡ ለመተካት በሚደረግ የፌሚንስት እንቅስቃሴ ወቅት ይመስል ከየቦታዉ ሴቶችን ለቃቅሞ ሀምሳ ፐርሰንት የካቢኒየን መቀመጫ ለሴቶች ሰጥቻለሁ ይልሃል፣ ገብረ መድህንን  በደቻሳ በመተካት “ርፎርም አድርጌአለሁ፤ ጠንካራ ተቋም ገንብቻሃለሁ፤ እኔም ተለዉጫለሁ” ይልሃል፡፡

ኢትዮጵያን የሚያስፈልጋት አንድ ግለሰብ ወይም  ድርጅት  በሌላ ግለሰብ ወይም  ድርጅት መተካካትን  ሳይሆን፣ ይልቁንም ግለሰብ ወይም ድረጅት ተቀየረም አልተቀየረም ጠንካራ የሆኑ ተቋማት ተፈጥረዉ የህዝብን ችግር በቋሚነት መፍታት መቻል አለመቻሉን ማረጋገጥ መሆን አለበት፡፡ እንደማሳያ ትናንት ህወሓት በበላይነት የሚዘዉረዉ የመከላከያ ሰራዊት ዛሬ ላይ በኦዴፓ ወርድና ቁመት ተጠፍጥፎ ተሰርቶ የኦዴፓን ስልጣን ለማራዘም ደፋ ቀና ከማለት ይልቅ፣ ከሁሉም ብሄረሰብ የተዉጣጣና አገሩን በሚገባ የሚወድ፣ በመልካም ስነ-ምግባር የታነፀ፣ ለአንድ ድርጅት ጤንነት እና እድሜ የሚጨነቅ ሳይሆን፣ ለአገር ደህንነትና ሰላም የሚሰራ ህዝባዊ የሆነ የአገር መከላካያ ሰራዊትን ለመገንባት መስራት ከአንድ ትክክለኛ ኢትዮጵያዊ መሪና ዜጋ የሚጠበቅ ነዉ፡፡

አሁን ላይ ዶ/ር አብይ በበላይነት የሚያሽከረክሩት ኦዴፓ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች ተጠቅሞ በተቃራኒዉ ደግሞ እየታዩ ያሉትን ተግዳሮቶች በጥንቃቄና በተጠና መልኩ በማለፍ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት መስቀለኛ መንገድ  በማዉጣት ማሸጋገር ቢችሉ ይህ ተግባር በደማቅ ቀለም ተፅፎ ሁሌም ሲታወስ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ የሴራ ፖለቲካን ተጠቅሞና በአክራሪ ፖለቲከኞች አጀንዳ ተጠልፎ ሌሎችን ጥሎ እራስን ብቻ ከስልጣን ማማ ለማዉጣት መሞከር ዉጤቱ “ከታሪክ የማይማሩ ክፉዉን ለመድገም ይገደዳሉ” (those who never learn from history are doomed to repeat it) እንዲሉ ወይም “ታላላቅ ኩነቶች ተከሰቱና ታናናሽ ሰዎች አስተናገዷቸዉ” (great moment has found little people) እንዳለዉ ጀርመናዊዉ ፍሬድሪክ ሼለር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይም ካለፈዉ ታሪካችን መማር ያልቻሉ እና በታሪክ አጋጣሚ ያገኙትን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉ ታናሽና እድለ-ቢስ መሪ ያደርጋቸዋል እላለሁ፡፡

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*