የታሪክ ፍጥጫው እንዴት ይቋጭ? – ሰሎሞን ኀይሉ

ከሁለት ሳምንት በፊት ከወደ ትምህርት ሚኒስቴር አንድ አስደንጋጭ ወሬ አፈትልኮ ወጣ፡፡ ይህ ወሬ ለሰባት ዓመት የተደከመበት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች መማሪያ የሚያገለግል የታሪክ መጽሐፍ እንዲሰረዝ የሚያዝ ነበር፡፡ የውሳኔውን የወዲያው ምክንያት ውሳኔውን ካሳለፉት የፖለቲካ ሹመኞች በስተቀር በውል ባናውቀውም  የጉዳዮ ስረ-ምክንያት  ግን የታሪክ ፍጥጫችን ካለመቋጨቱ ጋር የሚያያዝ ስለመሆኑ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ እንደአገር በታሪካችን ሐዲድ ላይ የጋራ ተግባቦት የለንም፡፡ የትምህርት ሥርዓታችንን መካን ያደረገው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነቱ እንደሆነው ሁሉ ለታሪካችን ፍጥጫ እና መካረር የፖለቲካው ቅጥ ያጣ ጣልቃ ገብነት ስለመሆኑ የሚያከራክር አይመስልም፡፡ በለኮሰው እሳት መልሶ እየተለበለበ ያለው የኢሕአዴግ አገዛዝ ከታሪክ ብያኔ አንጻር እንደ ሀገር ያመጣብን ብሔራዊ ኪሳራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የጽሑፌ ተጠየቅም በዚሁ አግባብ የተቃኘ ሆኖ ስለ ታሪካችንና የታሪክ ምንጮቻችን አስተያየት ለመሰንዘር ወድጃለሁ፡፡ አስተያየቴ በአመዛኙ ከኦሮሞ የታሪክ ምንጮች እና የታሪክ አቀራረብ ጋር ይያያዛሉ፡፡

እኛና ነገረ-ታሪካችን …

በኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ላይ ብዙ ልዩነቶች ይስተዋላሉ፡፡ ከልዩነቶቹ ሥረ- ምክንያት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የሥርዓታቱን (ኢትዮጵያን ከዚህ ቀደም ያስተዳደሩ ገዥዎችን) ሥርዓታዊ ባሕሪ መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የኢትዮጵያን የቀደመ ታሪክ የሚቃኙ የተለያዩ ኀይለ-ሐሳቦች እንዲንጸባረቁ ግድ ብሏል፡፡ የታሪክ ትንቅንቁ በ”አጥቂነት” እና “ተከላካይነት” የሚበየን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ አተራረክ ዙሪያ “ፍልስት”፣ “መስፋፋት”፣ “ብሔራዊ ጭቆና”፣ “ቅኝ ግዛት”፣ … መሰል ቃላት ላለፉት ሐምሳ ዓመታት፣ በተለየ መልኩ ደግሞ በድኀረ -ደርግ  ጊዜያት የታሪከ ሙግት አጀንዳ አስቀማጭ ቃላት ሆነዋል፡፡

ባሳለፍናቸው ሦስት ዐሥርት ዓመታት ጉዟችን፣ የታሪክ ጉዳይ እጅግ አብሰልሳይ እና ውርክብ የበዛበት ሊሆን የቻለው፣ አገዛዙ ለኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ በጎ እይታ የሌለው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ሥርዓቱ ሀገራዊ የጋራ ማንነቶችን ከማሳደግ እና ከማበልጸግ ይልቅ ልዩነትን በመስበክ የተጠመደ በመሆኑ ለወል ትውስታና ለብሔራዊ ማንነት ግንባታ መዋል የሚችሉት እንደ ዐድዋ ያሉ ወታደራዊ የድል በዓላት አከራካሪ ሆነው እንዲታዩ አድርጓል፡፡ የአንድ ዘውግ ታሪክ ተነጥሎ ሲጻፍ፣ ታሪኩ ከፖለቲካ እና የባህል ጥቅም ጋር ተያይዞ እንዲቀርብ በመደረጉ የታሪክ አጻጻፉ በሀገር ደረጃ ማኅበራዊ ማንነት እና አንድነትን ከመገንባት ይልቅ ልዩነትን፣ ብሎም የተበዳይነትንና የተጠቂነትን ስሜት የሚያሸክም አቀራረብ ይታይበታል፡፡ የታሪክ ቁጭት ፈጠራው በስሜት ለሚናጠው የዘውግ ፖለቲካ ግብዓት በመሆን፣ ለልሂቃኑ የሥልጣን መወጣጫ እርካብ ሆኖ ሲያገለግላቸው ቢታይም ለብዙሃኑ የአብሮነት ጠንቅ በመሆኑ ብሔራዊ ኪሳራው አመዝኗል፡፡

