ጠ/ሚ/ር ዐቢይ የካዱን ሃቆች

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ጥር 24/2011 ዓ.ም. ከፓርላማው ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል:: ጠ/ሚ/ሩ ለጥያቄዎቹ መልስ ሲሰጡ በርካታ መልካም ነገሮችን ተናግረዋል:: በእቅድ ደረጃም ሆነ ተግብረናቸዋል ብለው ያቀረቧቸው ጉዳዮች አሉ:: ይሁንና የጠ/ሚ/ሩ ንግግር ላይ ላዩን የ‹‹ለውጥ›› ሀሳብ የያዘ ቢሆንም፣ እስካሁን ከተናገሯቸው የሚጣረሱ፣ በተግባር የማይታዩ፣ አንዳንዶቹም መለስ ዜናዊ አስቀው እውነታውን አድበስብሰው ያለፏቸው አይነት ናቸው:: በንግግራቸው የካዱን በርካታ ሀቆችም አሉ::

የዐቢይ ‹‹መንግስትስ›› መንግስት ነው?

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ፣ መንግስት 20 ያህል ከሚሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መደራደሩን ገልፀዋል:: ‹‹መንግስት ሃያ ከሚጠጉ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ ሀገራት ድርድር ሲያደርግ መደራደሪያ መርሁ አንድ ነው:: ከአንድ ፓርቲ ጋር የሚደራደርበትን መርህ ከሌላ ፓርቲ ጋር የሚቀይር ከሆነ መንግስት መሆን አይችልም:: ንግግራችን መርህን የተከተለ ነው፤›› ብለዋል ጠ/ሚ/ሩ:: እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው:: መንግስት በግልፅ ውይይት እያደረገ ስለመሆኑ በስፋት የተወራው ኤርትራ ከነበሩ ቡድኖች ጋር ነበር::

ከእነዚህ ቡድኖች ጋር የነበረውን ግንኙነት እንኳ ብንመለከት መርህ አልባነቱን በግልፅ እናያለን:: ኤርትራ ከነበሩ ቡድች መካከል ኦነግ፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ አዲኃን፣ ኦብነግ ጋር ውይይቶች እንደነበሩ በስፋት ተወርቷል:: ከእነዚህ ቡድኖች መካከል ግን የጠ/ሚ/ር ዐቢይ መንግስት እንደ ኦነግ ደጅ የጠናው አልነበረም:: ለሌሎች ቡድኖች ያልተደረገውን ለኦነግ ሲሆን ከሌላ ሀገር ጋር ድርድር የሚደረግ ያህል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደረጃ ድርድር ተደርጓል:: የጠ/ሚ/ር ዐቢይ መንግስት ከአንዴም ሁለት ጊዜ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ አስመራ ድረስ ሄዶ የተለማመጠው ኦነግ፣ ሲመለስም መንግስት መጀመርያ ያሳየውን ከልክ ያለፈ ማቆላመጥ እንደመፈራት ቆጥሮ ሀገር ሲያምስ ለመክረሙ የመንግስት መርህ አልባነት አንደኛው መንስኤ ሆኗል::

መንግስት አስመራ ድረስ ተመላልሶ፣ አቆላምጦ ወደ ሀገር ቤት ላስገባው ኦነግ ከዓመታት በፊት የነበረውን ፅ/ቤቱን ሲመልስ፣ ተደራደርኳቸው ለሚላቸው ሌሎች ፓርቲዎች ግን ቢሮ አልሰጣቸውም:: ሌላው ቀርቶ ተደራድረው ገቡ ከተባሉት 20 ድርጅቶች መካከል አብዛኛዎቹ ‹‹ኦነግ ነን›› እያሉ በየጊዜው የሚገቡትን ያህል ክብር ተሰጥቶ አቀባበል አልተደረገላቸውም:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ይህን የመርህ ጉዳይ ከእነ ኦነግ ጋር እንዳደረጉት ስምምነት ባይገልፁት በተሻለ ነበር:: ስለ መርህ ካወሩ ግን አሁንም ድረስ እየፈፀሙት ያሉት ከመርህ ያፈነገጠ ነው:: ኦነግ መሳርያ ወልውሎ ጫካ ሲገባ መሪው ዳውድ ኢብሳ አዲስ አበባ ላይ መንግስት ላይ መግለጫ ሲሰጥ ጠበቅ ያለ ቃል ለመናገር እንኳ ድፍረት አልነበራቸውም:: እነ ዳውድ አፋቸውን ሞልተው ‹‹ትጥቅ አንፈታም›› እያሉ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍ ወለምታ ነው›› ሲሉ አስ ተባብለውላቸዋል::

