“የቆጠራው ግጭት ቀስቃሽ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው” – ዳዊት አወቀ

በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ሀገሮች በየዐሥር ዓመቱ አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራ (population census) ማካሄድ የተለመደ ነገር ነው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 103 ንዑስ አንቀጽ 5 “የሕዝብ ቆጠራ በየዐሥር ዓመቱ ይካሄዳል፤” ይላል። በዚህም መሠረት በዘመነ ወያኔ ሁለት ጊዜ፣ ማለትም በ1994 እና በ2007 – አጠቃላይ የሕዝብና ቤት ቆጠራ መካሄዱ ይታወሳል። በዘመነ አንድ ጊዜ በ1984 ተካሂዷል። አራተኛው አጠቃላይ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ደግሞ በመጭው ግንቦት፣ 2011 ዓ.ም. እንደሚካሄድ መንግሥት በቅርቡ አስታውቋል።

የሕዝብና ቤት ቆጠራ ብዙ ወጭ የሚያስወጣ ትልቅ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታወቃል። ለምሳሌ አሜሪካ በ2010 በተካሄደው የሕዝብ ቆጠራ 13 ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበታል። በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የኢትዮጵያ ሀገር ዐቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ 180 ሺሕ ታብሌቶች ከአንድ ዓመት በፊት እንደተገዛ፣ ከኀይል መቆራረጥ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይገጥማቸው ታስቦም በመጠባበቂያነት የሚያገለግሉ 126 ሺሕ ተንቀሳቃሽ የኀይል ማከማቻዎች እንደተገዛ፣ እንዲሁም 30 ሺሕ በፀሐይ ኀይል የሚሠሩ የባትሪ አቅም መሙያዎች ግዥ እንደተፈጸመ፣ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ እና የብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቢራቱ  ተናግረዋል። መንግሥታት ለምንድን ነው በጣም ብዙ ወጭ አውጥተው አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራ የሚያካሂዱት? የኢትዮጵያ መንግሥት ለምንድን ነው በየዐሥር ዓመቱ አጠቃላይ ሕዝብ ቆጠራ የሚያካሂደው? ጥቅሙ ምንድነው? የሚለውን ነገር መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ ሀገሮች አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራ የሚያካሂዱት በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እና ጥቅሞች ስላሉት ነው። አንዱና ዋነኛው የፖለቲካ ውክልና ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ኣንቀጽ 54 ንዑስ ኣንቀጽ 3” የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር የሕዝብ ብዛትንና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቁጥር መሠረት…” በማድረግ  እንደሆነ ይደነግጋል። ስለዚህ በእያንዳንዱ አካባቢ ያለውን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥርን ማወቅን ይጠይቃል።  (The whole system of representative democracy is based on population representation, and census is very important to ensure that each community gets the right number of representatives in government) እንደሚሉት ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያለው ክልል ብዙ የሕዝብ ተወካዮች ይኖሩታል ማለት ነው። ሁለተኛው የሕዝብ ቆጠራ ዓላማ ከኢኮኖሚ እና ፍትሐዊ የሆነ የሕዝብ ሀብት ክፍፍል ለማድረግ ከማሰብ ጋር የተያያዘ ነው። በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ከሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚገኙትን ስታቲስቲካዊ መረጃወች የሚያገኙዋቸውን ጥቅሞች ሲገልጽ 1) በክልሎች መካከል ለተመጣጠነና ለተስተካከለ የልማትና የዕድገት አቅድ ዝግጅት፣ 2) የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማጎልበት አስፈላጊ የሆኑትን የምርቶችና አገልግሎቶች ፍላጎት አቅርቦትን ስርጭት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመወሰን፣ 3) እንደ አስፈላጊነቱ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ለመስጠት እና የመሳሰሉትን ጥቅሞች እንዳሉት ይገልጻል።

የዛሬ ዐሥር ዓመት የተካሄደው ሀገራዊ የሕዝብ ቆጠራ እጅግ ኣወዛጋቢ ነበር፣ በተለይ የአማራው ቁጥር ከመጠን በላይ በመቀነሱ ምክንያት በወያኔ ፓርላማ ሳይቀር ተቃውሞ ተነስቶበት እንደነበር ይታወቃል።  በእኔ አስተያየት በዚህ ዓመት የሚካሄደው ቆጠራ ያለፈውን ሁኔታ ማረኝ የሚያስብል፣ ከድጡ ወደ ማጡ የሚከት ነገር ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ዘንድሮ በሚካሄደው የሕዝብ ቁጥር ከእስከዛሬው በተለየ የብሔር ምርጫ ላይ “ብሔራዊ ማንነቴን አልገልጽም” ብሎ መሙላት እንድሚቻል እየተነገረ ነው። የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ እና የብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቢራቱ ለቢቢሲ አማርኛ “ድብልቅ የብሔር ማንነት ያላቸውም ሆነ፣ የብሔር ማንነታቸውን መግለጽ የማይፈልጉ ሰዎች ይህንኑ ለቆጣሪያቸው ቢናገሩ፤ ቆጣሪያቸው የሚሞላው ወይንም የምትሞላው  ኮድ አለ” በለዋል። ከቀጣዩ ምርጫ አንድ ዓመት በፊት እንዲሁም በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች በተበራከቱበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ተንኮል እና ሴራ የማጋለጥ ግዴታ አለብን።

የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ አስተዳርደር ሁኔታ ብሔር የሁሉም መነሻ እና መድረሻ ነገር ነው። የሀገሪቱ ክልሎችም በመሠረታዊነት የተዋቀሩት በብሔር እንደሆነ ይታወቃል። ወደድነውም ጠላነውም ሁሉም የሀገሪቱ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ውሳኔ በብሔር ላይ የተመሠረተ ነው። በብሔር ላይ የተመሠረተውን የፖለቲካ መዋቅር መቃወም ይቻላል፣ ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ደሞ የመገንዘብ ግዴታ አለብን።