በዚህ የተነሳ የታሪክ ነክ ሙግቶቻችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከምሁራዊ ስብዕና በወረደ ሁኔታ ዱላ ቀረሽ የዘለፋ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ የጉዳዩ አሳሳቢነት የሳይንሳዊ ዕውቀት ምንጭ ይሆናሉ ተብሎ በሚታንባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን የመፍትሔ አካል ከመሆን ይልቅ የችግሩ ምንጭ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ በየጥናት መድረኮች፣ አፈ ታሪክን እንደ ብቸኛ የታሪክ ምንጭ ወስደው ለሚጽፉ የዘውግ ታሪክ ደራሲያን የሚሰጡት የአደባባይ ምስክርነት፤ ከምሁራዊ ተልዕኮ ይልቅ ለፖለቲካዊ ግቡ ያደላ ሆኖ ይገኛል፡፡ “ታሪክ እና ፖለቲካ ሲላቀሉ ትምህርት ይመክናል፤” የሚለው አባባል እውነታነትም ከዚህ መሠረታዊ ችግር ይመነጫል፡፡

በኢትዮጵያ የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፈር ቀዳጅ ከሆኑ ምሁራን አንዱ የሆነው ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከታሪክ አጻጻፍ ጋር በተያያዘ ይህን ብሎ ነበር፡፡ “ታሪክን መማር ለሁሉ ይበጃል ለቤተ መንግሥት መኮንን ግን የግድ ያስፈልገዋል፡፡ የድሮ ሰዎች ስህተትና በጎነትን አይቶ ለመንግሥቱና ላገሩ የሚበጀውን ነገር ያውቅ ዘንድ የታሪክ ትምህርት ግን የሚጠቅም የእውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲሆን ነው፡፡ እውነተኛውንም ታሪክ ለመፃፍ ቀላል ነገር  አይደለም፡፡ የሚከተሉትን ሦስት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ያስፈልጋልና፡፡ መጀመሪያ ተመልካች ልቡና፣ የተደረገውን ለማስተዋል፤ ሁለተኛ የማያዳላ አእምሮ፣ በተደረገው ለመፍረድ፤ ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ” (የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣ 2002 ዓ.ም.) ገብረ ሕይወት ልክ ነበር፡፡ የገብረ ሕይወት ምክረ-ሐሳብ የሚሰራው ግን ታሪክ የፖለቲካ እስረኛ መሆን ስታቆም ነው፡፡

ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ “Pioneers of change in Ethiopia, the Reformist Intellectuals of the Early 20th Century” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ከላይ የተመለከትነውን የገብረሕይወትን ሂሳዊ ምክረ – ሐሳብ  ከቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ አኳያ ተመልክተውታል፡፡ ፕሮፌሰር ባሕሩ፣ የገብረ ሕይወት ሂሳዊ ምልከታ የቤተ መንግሥት እና ቤተ ክርስቲያን ተቀጣሪ የዜና መዋዕል (chronicle)  ዘጋቢዎችን  እንደሚያመለክት ይገልፃሉ፡፡  በሰለሞናዊው የንጉሣዊ ሥርዓት  ውስጥ የታሪክ አዘጋገብ፣ በንጉሡ እና በዙሪያው ካሉ ባለሟሎች/መሳፍንታት ዕለታዊ ክንዋኔ፣ የጦርነት ውሎዎች፣ ምርኮ እና ግዳይ፣ ወዘተ ጋር የተያያዙ ኩነቶች ተመርጠው እንደሚጻፉ ቀደምት ድርሰናት ያመላክታሉ፡፡ እንደ እውነቱ ግን ተግባራቸው በፖለቲካ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ወደ ጎን  ለማድረግ ያለፈውን ጊዜ ከንጉሣዊ ሥርዓት ውግንና በፀዳ መልኩ (dispassiontate) መልሶ መገንባት (reconstruct) እና መተርጎም ነበረባቸው የሚሉ ትችቶች ጎላ ብለው ይደመጣሉ፡፡

