እምቦጭን በተመለከተ የሚቀርበው ሪፖርት ከእውነት የራቀ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ።

በጎርጎራ አካባቢ አዲስ አረም ተከስቷል

በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው እምቦጭ የተባለ አረም እየጠፋ እንዳልሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ለበረራ ተናግረዋል:: እምቦጭ በጣና ሐይቅ ላይ ከታዬ
ጊዜ ጀምሮ፣ የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ሙከራዎች መደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኙት የጎንደር እና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ማጨጃ ማሽኖችን
በመግዛት የማስወገድ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም እስካሁን ባለው ሂደት ፍሬያማ መሆን እንዳልቻለ ለማወቅ ተችሏል::

በሌላ በኩል፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለባዮሎጂካል ሙከራ የወሰደው የእምቦጭ ናሙና አባይ ወንዝን እየወረረ ነው ተብሏል:: እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ፣ መንግስት
ለሪፖርት እንዲያመቸው ትኩረቱን ከተማ ላይ ብቻ አድርጓል:: በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ማክሰኝት ወረዳ ንጥርሃ አባዋርካ፣ ሸዋ ጎመንጌ፣ ለምባና ሲርቃ ዳንጉሬ፣
እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምከም ወረዳ ጥርኛ፣ አግድ ጥርኛ፣ ጤዝአምባ እና ካብ ቀበሌዎች 70 ኪ.ሜ. ያህሉ ጀልባ እንደማያስገባ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል::

ለ12 ዓመታት ያህል በአሳ ማስገር ሥራ ላይ የተሰማሩትና በበጎ ፍቃድ አረሙን የማስወገድ ስራ እያከናወኑ የሚገኙት የማክሰኝት ወረዳ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ
ውብነህ፣ ‹‹በእምቦጭ ጉዳይ የተያዘው ቀልድ ነው:: የገንዘብ ምንጭ በማድረግ ችግሩ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ:: በውጪ ሀገር ያሉ ገንዘብ ይለግሳሉ፤ ማሽኖች ተገዙ
ይባላል:: ያሉት ማሽኖች ተመረቁ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ፣ አንድም ቀን ስራ አልሰሩም:: በዚህ ውስጥ ሰፊና የተደራጀ የገንዘብ ትስስር አለ:: በተለያየ ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያና
በዋና መገናኛ ብዙሃን ፕሮፓጋንዳ ያሰራጫሉ›› ብለዋል::

አቶ ብርሃኑ አክለውም፣ ‹‹ሐይቁን ከእምቦጭ አረም ለማንጽዳት እየተሰራ ያለ ጉልህ ስራ የለም፤ ብዙዎች የገንዘብ ምንጭ አድርገውታል፤ አማራ ቴሌቭዥንን
ጨምሮ ሌሎች ጣቢያዎች ዘጋቢ ፊልም ቢሰሩበትም ሳይተላለፍ ቀርቷል፤ ይህ ከባድ የጥቅም ሰንሰለት እንዳለ ይጠቁመናል፤ ያም ሆነ ይህ ግን፣ እምቦጭን ለማጥፋት
በማሽን ሳይሆን፣ የክረምት ወራት ከመድረሱ በፊት ሰፊ የሰው ኃይል በማሰማራት ማጥፋት ይቻላል:: በጣና ጨርቆስ ገዳም አካባቢ ያለው እንቦጭ የተወገደው በሰው
ኃይል ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል::

ከባህር ዳር ከተማ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ሻሼ ፋንታ የተባሉ ግለሰብ በበኩላቸው፣ “ስራውን በበላይነት የሚቆጣጠርና የሚያግዝ የመንግስት አካል የለም:: የሚያቀርበው ሪፖርትም ውሸት ነው:: እምቦጭ
እየተስፋፋ ነው፤ ጣና ወደ ነበር ሊቀየር ይችላል፤›› ብለዋል:: ለጣና ሐይቅ ተቆርቋሪ ተቋም ጠፍቷል የሚሉት ወጣቶች፣ “በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከቱሪዝም
ፍሰቱ ይገኛል፤ ነገር ግን ተጨባጭ የሆነ ስራ እየተሰራ አይደለም፤” ብለዋል::

ሦስት የመከላከያ መንገዶች እንዳሉ የገለፁት የኢትዮጵያ ደንና ምርምር ኢንስትቲዩት ተመራማሪ አቶ አዱኛው አድማሱ በበኩላቸው፣ ‹‹መካኒካል፣ ባዮሎጂካል፣ ኬሚካል መንገዶችን በመጠቀም እየሰራን
ነው፤ ይኸንንም በሐይቁ አቅራቢያ ጎርጎራ ላይ እየሰራን ነው፤›› ብለዋል:: ጣና ላይ ከተጋረጠው እምቦጭ በተጨማሪ፣ በጎርጎራ በኩል አዲስ አረም ተከስቷል ያሉት ተመራማሪው፣
‹‹እሾሃማና ቁመቱ ዘጠኝ ሜትር የሚደርሰው ይህ አረም፣ የጣናን ሦስት ሄክታሩን ያህል ይዞታል፤ አረሙ እስካሁን ስም አልወጣለትም፤ በሳይንስ ስሙ Aeschynomene elaphroxylon ይባላል:: ምንጩ Tropical area ሲሆን
ዋና መገኛው ሴኔጋል ነው፤›› በማለት አዲስ ስለተከሰተው አረም ተናግረዋል::

– ዮሐንስ አለነ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*