በሌላ በኩል፣ እነ ዳውድ ኢብሳ በገቡ በማግስቱ በቡራዩና አዲስ አበባ የተፈጠረውን ችግር ለማዳፈን ንፁሃን ወጣቶች ለእነ ዳውድ የጦስ ዶሮ ሆነው ወታደራዊ እስር ቤት ከርመዋል:: በዚህ ወቅት ንፁህ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ወጥተዋል የተባሉት የግንቦት 7 አባላት ብዙ ክስና ውንጀላ ሲቀርብባቸው ድርጅቱም ፈራ ተባ ማለቱ ጥፋት ሆኖበት የመፈንቅለ መንግስት ክስና ወቀሳ መጥቶበታል:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ‹‹ከአንድ ፓርቲ ጋር የሚደራደርበትን መርህ ከሌላ ፓርቲ ጋር የሚቀይር ከሆነ መንግስት መሆን አይችልም፤›› ብለዋል:: ይህን የጠ/ ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ቃል እንደ እውነት እንውሰደው ከተባለ፣ የጠ/ሚ/ር ዐቢይ መንግስትም ‹‹መንግስት›› አይደለም ለማለት እንገደዳለን:: ምክንያቱም ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ መርህ ሲከተል አልታየምና::

ስለ ገዳዩ መከላከያ ለምን አልነገሩንም?

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በአርቡ የፓርላማ ውሎ፣ ‹‹ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን ለመውረር ወይም ለመድፈር ሞክሮ መከላከያው ሰንፎ ያሳለፈበት ጊዜ የለም፤›› ሲሉ የምናውቀውን ሀቅ ክደውናል:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ በኋላ እንኳን የሱዳን መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ፣ የአማራ ገበሬዎችን በከባድ መሳርያ ሲጨርስ፣ ሰብላቸውን ሲያወድም፣ መከላከያ ሰራዊቱ በቅርብ ርቀት ተቀምጦ ከተመልካችነት ያለፈ ሚና አልወሰደም:: የአማራ ገበሬና ሚሊሻ ከአንድ ወር በላይ ከሱዳን ዘመናዊ ጦር ጋር ሲፋለም ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ የሱዳን ጦር ዳር ድንበር ጥሶ እንደገባ ሪፖርት ስላልደረሳቸው አይደለም:: የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግይተውም ቢሆን፣ የሱዳን ጦር ያደረገውን ወረራ ዘግበውታል:: በየቀኑ የሚዲያ ዳሰሳ አጭር ሪፖርት የሚደርሳቸው ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ይህን ጉዳይ ስለማያውቁት አይደለም::