በዚህ ረገድ በአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ተጽፎ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ለሕትመት የበቃው “ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ” የተሰኘው መጽሐፍ አቀራረቡ በፖለቲካ ውግንና ትችት ውስጥ ይወድቃል የሚሉ አስተያቶች ተሰንዝረውበታል፡፡ በተለይም ትግሬዎችን እንደ ሕዝብ ለመግለጽ የተጠቀመባቸው ቃላት “ኢትዮጵያዊ ጨዋነት” የሚጎድላቸው ነበሩ፡፡

“አወዛጋቢው የጥበብ ሰው” በመባል የሚጠራው አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ከቤተ መንግሥት ቅጥር ጸሐፊያን የተሻለ ትምህርት በአውሮፓ (ጣሊንያ፣ 1987) ያገኘ ቢሆንም፣ የታሪክ ዘገባዎቹ ውግንና ይታይባቸዋል፡፡ በጸሐፊው  የሕይወት ጉዞ ላይ ፖለቲካዊ የአቋም መገላበጥ የበዛበት በመሆኑ የታሪክ ዘገባዎቹ ላይ ጥርጣሬ እና ትችት አዘል  ጥያቄዎች ያለማባራት መነሳታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከዚህ  በተቃራኒው ጽንፍ ደግሞ የአፈወርቅ ደጋፊዎች “የዘመኑን አስተሳሰብ እና አጠቃላይ ገጽታ ግልጽነት በተሞላበት መልኩ በጽሑፍ ትቶልን ሂዷል፤” በሚል ጥብቅና ሲቆሙለት ይታያል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ በአንድ ጎን ጉንተላና ዘለፋ በሌላ ገጽ ደግሞ ውዳሴና ለዘብተኛ ሂስ የታየበት የአፈወርቅ አወዛጋቢ የታሪክ አቀራረብ ዛሬ ላይ ለደረስንበት የታሪክ ውዝግባችን ድንጋይ አቀባይ መሆኑን ማስተባበል የሚቻል አይመስልም፡፡

ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከላይ በተጠቀሰ ሥራው የቤተ መንግሥት የታሪክ ዘጋቢዎችን ሥራ “የሰይጣን ወይም እግዚአብሔር ፈቃድ ለድርጊቶቻቸው ለማልበስ የሚፈልጉ ሰዎች” በሚል ይገልጻቸዋል፡፡ የአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ሥራም ከዚህ ምድብ የሚገኝ ይመስላል፡፡ ቤንስ በአቀራረብ ደረጃ፡፡

እዚህ ላይ መታወስ ያለበት አንድ መሠረታዊ ነጥብ አለ፡፡ እንደ አፈወርቅ ዘለግ ያለ የምዕራቡን ዓለም ትምህርት ያልቀሰሙ ቢሆንም ሌሎች ሕዝባዊ የታሪክ ጸሐፊያን እርስ በርሳቸው ሲተቻቹ ነበር፡፡ በተለይም ከኢትዮጵያ የታሪክ አዘጋገብ ጋር በተያያዘ ትችት በማቅረብ አለቃ አፅመ ጊዮርጊስ ይታወሳሉ፡፡ አፅሜ፣ የቤተ-መንግሥት የታሪክ ጸሐፊያንን ሲተቹ “ትኩረታቸው በንጉሡ ጀግንነት ላይ እንጅ በታሪክ ሁነቶች ላይ እንዳልሆነ” በመግለጽ ነው፡፡ በሌላኛው የታሪክ አዘጋገብ ትችታቸው ላይ ደግሞ የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኦሮሞን ሕዝብ ፍልሰት በተመለከተ የተሰናዳውን ብቸኛ የታሪክ ምንጭ ይተቻሉ፡፡

