አንዳርጋቸው ምን ያድርግ? – (በጌታቸው ሽፈራው)

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ትናንት በናሁ ቲቪ ለቀረቡት ታጋዮች መልስ እንዲሳጥ ተጠይቆ ስሜታዊ ሆኖ የሰጠውን ምላሽ አየሁ። ሰዎች ፌስቡክ ላይ ሲወቅሱት አየሁ። እኔ ግን በአንዳርጋቸው አልፈርድም። አቶ አንዳርጋቸውኮ እየሰራ ያለው በአንድ በኩል የግንቦት 7 ጉድ እሸፍናለሁ ሲል በሌላ በኩል እርቃኑን ከሚያስቀሩበት እነ ኤፍሬም ማዴቦ ጋር ነው።

አንዳርጋቸው ከኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ጋር ያለው ነገር ሲያስጨንቀው ኤፍሬም በሚዲያ ወጥቶ “እነሱ የሚፈልጉት የድሮዋን ኢትዮጵያን ነው” እያለ ህወሓትና ኦነግን በአሁኑ ወቅት የተውትን ፍረጃ ይለጥፍና ድርጅቶቱን ገመና ይገልጣል። አቶ አንዳርጋቸው የታጋዮች ጉዳይ ይፈታል ሲል ኤፍሬም ማዴቦ የእነሱ ጉዳይ ጉዳዬ አይደለም ብሎ ሌላ ጣጣ ያመጣበታል። አንዳርጋቸው ክፍለ ሀገር ሄዶ የታጋዮቹን ምሬት ሰምቷል። ታጋዮቹ ቃል በቃል “ለአንዳርጋቸው አዘንለት” ሲሉ ሰምቻለሁ። እነ ኤፍሬም ያበላሹትን ሊጠግን ሲጥር እንደገና ያፈራርሱበታል። ታዲያ አንዳርጋቸው እንዴት ስሜታዊ አይሁን?

አራት አመት ተሰቃይቷል። እሱ እንዲዋሃድ ጥረት ያደረገለት የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርና ግንቦት 7 በኤርትራ መንግስት ግዳጅ እንጅ በአላማ አልቆዩትም። አሁን እርስ በእርስ እየተናቆሩ ነው። አንዳርጋቸው እንደተፈታ “አልተኮስንም” ብለው አስዋሹት። ቆይቶ ተኩሰውም ክብር ያልተሰጣቸውን ሰዎች ሰማ። አሁን ለማስተባበል ተገደደ። አምስት ሺህ ጦር አለን አሉት። ከኤርትራ የመጡት 250 አይበልጡም። የእኛ ናቸው ያሏቸው የአማራ ፋኖዎችን “ኑ እኛ እናስገባችሁ!” ቢላቸው “አናምናችሁም” አሏቸው። አንዳርጋቸው የተግባር ሰው ስለሆነ የሚወራው ሁሉ እውነት መስሎታል። እውነታው ግን ሌላ ነው። ያበሳጫል። ስሜታዊ ያደርጋል። እንዴት አይናደድ? እንዴት ስሜታዊ አይሁን?

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እስረኞችን ለማስፈታት ጥረት አድርጓል። እስረኛ የለንም ብለው ዋሽተውት ነበር። እውነታውን ሲሰማ ሳይደነግጥ አልቀረም። ለታጋዮች ቋሚ መተዳደርያ ይኖራቸዋል ተብሎ ነበር። አልሆነም። ይባስ ብሎ በግንቦት 7 አቀባበል ሰበብ ያለ አግባብ የታሰሩትን የአዲስ አበባ ወጣቶች ይፈቱ ለማለት ድፍረት ጠፋ። አንዳርጋቸው በዚህ ተናዶ ይመስላል ወደአውሮፓ ተመልሶ ነበር ተብሏል። እንደገና ወደስራው ተመልሶ ተፍ ተፍ ቢል እንኳ የግንቦት 7 ጉድ የሚሸፈን አይደለም። እነ ኤፍሬም እያሉ?

አሁን ብዙዎቹ ችግር ላይ ናቸው። የግንቦት 7ን ጣጣ አንድ አንዳርጋቸው የሚፈታው አይደለም። በአንዱ ሊሸፍን ሲጥር በሌላኛው ይጎትቱበታል!

አንዳርጋቸው ከእነ ኤፍሬም ጋር ከቀጠለ ብዙ ትዝብት ውስጥ ያስገቡታል። እንደኔ ሁለት የተሻሉ አማራጮች ያሉት ይመስለኛል።

ግንቦት 7 ውስጥ ካሉት ጥቂት ደፋሮች ጋር ሆኖ ከእነ ኤፍሬም በየጊዜው የማይጎትቱት አዲስ ድርጅት መመስረት አንዱ አማራጭ ነው። በአዲስ መልክ ይደራጃል የሚባለው ፓርቲም ተስፋው ያን ያህል ነው። ኢዴፓን ሀገር ያውቀዋል። ሰማያዊ ፓርቲ ደፋርና ከአንዳርጋቸው ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ወጣቶ ቢኖሩትም አብዛኛው ገለባ ነው። ደሕንነቶች የተሰገሰጉበት ፓርቲ ነው። ከሳምንት አንድ ቀን ቢሮ ብቅ ብለው ዜና ጠይቀው ከመሄድ ውጭ የረባ ስራ ሊሰሩ የማይችሉ አዛውንቶችም ሞልተውበታል። ልክ እንደ ጥቂት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ሁሉ ከቀድሞው አንድነትም ሰዎች አሉ። የእነ የሺዋስ ሰማያዊ ውስጥ ያሉ በጣት የሚቆጠሩ ለፖለቲካው የሚያስፈልጉ ሰዎች ከእነ ኢንጅነር ይልቃል ጋር የተለያዩት በእልህና ደሕንነት በሚያስወራባቸው አሉባልታ ነው። ችግር ቢኖርም በአላማ የሚለያዩ ሰዎች አይደሉም። እነሱን አስታርቆ እነዚህን ሰዎች ማንጠር ቢችል አንዳርጋቸው ከሚባለው የተሻለ ፓርቲ ማቋቋም ይችል ነበር። ገለባው ግን ብዙ ነው። አያሰራውም።

ሌላው አማራጩ ቀድሞ ወደነቃበት ፖለቲካው መመለስ ነው። አቶ አንዳርጋቸው የእነ ኤፍሬም ማዴቦን ግንቦት 7 ጥሎ ድሮ ያቀነቅነው የነበረውን የአማራ መደራጀት ላይ እየሰሩ ያሉትን የአብን ወጣቶች ቢመክር የሚሻለው ይመስለኛል። አባል ባይሆንም ቀድሞ የነቃበትን የአማራ መደራጀት ጉዳይ እየመከረ ቢፅፍና ቢያስተምር የሚሻለው ይመስለኛል። እነ ኤፍሬም ማዴቦ ጋር ሆኖ እየሰራ ቢበሳጭና ስሜታዊ ቢሆን ግን አይገርምም። እኔ ያሳዝነኛል። ሊተች የሚችለው ከአሁን በኋላም ይህን ሁሉ ጉድ ተሸክሞ ከቀጠለ ነው።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*