አንደኛው ልክ እንደነ ፈረንሳይ ዘር የሚል ጥያቄ  በሕዝብና ቤት ቆጠራ ቃለ መጠይቁ አለማስገባት ነው። በብዙ ሀገራት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሲደረግ የብሔር ወይም የዘር ማንነት አይጠየቅም። ለምሳሌ በፈረንሳይ ሀገር ሁሉም ዜጋ ፈረንሳዊ ነው ስለሚባለ በመንግሥት ደረጃ የፈረንሳይ መንግሥት የሕዝብ ቆጠራ ሲያካሂድ የዘር መረጃ ኣይሰበሰብም። እንደዚህ ዓይነት አሠራር በብዙ ሀገራትም የተለመደ ነው። በነዚህ ሀገራት የመንግሥት ፖሊሲ በኢኮኖሚውም ሆነ በማኅበራዊ ፖሊሲወች በዘር ስለማይወሰኑ በሕዝብ ቆጠራ ጊዜ የዘርን መረጃ መሰብሰብ ወይም አለመሰብሰብ ምንም ጥቅም ወይም ጉዳት የለውም።

ሁለተኛው፣ ብሔር የሚባለው ነገር በህዝብ ቆጠራ መግባት አለበት ከተባለ ደሞ ብሔሩን መሙላት መብት ሳይሆን ግዴታ መሆነ አለበት። ለምሳሌ ፎርም ሲሞላ ጾታየን አልሞላም እንደማይባለው ሁሉ የብሔር ማንነትን መግልጽ ግዴታ መሆን ኣለበት። ሀገሪቱ ባለችበት ነባራዊ ፖለቲካ ሁናቴ የብሔር መረጃ እጅግ በጣም መሠረታዊ መረጃ (vital statistics) ነው። በአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ አስተዳርደር  (ሀ) ብሔር የሁሉም መነሻ እና መድረሻ በሆነበት ሀገር፣ (ለ)  ክልሎችም በመሰረታዊነት የተዋቀሩት በብሔር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ (ሐ) የሀገሪቱ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ውሳኔ በብሄር ላይ የተመሠረተ በሆነበት ሀገር፣ ይህ የብሔር መረጃ እጅግ በጣም መሠረታዊ መረጃ (vital statistics) በመሆኑ፣ መሰብሰብ ካለበት በጥራት ሁሉም አካባቢ መረጃው መሰብሰብ አለበት እንጅ አንድን ማህበረሰብ እንደሚጎዳ እየታወቀ እንደ ባጣ ቆየኝ ከፈለግህ ሙላው ካልፈለግህ አትሙላው ተብሎ መተው የለበትም። ይህን የምንለው በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ክስረቶችን ስለሚያስከትል ነው።

ፖለቲካዊ አንድምታው

በመጀመሪያ ፖለቲካው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ኪሳራ እንመልከት። ለምሳሌ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የተወካዮች ምክር ቤት ኣባላት ቁጥር ያክል 548 ነው፣ ከነዚህም ውስጥ ከኦሮሚያ 178፣ ከአማራ 138፣ ከደቡብ 123 እና ከትግራይ 38 ተወካዮችን የያዘ ነው። ይህም የተወካዮች ምክር ቤት ክፍፍል የተወሰነው መንግሥት ባካሄደው አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ላይ መሠረተ በማድረግ ነው። የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እንድሚለው አጠቃላይ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከ550 መብለጥ የለበትም፣ ነገር ግን የአማራ ሕዝብ የሚያገኘው ውክልና ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል፤ እንደ አጠቃላይ ሕዝብ ቆጠራው ውጤት መሠረት አድርጎ። ለምሳሌ በመጪው በሚካሄደው አጠቃላይ ሕዝብና ቤት ቆጠራ የኦሮሞ ሕዝብ ብዛት ከጨመረ እና የኣማራ ሕዝብ ከቀነሰ የኦሮሞ የተወካዮች ምክር ቤት ከኣማራ ተቀንሶ ለኦሮሞ ይጨምራቸዋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ መሠረት አጠቃላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቁጥር ከ550 መብለጥ ስለማይችል፣ ካንዱ ቀንሶ ወደሌላ ሽግሽግ ነው የሚደረግ።

ይህ አሠራር አሜሪካም ላይ የተለመደ ነው። ለምሳሌ በኣሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኣጠቃላይ 538 electors አሉት (The Electoral College consists of 538 electors)፣ ሕዝብ ቁጥር ጨመረም አልጨመረም ኣይቀንስም ኣይጨምርም። እነዚህ electors ከእያንዳንዱ እስቴት በሕዝብ ቁጥር መሠረት ተደርጎ የተከፋፈለ ነው። ለምሳሌ ሮናልድ ሬገን በ1980 ፕሬዚዳንት ሆኖ ሲመረጥ ነው ኒውዮርክ 41 መራጮች (electors) ሲኖሯት፣ ቴክሳስ 26፣ fastforward በ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የቴክሳስ የሕዝብ ቁጥር ሸር በመጨመሩ፣ የኒውዮርክ የሕዝብ ቁጥር ሸሩ ስለቀነሰ፣ ከ538 መራጮች (electors) ወስጥ የቴክሳስ ወደ 38 ሲጨምር፣ የኒውዮርክ ደሞ ወደ 29 ቀንሷል፣ ምክንያቱም 538 electors በሕዝብ ቁጥር መሠረት አድርጎ ካንዱ ቀንሶ ወደሌላ ሽግሽግ እንጅ መጨመር ስለማይቻል።

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*