የኦሮሞ ታሪክ ምንጭ እና ፖለቲካዊ አንድምታዎቹን በጨረፍታ

አቀባበሉ ላይ የሐሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም፣ የኦሮሞን  ታሪክ በተመለከተ ቀዳሚ የጽሑፍ ሰነድ ሆኖ የሚጠቀሰው የአባ ባሕርይ ሥራ ነው፡፡ ጥልቅ አሳቢ በነበሩት አባ ባሕርይ የተጻፈው “ዜናሁ ለጋላ” (“የጋላ ታሪክ”) በዓለቃ አፅሜ እይታ ተቀባይነት የለውም፡፡ ራሳቸው  አለቃ አፅሜ “የጋላ ታሪክ” ሲሉ በሰየሙት መጽሐፍ ውስጥ “የተመዘገበ ሰነድ ባለመኖሩ፣ እንዲሁም የተመዘገቡትም ቢሆኑ ከኦሮሞ ባህል ጋር የማይሄዱ በመሆናቸው፣ የኦሮሞን ታሪክ ከባዶ ለመጀመር” ማቀዳቸውን ጽፈዋል፡፡

ለዚህም ይመስላል፣ ብዙዎቹ የኦሮሞ የታሪክ ምሁራን አለቃ አፅሜን በታሪክ አዘጋገባቸው ሲያመሰግኑ በአንጻሩ አባ ባሕርይን “የጥላቻ መሠረተ ሐሳብ አመንጭ” በማለት ሲተቹ የሚታዩት፡፡ እ.ኤ.አ. በ1593 እንደተጻፈ የሚነገርለት የአባ ባሕርይ ሥራ ስለኦሮሞ ታሪክ ቀዳሚ የጽሑፍ ማስረጃ በመሆኑ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር የታሪክ ጸሐፊዎች በዋቢነት ሲጠቀሙበት ኑረዋል፡፡ የነገሩ ምፀት እንደ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ያሉ የኦሮሞ የታሪክ ልሂቃን ለአባ ባሕርይ ታሪካዊ ሰነድ ምስጋናቸውን በአደባባይ ማቅረባቸው ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ Horn of Africa በተሰኘው ጥናታዊ መጽሔት (ጆርናል) ላይ የአባ ባሕርይ ትረካ ለኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ ያለውን ጥቅም ሲያስረዱ ‹‹Bahrey’s greatest contribution to our knowledge of Oromo history is his impressive presentation of Oromo migrations which are conveyed through many chapters which use the framework of the eight year Gada period›› (የአባ ባሕርይ ዋናው ለኦሮሞ ታሪክ ያደረጉት አስተዋጽዖ የሕዝቡን እንቅስቃሴ እና የገዳ ሥርዓቱን ሁኔታ በተለያየ ምዕራፍ በመግለጻቸው ነው) በማለት የአባ ባሕርይ መጽሐፍ የመጀመሪያው የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ የታሪክ ሰነድ እንደሆነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ፕሮፌሰሩ  “The oromo of Ethiopia; A History 1570-1860” (1990) የሚለውን መጽሐፋቸውን ሲያዘጋጁ፣ የአባ ባሕርይን መጽሐፍ በዋቢነት ደጋግመው ተጠቅመዋል፡፡ በአንጻሩ በአለቃ አፅሜ የተዘጋጀውን ሥራ እምብዛም አልተጠቀሙበትም፡፡ በታዋቂው የኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊ ፕ/ር መሐመድ ሐሰን አረዳድ፣ የአባ ባሕርይ ታሪካዊ ሰነድ ከአለቃ አፅሜ መጽሐፍ በተሻለ ሁኔታ ስለ ኦሮሞ ታሪክ የሚናገረው ቁም ነገር አለው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር አጽኖት ሰጥቶ ማለፍ ተገቢ ነው፡፡ በመካከለኛው የኢትዮጵያ ዘመንም ሆነ፤ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ባሉ ጊዜያት የኦሮሞ የታሪክ አዘጋገብ (በኦሮሞ ልሂቃን ዘንድ የሚዘጋጁ የታሪክ ድርሳናት) ምንጫቸው ተረት እና አፈ ታሪክ ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ ይታያል፡፡