ዐቢይ በፓርላማው ንግግራቸው መከላከያ ሰራዊቱ ዋጋ እየከፈለ የዜጎችን ሕይወት እንደሚያተርፍም ሲናገሩ ተሰምተዋል:: ይህን ሲሉ ግን መከላከያ ሰራዊቱ በቅርቡ የሕወሓት ሀብት የሆነውን ሱር ኮንስትራክሽን ለማጀብ ሲል ኮኪትና ገንዳ ውሃ ላይ በአማራ ሕዝብ ላይ የፈፀመውን ጭፍጨፋ ስላልሰሙ አይደለም:: ጀ/ል አሳምነው ፅጌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ መከላከያ ሰራዊቱ በንፁሃን ላይ የአየር መቃወሚያን የመሰለ ከባድ መሳርያ ሳይቀር መጠቀሙን በግልፅ ተናግረዋል:: ይህ ሀቅ ከጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ የተደበቀ ሆኖ አይደለም:: ጠ/ሚ/ር ይህን ሀቅ በዝርዝር መናገር ቀርቶ መከላከያ ሰራዊቱ በሕዝብ ላይ የፈፀመውን ስህተት ነው ብለው በአጭሩ ማለፍ እንኳ አልፈለጉም:: ይህን አይነት ወንጀል የሚፈፅመውን መከላከያን፣ ሰራዊቱ የሚያኮራ ለውጥ አድርጓል ሲሉ በተደጋጋሚ ሙገሳ ሲያቀርቡለት ይደመጣሉ::

መከላከያ ሰራዊቱ ተለውጧል የሚባለው ንፁሃንን በክላሽ ከመግደል የአየር መቃወሚያ መጠቀሙ ከሆነ አረመኔ መሆኑን ካልሆነ በስተቀር፣ መልካምነቱን ሊነግሩን አይችሉም:: ከጎንደሩ ጭፍጨፋ ባሻገር መከላከያ ሰራዊቱ ወጣቶችን ቤት ለቤት እየዞረ እያነቀበት ያለው የድሬዳዋ ጉዳይም ለጠ/ሚ/ር ትኩረት የሚሰጥ ሆኖ አልተገኘም:: የፓርላማ አባላት የሚጠይቁት ጥያቄ በጠ/ሚ/ር እውቅና ያለውና የተፈቀደ እንደመሆኑ ስለ ድሬዳዋም ሆነ ስለጎንደሩ ጭፍጨፋ ጥያቄ እንዲነሳ አልተፈለገም::

ስለተፈናቀሉት ዜጎች

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ‹‹ሰውን ማፈናቀል ኢ-ሕገመንግስታዊ ብቻ ሳይሆን ኢሞራላዊም ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል:: ሆኖም፣ ይህን ተግባር ጠ/ሚ/ር ዐበይ ከንግግር ባለፈ በተግባር ያምኑበታል ለማለት እየከበደ ነው:: በየክልሉ የሚፈናቀለውን ሕዝብ ለጊዜው ትተነው አዲስ አበባ ውስጥ የሚፈፀመውን ብንመለከት ይህን የጠ/ሚ/ሩን ንግግር ፉርሽ የሚያደርግ ነው:: ከ450 በላይ አባዎራዎች (ወደ 2000 የሚሆን ሕዝብ) ከዚሁ ከአዲስ አበባ በማንነት ምክንያት ተፈናቅለው ኮልፌ ፋኔኤል ቤተክርስትያን ውስጥ ይገኛሉ:: እነዚህን ኢ-ሞራላዊ በሆነ መንገድ የተፈናቀሉ ወገኖች ቤተ ክርስትያን ማስጠለሏ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በኦህዴድ/ኦዴፓ/ ኢህአዴግ ካድሬዎች በቤተ ክርስትያን አባቶች ላይ ጫና እያደረጉ ይገኛሉ::

እነዚህ ወገኖች ኢሞራላዊ በሆነ መንገድ በተፈናቀሉበት ወቅት፣ ሊዘግቡ የሄዱ ጋዜጠኞች ጠ/ሚ/ር በዚሁ ፓርላማ ‹‹የታችኛው አመራር ምንም አላደረገም፤›› ብለው በተከራከሩላቸው አመራሮች እንግልትና ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል:: ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ ከጠ/ሚ/ር ቤተ መንግስት በግማሽ ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው አራት ኪሎ ዜጎች ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ተደርገዋል:: እነዚህ ዜጎች መጠለያ ሸራና ዳሳቸውም ፈርሶባቸው ልጆቻቸውን አስፓልት ላይ ዘርግተው ሲውሉ እነ ዐቢይ የማያውቁ ሆነው አይደለም::