የኦሮሞ የታሪክ አጥኝዎች የጋራ መከራከሪያ “የኢትዮጵያ የታሪክ ምንጭ የሚባሉት ለቤተ  መንግሥት ወገናዊ//ነትን በሚያሳይ መልኩ የተጻፉ በመሆናቸው የኦሮሞን ታሪክ አዛብተውታል” የሚል ሆኖ እናገኘዋን፡፡ ሌላው ቀርቶ የየጁ ኦሮሞዎች በጎንደር ቤተ መንግሥት የንግሥና ተጋሪ ሆነው በነበሩበት ወቅት የነበራቸውን የታሪክ አሻራ ዘገባዎች ከነባሩ የኢትዮጵያ ታሪክ ምንጭ ወስዶ/ጠቅሶ ለመጠቀም ውስንነት ይታይባቸዋል፡፡ ልሂቃኑ መፍትሄ ያሉት አማራጭ የኦሮሞን ተረቶች እና አፈ- ታሪኮች እንደ “ታሪክ ምንጭነት” መጠቀም ነው፡፡ ይሁንና አስተማማኝ መረጃ የማይገኝለት ነገር ሁሉ “ታሪክ” ሊጻፍለት እንደማይችል ፕሮፌሽናል የታሪክ ባለሙያዎች አጥብቀው ይመክራሉ፡፡ በፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት አንደበት “ታሪክ በእምነት አይጻፍም”፡፡ ቀደም ሲል በነበሩ ጊዜያት የጽሕፈት ባህል ባልዳበረባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በጽሑፍ ከቆዩት የታሪክ ምንጮች ይልቅ በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተረቶች እና አፈ ታሪኮች ጎላ ያለ ቦታ ይዘው ይታያሉ፡፡ የኦሮሞ የታሪክ አዘጋገብም ከዚህ ጋር የተገናኘ ሆኖ ይታያል፡፡

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “History of the Sayyoo Oromo of Southwestern Wallaga, Ethiopia from about 1730 to 1886” (1984) በሚል ርዕስ ለሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ በሰሩት ጥናት፣ የተለመደውን የኢትዮጵያ ታሪክ አዘጋገብ ተሻግረውታል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በአዲሱ አተያያቸው በተለምዶ ‹የኦሮሞ ሕዝብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ መካከለኛው የኢትዮጵያ  ግዛት ፈልሶ ገብቷል› የሚለውን ትርክት (narrative) ውድቅ በማድረግ፤ ኦሮሞ ላለፉት አንድ ሺሕ ዓመታት በመሃል ኢትዮጵያ የቆየ መሆኑን ይከራከራሉ፡፡ ነጋሶ ከላይ በተጠቀሰ የጥናት ውጤታቸው በነገሥታት እና በአፄዎቹ ላይ ከማተኮር ይልቅ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ የተዘነጉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ለማተኮር ሞክረዋል፡፡ ለዚህ መሰሉ አቀራረብ የአጥኝው መከራከሪያ “የሰፊው ሕዝብ ታሪክ ሲጻፍ አለማየታቸው” እንደሆነ በተለያዩ መድረኮች ሲገልጹ ታይቷል፡፡ የነጋሶ የታሪክ ምንጭ ሆነው የቀረቡት የደቡብ ምዕራብ ወለጋ የኦሮሞ ተረቶች እና አፈ ታሪኮች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ በረጅሙ የሀገሪቱ ታሪክና የጊዜ ዑደት ውስጥ ተረቶችም ሆኑ አፈ ታሪኮች በአተረጓጎም እና በአቀራረብ ደረጃ የሚፈጠሩባቸውን ልዩነቶች (መቀየጥና መዛባት) ተከትሎ የታሪክ ዘገባው ላይ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የዶ/ር ነጋሶ የጥናት ውጤት ላይ ከታሪክ ምንጭነት አኳያ የተገቢነት ጥያቄ መነሳቱ የሚጠበቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ካላት ሰፊና የተወሳሰበ ታሪክ እና የማንነት ስብጥር አኳያ የብዙሃን-ዕይታን የታሪክ አረዳድ እንደ መሪ የታሪክ ማስተማሪያ ዘዴ መጠቀም አማራጭ የሌለው አስቻይ የመፍትሔ መንገድ መሆኑን አስምረንበት እናልፋለን፡፡ ይሁንና ከታሪክ ምንጭ አጠቃቀም፣ አተረጓጎም እና አቀራረብ አኳያ ጥንቃቄ ሊለየው የማይገባ ስለመሆኑ የታሪክ ምሁራኑ ይመክራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ትልልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ምሁራን መካከል ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት እና ፐሮፌሰር ሥርገው ኀብለ ሥላሴ ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህ የታሪክ ሊቃውንት የኢትዮጵያ ታሪክ ከልማዳዊው ተረት ቀመስ አጻጻፍ ወጥቶ በአዲስ መልክ ሁሉንም የኢትዮጵያ ክፍል ባቀፈ መልኩ እንዲጻፍ ሰፊ ጥረት ስለማድረጋቸው የሁለቱም ሊቃውንት የታሪክ ሥራዎች ህያው ምስክር ናቸው፡፡ በነዚህ ምሁራን ተዘጋጅተው፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከበሩ የታሪክ ሰነዶችን “ተረት ብቻ ናቸው” እያሉ የሚያጥላሉ አንዳንድ የኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊዎች የእነርሱን የታሪክ ሥራ ከኦሮሞ ተረቶች እና አፈ-ታሪኮች ጋር አዛምደው እንደሚፅፉ ሲነግሩን ከኩራት ጭምር ጋር ነው፡፡

የአርሲ ኦሮሞ የሆኑት ፕሮፌሰርር አባስ ሐጂ ገናሞ “The History of Arsi, 1880-1935”  በሚል ርዕስ በሰሩት የመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ ጥናታቸው ላይ፤ በራስ ዳርጌ የተመራው የዐፄ ምኒልክ ጦር አርሲ ላይ “የሴቶችን የቀኝ ጡት ቆርጧል” በሚል ይገልጻሉ፡፡ አባስ ሐጂ ይህን ጥናት ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት ሲሠሩ አንድም የታሪክ ሰነድ በዋቢ ማስረጃነት አላካተቱም፡፡ ይልቁንስ ተረተቶችን እና አፈ-ታሪኮችን እንደዋነኛ የታሪክ ምንጭ አጉልቶ ለማውጣት በጥናታቸው ላይ ሲደክሙ ይታያል፡፡ በታሪክ ሙያ መስፈርቶች ተቀባይት የሚኖረው ታሪካዊ ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ የአባስ ሐጂ ገናሞ ተረት እና አፈ-ታሪክ ላይ የቆመ የ‹ታሪክ ጥናት›፣ ጥናቱ ከተሠራ ከሠላሳ አምስት ዓመት በኋላ ፖለቲካዊ ድጋፍ አግኝቶ በሕወሓት የበጀት ድጋፍ ‹አኖሌ› የተሰኘው ሐውልት ሊቆም ችሏል፡፡ ታሪክ እና ፖለቲካ ሲቀላቀል እውነተኛ የታሪክ ምዕራፎች እየተፋቁ፣ የሕዝቦች የዘመናት መስተጋብር እየተካደ፣… ሐሳዊ ፕሮፖርጋንዳ እንዲነግሥ ያደርጋል፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት መትክላዊ የጥላቻ ርዕዮት ሐውልቶችን አዋልዷል፡፡ “አኖሌም” ሆነ “ጨለንቆ”፤ በታሪክ እና ፖለቲካ መቀላቀል የተፈጠሩ የአብሮነት ጠንቆች ናቸው፡፡