ይባስ ብለው ጠ/ሚ/ር ‹‹ከ‹ሪፎርሙ› በኋላ በችኮላ የተፈናቀሉ ሰዎች ዘጠና በመቶዎቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፤›› ሲሉ ሌላ ሀቅ ክደውናል:: የአማራ ተፈናቃዮችን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ከባህር ዳር እስከ ቆቦ፣ ከሰሜን ሸዋ እስከ ሰሜን ጎንደር በየቦታው በሕዝብ ድጋፍ በተለያየ መጠለያ ይገኛሉ:: እነዚህ ተፈናቃዮች ከኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ ቤንሻንጉል፣ ሶማሊና ሌሎች አካባቢዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢሞራላዊ በሆነ ሁኔታ የተፈናቀሉ ቢሆኑም ወደ ቦታቸው መመለስ አልቻሉም:: መንግስት እገዛ ሲያደርግላቸው አይስተዋልም::

የመለስን ጮሌነት የተዋሱት ዐቢይ

የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት ከሚመሰገንባቸው ተግባራት አንዱ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባቸውን፣ የፖለቲካና የሕሊና እስረኞችን ከመፍታት ባሻገር፣ በእስር ቤት ውስጥ በደል ከፈፀሙት መካከል በሕግ እንዲጠየቁ ስራ መጀመራቸው ነው:: በሌላ በኩል ግን በሰብአዊ መብትም ሆነ በሌብነት ከተጠረጠሩት መካከል አንዳንድ አይነኬዎችን ለማሰር ድፍረት ማጣቱ ሲያስተቸው ቆይቷል::

ይህ በሆነበት ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ፣ ወንጀል መስራቱ በመንግስት ተገልጾ ያልታሰረ ሰው የለም፤›› ብለዋል:: ይህን ካሉ በኋላም ‹‹ልዩነቱ መንግስት ባዘጋጀው እስር ቤት ውስጥ፣ መንግስት እየጠበቀው፣ እየቀለበው በመታሰርና ራሱን ማሰር ካልሆነ በስተቀረ፣ ‹አልታሰረም› የሚል እሳቤ በግሌ የለኝም:: ምክንያቱም ሰው የማይታሰረው በህሊናው እና በአካል በመንቀሳቀስ ነው:: ሰው ገድለህ፣ ወንጀል ሰርተህ ህሊናህ ሰላም አግኝቶ ተኝቶ ማደር አይቻልም:: አንድ ቦታ ራስን አቅቦ መኖር ወዶ ታሳሪ መሆን ነው እንጂ፣ ያልታሰረ መሆን አይደለም፤›› ሲሉ ስለ ፍልስፍና አውርተዋል:: ይህ ንግግር እንደ ፍልስፍና ትክክል ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ከመጀመርያው አባባላቸው የሚቃረን፣ ከመንግስት የሚጠበቅ ንግግርም አይደለም:: እንዲያውም እነ ጌታቸው አሰፋን ለማሰር አቅም ያጡት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ከትችት ለማምለጥ ያደረጉት የመለስ ዜናዊን አይነት የጮሌነት ንግግር መሆኑ ግልፅ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ፣ ወንጀል በመስራቱ በመንግስት ተገልጾ ያልታሰረ ሰው የለም፤›› ያሉት ትክክል አይደለም:: ምክንያቱም የሰብአዊ መብት በመጣስም፣ በሌብነትም ፊት አውራሪ የሆኑት አይነኬዎች መቀሌ መሽገው ይገኛሉ:: አልታሰሩም!