ከታሪክ ምንጭ መዛባት እና ከፖለቲካዊ ፍላጎት አኳያ ሌላ ተጨማሪ ምሳሌ እንመልከት፡፡ ከብዙዎቹ የኦሮሞ ታሪክ ጸሐፊያን ‹የተሻለ አቅራረብ› አላቸው የሚባልላቸው ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን፣ በአንድ በኩል ኦሮሞነትን ከእስልምና ነጥሎ ለማየት ሲቸገሩ ይታያል፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሞን የጥንተ-ሀገሪቱ ባለቤት መሆኑን ለማስረገጥ የኦሮሞን ተረቶች እና አፈ-ታሪኮች እንደዋነኛ የታሪክ ምንጭ ሲወስዱ ይታያል፡፡ “The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia: 1300-1700” በሚለው መጽሐፋቸው ከላይ የተመለከቱትን ጭብጦች በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ እንደ ገዥ- ሐሳብ እንዲታዩ ሲተጉ ይስተዋላል፡፡ የዚህ ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም አካሄድ የብዝሃ – እይታን የታሪክ አረዳድ ለመፍጠር ያለመ ቢመስልም፣ አቀራረቡ የኢትዮጵያ የታሪክ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉትን የጽሑፍ እና የቅርጻ ቅርጽ መረጃዎችን ለማምከን ያለመ ያስመስለዋል፡፡

በመሠረቱ ከሆነ ‹የኢትዮጵያ ነባር የታሪክ ምንጮች ምልዑ› ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ይሁንና በታሪክ ሙያ መስፈርት ቀላል የማይባል ዋጋ ያላቸው ስለመሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈች አገር እንደመሆኗ መጠን የታሪክ ምንጮቻችን ከዘመን ዘመን የተለያዩ ሆነው ይታያሉ፡፡ ለአብነት… ቅድመ አክሱምም ሆነ ከፊሉ የአክሱም ዘመን ሥልጣኔ አሻራዎች የድንጋይ ቅርጻ ቅርጾች፣ ሐውልቶች፣ የተቀረጹ ፊደላት፣… ከመሆን የተሻገረ የጽሑፍ ማስረጃ አይገኝላቸውም፡፡ እነዚህ አሻራዎች በኢርኪዮሎጂካዊ ግኝት የታሪክ ምንጭ ሆነው ለአያሌ ዓመታት  አገልግለዋል፡፡

በርግጥ ለአክሱም ዘመን (እስከ 750 ዓ.ም. አካባቢ) እና ለመጀመሪያው የሰሎሞናውያን ዘመን (ከዐፄ ይኩኖ አምላክ እ.ኤ.አ 1270 እስከ ዐፄ ልብነ ድንግል 1527 ድረስ) ያሉት የታሪክ ምንጮች፣ ከቤተ መንግሥት እና ከቤተ ክህነት የጋራ ውሕደት ጋር በተያያዘ ዜና መዋዕሎች ቀዳሚ ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ የውጭ ሀገር ሚስዮኖች፣ አሳሾች፣ ለፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተልዕኮ የመጡ ተጓዦች የጻፏቸው የጉዞ ማስታወሻዎችም የታሪክ ምንጭ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ፕ/ር ታደሰ ታምራት “ተረት እና ታሪክ በኢትዮጵያ” በሚለው ጽሑፋቸው ላይ ከ750 ዓ.ም. እስከ 1270 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የታሪካችን ምንጮች አነስተኛ መሆናቸውን፣ ከእነርሱም አብዛኛዎቹ ከውጭ አገር የተገኙ ስለመሆናቸው ያብራራሉ፡፡ በታሪክ ምንጭ ድህነቱ የተነሳ “የጭለማ ታሪክ” እየተባለ የሚጠራው ያ- ዘመን በታሪካችን ውስጥ እንደ “ዮዲት ጉዲት” (940-975ዓ.ም) ያሉ የታሪክ ተዋንያንን በመፍጠር ያደፈ ሆኖ ይታያል፡፡ አለቃ ታየ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው “በጉዲት ዘመን ከምሥር ንጉሥ ሸሽተው ከጉዲት ጋር ኢትዮጵያ ገብተው የክርስቲያንን መንግሥት የገለበጡና ያፈረሱ፣ የአክሱምንም ቤተ ክርስትያን ያቃጠሉና  ክርስቲያንን ያረከሱ ናቸው፤” በማለት የዚያን – ዘመን ተዋናዮች ይከስሷቸዋል፡፡ ይሁን እንጅ እንደ አንድ የታሪክ ተማሪ  የአለቃ ታየን መጽሐፍ ለሚገመግም አካል መጽሐፉ ላይ የታሪክ ምንጭ ድህነት ይታይበታል፡፡ የዚህ ሥረ-ምክንያት የታሪክ ምንጭ መሆን የሚችሉ መረጃዎች በጦርነት ከመውደማቸው እና በወቅቱ  የጽሕፈት ባህል ጨርሶ ካለመኖሩ ጋር ይያያዛል፡፡ “የጭለማ ታሪክ” ዘመናት በተረት እና በአፈ ታሪክ እየተሸፈነ እንደመጣ የአለቃ ታየ ስራ ላይ የተጠቀሰው (የያ-ዘመን) የታሪክ አዘጋገብ በአብነት ይጠቀሳል፡፡