ይህን የመንግስትን መለሳሰለስና ድክመት ለመሸፈን ግን ‹‹የሕሊና እና የአካል እስር›› ፍልስፍናን በማስረዳት መለሳዊ ዲስኩር አደርገዋል:: እንደ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ንግግር ከሆነማ እርሳቸውን ጨምሮ ከላይ እስከታች ያለው የኢህአዴግ አመራር ለ27 ዓመታት በእስር ላይ ነበር ማለት ነው:: እንደ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ፍልስፍና ከሆነማ እርሳቸው ስልጣን ላይ ያስቀመጧቸው፣ የ1997 ዓ.ም. ጭፍጨፋን ያስፈፀሙ፣ የዘረፉ ነገር ግን ‹‹ተደምረዋል›› የተባሉት ሳይቀሩ በርካቶች በእስር ላይ ናቸው ማለት ነው:: እንደ ጠ/ሚ ዐቢይ ከሆነማ አሁን በእስር ላይ የሚገኙትንም ‹‹ሕሊናቸው ይውቀሳቸው›› ብሎ መተው ሊገባ ነበር ማለት ነው::

በሚዲያ ላይ ያሳዩት አምባገነንነት

የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ጥሩ ለውጥ ከታየባቸው መካከል ሚዲያ አንደኛው ነው:: እንደ አሸባሪ ሲታዩ የነበሩ ሚዲያዎች ሀገር ውስጥ ቢሮ እንዲከፍቱ ከመደረጋቸው ባሻገር ከዛ ቀደም የነበሩት መሰናክሎች በመጠኑ ተነስተዋል:: በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች ተፈትተዋል:: ይሁንና ባለፉት የኢህአዴግ የሥልጣን ዘመናት የገዥዎቹ ቃል አቀባይ በመሆናቸው ምክንያት ሁሉም በእጄ ሁሉም በደጄ የሆነላቸው ሚዲያዎች ዛሬም የፈረጠመ ክንዳቸውን ይዘው ቀጥለዋል:: እነዚህ ሚዲያዎች ድሮም አብረውት ይሰሩት የነበረውን የኢህአዴግ መዋቅር ተጠቅመው መረጃ ያገኛሉ:: በሌላ በኩል ግን የቆየው ድብቅ የኢግአዴግ አሰራር ተቀይሯል ለማለት የሚቻል አይደለም:: በተለይ፣ መረጃን በመስጠት:: ይህ ደግሞ ባለፈው ዘመን ከኢህአዴግ ጋር ሲሞዳሞዱ ከነበሩት ውጭ ላሉት ሚዲያዎች ይበልጥ ፈታኝ ነው:: በዚህም ምክንያት ሚዲያዎች በመረጃ እጥረት አስተያየት ሰጥተው የሚያልፉባቸው፣ ያልጠነከሩ መረጃዎችን የሚያወጡባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ:: ቢኖሩም የሚገርም አይደለም::

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በአርቡ የፓርላማ ንግግራቸው ‹‹ዶላር 70 ብር ይገባል ብሎ የሚጽፍ ማንም ግለሰብ ብሔራዊ ባንክን ካልጠቀሰ በሕግ የሚጠየቅ መሆኑ መታወቅ አለበት፤›› ብለዋል:: ይህ ንግግር ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ከመምህራን ጋር ባደረጉት ውይይት ‹‹ወደ አምባገነንነት ጫፍ ደርሰናል›› ያሉትን የሚያጠናክር ንግግር ነው:: አንድ ሚዲያ የተሳሳተ መረጃ ማውጣት የለበትም:: የተሳሳተ መረጃ ያወጣ ሚዲያ መጀመርያ የሚዳኘው በአንባቢውም ጭምር ነው:: የተሳሳተ መረጃ በሕግም ሊያስጠይቅ ይችላል:: ይሁንና ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ በሕግ ያስጠይቃል ያሉበት መንገድ በብዙ መንገድ ቢመዘን የተሳሳተ ነው:: አንደኛውና ዋነኛው የዶላር ምንዛሬን እንደፈለገ እንዲሄድ እያደረገው ያለው መንግስት ራሱ ነው:: የጥቁር ገበያ ሕገወጥ ነው እየተባለ ዶላር ሻጭዎች ግን መሃል መንገድ ላይ ‹‹ዶላር ፈልገህ ነው›› እያሉ አላፊ አግዳሚውን ሲወተውቱ ሲውሉ መንግስት የማያውቅ ሆኖ አይደለም:: እንዲያውም በዚህ የዶላር ጥቁር ገበያ ውስጥ ከፍተኛ የደሕንነት መስርያ ቤት ኃላፊዎች፣ የፖሊስ ኃላፊዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ እንዳለበት የሚካድ አይደለም::

የባንክ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ሳይቀር በዚህ የዶላር ገበያ መዘፈቃቸው ከመንግስት የራቀ ሀቅ ሆኖ አይደለም:: በአደባባይ ዶላር ሲቸበቸብ ዝምታን የመረጠ መንግስት ጋዜጠኛው የባንኮችን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ገበያውን ዋጋ ጭምር ግምት ውስጥ አስገብቶ ዘገባ ቢሰራ ስህተት ሊሆን አይችልም:: በተጨማሪም ለጋዜጠኞች በአግባቡ መረጃ የሚሰጥ የመንግስት ተቋም እምብዛም በሆነበት ሁኔታ ጠ/ሚ/ሩ ዶላር ተወደደ ብሎ የዘገበ ጋዜጠኛና ሚዲያ ላይ እርምጃ እንወስዳለን ዛቻ የራስን ችግር ወደ ውስጥ ካለማየት የሚመጣ፣ ኃላፊነት የጎደለው እርምጃ እንጅ ሌላ ሊባል አይችልም::

ዋለልኝ መኮንንና ዐቢይ ምንና ምን ናቸው?

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡባቸው የቅስቀሳ መንገዶች ዋነኛው የኢትዮጵያ አንድነት ነው:: ጠ/ሚ/ር በየጊዜው ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚያሰሟቸው ዲስኩሮች፣ በማንነት የተቋቋመው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ሊቀመንበር መሆናቸውንም እስከማስረሳት ደርሷል:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ባለፉት 6 እና 7 ወራት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የባለፈውን ታሪክ ችግሮች ከማውራት ይልቅ ወደፊት የሚኖረውን እድል ብናወሳ ተጠቃሚ እንደምንሆን ተናግረዋል:: የመነጣጠል ታሪክና ትርክት ከማመንዠክ ይልቅ አብሮነትን ብናቀነቅን እንደምናተርፍ ነግረውናል:: ጠ/ሚ ወደ ስልጣን ለመምጣትም ሆነ ስልጣን ከያዙ በኋላ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የፖለቲካ ቡድኖችም ሳይቀሩ እንዲያጨበጭቡላቸው ምክንያት የሆነው ሕወሓት/ ኢህአዴግ ባለፉት 27 ዓመታት ሲደጋግማቸው የነበሩ አሉታዊና ነጣጣይ ታሪኮችን በተለየ አዲስ አስተሳሰብ አምጥተዋል ተብሎ በመታሰቡ፤ ጠ/ሚ/ር ዐቢይም አዲስ አስተሳሰብ አምጥቻለሁ ብለው በተደጋጋሚ በመናገራቸው ነው::

ይሁንና በፓርላማው ውሎ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተምሳሌትነት ያነሱት የ1960ው ትውልድ፣ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በየአደባባዩ ሲናገሩት ከቆዩት ትርክታቸው ጋር የሚያጋጫቸው ሆኖ እናገኘዋለን:: ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ እየፈጠሩ ነው›› ብለው ለወቀሷቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተምሳሌት ይሆኑ ዘንድ በምሳሌነት ካነሷቸው መካከል ዋለልኝ መኮንን አንደኛው ነው:: ዋለልኝ መኮንን ‹‹የብሔሮች ጥያቄ›› በሚል አመለካከቱ የሚታወቅ የ1960ዎቹ ትውልድ መሪዎች መካከል ነው:: ዋለልኝ መኮንን ‹‹እንጀራና ሸማ የአማራ ነው:: በሌላው ሕዝብ ላይ የተጫነ ነው፤›› እያለ ሲሰብክ የነበር ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በእንጀራም፣ በቆጮም፣… በአልባሳትም፣ በምግብም፣…በምንም ሊለያዩ የማይገቡ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነግሩን ቆይተዋል::