ፕ/ር ታደሰ ታምራት ከላይ በተጠቀሰ ጽሑፋቸው ላይ የታሪክ ምንጮቻችንን በጊዜ ክፍልፋይ ሲያስቀምጡ፣ ከመጀመሪያው የሰለሞናውያን ዘመን እስከ ጎንደር ምሥረታ ድረስ ([ሁሉም አቆጣጠሮች እ.አ.አ. ናቸው]1527-1632) ያለውን ጊዜ “በጣም ወሳኝና ለታሪካችን አዳዲስና ዘለቄታማ መልክ ያስገኘ ዘመን” ይሉታል፡፡ ለዚህም በጊዜው ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሚስዮናውያን የጻፏቸው፣ በእርሱም ምክንያት በሕንድ  በኩል ከአውሮፓ ጋራ የነበረው ግንኙነት ያዳበራቸው፣ ከዚህም ጋር የተያያዙት የዐረበኛና የቱርክሽ ሰነዶች፣ የሐረር እና የአውሳ ኤሚሮችን መዛግብትና ገንዘቦች፣ የቤተ ክርስቲያን የከረረ የእምነት ክርክር የፈጠራቸው የታሪክ ምንጮችና የነገሥታቱ ረጃጅም ዜና- መዋዕሎች ሰፋ ያለ ይዘት ያላቸው መሆኑን ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡

ስለ ጎንደር የመሳፍንት ዘመን (1632-1855) የተለያዩ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ጸሐፊዎች የተውልን መረጃ እንደ ቀዳሚ የታሪክ ምንጮች የሚታዩ ናቸው፡፡ በፕ/ር ታደሰ ማብራሪያ፤ የሚቀጥሉት ዘመናት፣ ከዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ንግሥና (1855) እስከ ተፈሪ መኮንን ወደ ንግሥና  መምጣት (1930)፣ ከቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ (1930) እስከ ንግሥና ዘመን ፍጻሜያቸው (1974)፣ ከደርግ ውልደት (1974) እስከ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት (1991) ድረስ ያሉት ሦስት ተከታታይ ምዕራፎች  የታሪክ ምንጮችን በሚመለከት የተለዩ ሆነው ይታያሉ፡፡ ቅድመ 1632 (ከጎንደር ዘመን በፊት) ከነበሩት ዘመናት በዓይነትም ሆነ በመጠን የተለዮ ሆነው ይታያሉ፡፡ በተለይም በ20ኛው ምዕተ ዓመት ውስጥ ያሉት በብዙ ዓይነት ሰነዶች መዳበራቸውን ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ከላይ በተጠቀሰ ስራቸው ያብራራሉ፡፡ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ታሪክን በተመለከተ የታሪክ ፍጥጫው እየጨመረ የመጣው የፖለቲካ ሥልጣን ፍላጎትን ባስቀደመ መልኩ ከታሪክ ምንጭ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ስለመሆኑ አያከራክርም፡፡ አሁንም ቢሆን ከኢትዮጵያ የታሪክ ሙግት መውጫ ጫፎች የታሪክ ምንጮችን የሙያው ዲሲፕሊን በሚያዘው መሰረት ከጊዜ ኑባሬ ጋር እያነጸሩ መጠቀሙ ብቸኛ መፍትሔ ነው፡፡ ከሁሉም በፊት ግን ፖለቲከኞቹ  እጃቸውን ከታሪክ ሊያነሱ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴር ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ቢሆን የጋራ ተግባቦት እና የወል  ማኅበራዊ ኅሊና ያለው ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል ሥርዓት ትምህርት መቅረጽ ይቻላል፡፡

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*