ሆኖም፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እያመፁ ነው ላሏቸው ተማሪዎች ምሳሌ ይሆን ዘንድ የሚጠቅሱት ‹‹እንጀራ የአማራ እንጅ የአንተ አይደለም›› እያለ አንዱ ከሌላው እንዲለያይ ሲሰብክ የነበረን የአመፅ መሪን ሲጠቅሱ ተሰምተዋል:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ቃል በቃል ያደነቁት ዋለልኝ መኮንን ‹‹ኢትዮጵያ የብሔሮች እስር ቤት ነች›› ማለቱን ነው:: ይህን የዋለልኝ ሀሳብ ያደነቁት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ባለፉት ንግግሮቻቸው ያለፈውን ታሪክ ትተን ለወደፊቱ እናስብ ብለውን ነበር:: አሁን ደግሞ ተማሪዎች ዋለልኝን እንዲያስቡት እየተናገሩ ነው::

ዋለልኝ መኮንን ለሕወሓት፣ ኦነግ፣ ሻዕቢያና ሌሎች ተገንጣዮች የሀሳብ አባት መሆኑ ግልፅ ነው:: ‹‹ኢትዮጵያ የዛፍ ቅጠል አይደለችም:: አትገነጣጠልም፤›› ሲሉ የከረሙት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ታዲያ በአርቡ ንግግራቸው የሻዕቢያ፣ ኦነግና ሕወሓት የአስተሳሰብ አባት የሆነውን የ60ዎቹን ትውልድ ክፉ መንፈስ ለተማሪዎች በምሳሌነት ጠቅሰዋል:: በዚህ ፓርላማ ላይ የ60ዎቹ ትውልድ ፖለቲካ አጥፊ በመሆኑ አዲስ መንገድ መከተል እንዳለብን ሲመክሩ የዋሉት ጠ/ሚ/ር ከደቂቃዎች በኋላ ግን መጀመርያ የከፋ ያልነበረውን የተማሪዎች ንቅናቄ ‹‹ኢትዮጵያ የብሔሮች እስር ቤት ነች›› ብሎ የበጠበጠውን አስተሳሰብ ባለቤት በሞዴልነት አንስው የ60ዎቹን ፖለቲካ እንደማይጠሉት አሳይተዋል:: ዋለልኝ መኮንንን አስተሳሰቡን ወደጎን ጥለን ተግባሩን እንኳ ብናይ አውሮፕላን ሲጠልፍ እንደተገደለ አንረሳውም:: ድንጋይ አትወራወሩ ያሏቸውን ተማሪዎች ዋለልኝን ሞዴላቸው እንዲያደርጉ ሲመክሩ ሳያስቡት የአውሮፕላን ጠለፋ ጀብዱንም ሕጋዊ እያደረጉላቸው መሆኑን የዘነጉት ይመስላል::

ከዋለልኝ መኮንን በተጨማሪ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊ ማን ነው›› ብሎ ንጉሱን ጠይቋል ያሉት ኢብሳ ጉተማም የዚያ ‹‹ገዥና ተገዥ›› ትርክት አቀንቃኝ ትውልድ አባል ነው:: ልክ እንደዋለልኝ ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ እየተረገመ ያለውን አማራ ገዢ አድርጎ የሚቆጥር የጥላቻ ዘመን ትውልድ አንዱ ተዋናይ ነው:: ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድም ሳያውቁት ይህን የ1960 የጥላቻ ትውልድ አመለካከት በፓርላማ ሰብከዋል:: በአጠቃላይ ከላይ ከተጠቀሱት ባሻገር የተምታቱ፣ እርስ በእርስ የሚጣረሱ ጉዳዮችን ነግረውናል:: በርካታ ሀቆችንም ክደውናል:: ከላይ የተጠቀሱት እንደምሳሌ ይሆኑ ዘንድ ብቻ ነው::

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*