ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ጎንደር በተፈጸመው ግድያ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ አብን ጠየቀ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ጎንደር በመከላከያ ሰራዊቱ ንጹሃን መገደላቸውን በመጥቀስ፣
በጉዳዩ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ አዣዥ የሆኑት ዐቢይ አህመድ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጡ
ጠይቋል፡፡ አብን ጥር 04/2011 ዓ.ም. በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፣
በምዕራብ ጎንደር አካባቢ ለመንገድ ስራ በሚል በገባው፣ ‹‹የህወሓት ንብረት የሆነ›› ሱር ኮንስትራክሽን
የተባለ ተቋም ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት፣ መከላከያ ንጹሃንን መግደሉን አስታውቋል፡፡ የአማራ
ህዝብ ዛሬም አማራ-ጠል በሆኑ ተቋማት አማካኝነት ጥቃት እየደረሰበት እንደሚገኝ አብን በመግለጫው
አመልክቷል፡፡

አማራውን በጨቋኝነት ፈርጆ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች በጠላትነት እንዲነሱበት በማድረግ፣ ‹‹ዘላለማዊ ረፍት›› የመንሳት ስሁላዊ የትሕነግ/ሕወሓት
መመሪያዎች፣ ባለፉት 27 ዓመታት መንግስታዊ ፖሊሲ ሆነውና ተቋማዊ ቅርፅ ይዘው ሲተገበሩ እንደቆዩ
የገለጸው አብን፣ ሕወሓት በዋናነት በአማራ ተጋድሎና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እምቢተኝነት ከአዲስ አበባ
ተባሮ መቀሌ የመሸገ ቢሆንም፣ በአማራ ጠልነት የተገነቡ ተቋማት ግን ዛሬም ድረስ ከዚህ ትርክትና ስሁላዊ አስተምሮ ተላቀዋል ማለት አይቻልም ብሏል፡፡
‹‹በዚህ የተነሳ፣ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ዓይን በማየት በፍትሃዊነት ማስተናገድ የሚገባቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣ ዛሬም ድረስ አማራ ላይ ሲሆን
አማራ-ጠል መመሪያቸው ባለመቀየሩ፣ ሕዝባችንን በየጊዜው እየተነኮሱና አጀንዳ እያቀበሉ ሰላምና
መረጋጋቱን በመንሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ሲያልፍም፣ ከሰሞኑ በምዕራብ አማራ ገንደ ውሃና ኮኪት አካባቢዎች
ሰላማዊ ወገኖችን፣ በመደበኛ ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ትጥቆችን ጭምር በመጠቀም፣ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል፡፡

በዚህም ከአስር በላይ አማራዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፣ ከ25 በላይ ወገኖቻችን ደግሞ ቆስለው በሕክምና ላይ
ይገኛሉ›› ብሏል አብን በመግለጫው፡፡ መከላከያ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች ዳር ድንበርን ለመጠበቅ የመሰማራት ሕጋዊ መብቱ እንዳለ
ሆኖ፣ በመደበኛ የፀጥታ አሰራር የፖሊሲን ተግባርና ኃላፊነት ተክቶ እንዲሰራ ግን አይጠበቅም፤ ከሕግ አሰራር
ውጭም ነው ያለው መግለጫው፣ ይባስ ብሎ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ መዋቅሮች የየአካባቢያቸውን የፀጥታ
ሥራ ለመስራት ከአቅማችን በላይ ነው ብለው የፌዴራል መንግስቱን እገዛ ባልጠየቁበት፤ ጉዳዩ ከፌዴራል
መንግሥቱ መደበኛ የፀጥታ አካላት አቅም በላይ ሆኖ የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብነት ባልተጠየቀበት
ሁኔታ፣ መከላከያ ሰራዊቱ በምዕራብ አማራ ገንዳ ውሃ እና ኮኪት ከሰሞኑ ያደረገው ሕግን ያልተከተለ ጣልቃ
ገብነት ጨምሮ፣ ባለፈውም የቅማንት ኮሚቴ ነን በሚሉ አካላት በፈጠሩት ግርግር ወቅት የነበረው ተሳትፎ፣
መላው ሕዝባችንን ያስከፋና በመከላከያ ላይ እንደተቋም አመኔታን የሚያሳጣ እንደሆነ አስገንዝቧል፡፡
በመከላከያ የሚሰጡ መግለጫዎችን የተቸው አብን፣ ‹‹መከላከያው ወደ ሰማይ ነው የተኮሰው›› በሚል
የተሰጠው አማራውን የመናቅ እና አማራ-ጠል መግለጫ፣ ከተደረገው ግድያ በላይ የሕዝባችንን ስሜት ክፉኛ የጎዳ
ሆኗል ብሏል፡፡ ‹‹አማራ በሰማይ በራሪ ወፍ አይደለም፣ መከላከያ ወደ ሰማይ ተኩሶ የሚገድለው፡፡ አማራ
የማናቸውም ኃይል የተኩስ መለማመጃም አይደለም፡፡ በመካለከያ ምክትል ኤታማዦር ሹሙ በኩል የተሰጠው
መግለጫ ግን ሕዝብን ለበለጠ ቁጣ የሚያነሳሳ፣ ተንኳሽና በአማራ-ጠልነት የተሞላ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ብሏል አብን፡፡
የአማራ ሕዝብ ማናቸውም አማራ-ጠልና የሕወሓት ‹አሽከር› የሆነ ተቋም ወይም ቡድን በሚያደርሰው ጥቃትና ግድያ መሰላቸቱን የጠቀሰው
መግለጫው፣ ‹‹የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መንግሥት የሕዝባችንን ደኅንነት ያስከብር እያለ በየጊዜው መግለጫ ማውጣቱንም አንዳንዶቹ እንደማይናከስ ጩኸታም ውሻ
አድርገው ወስደውታል፡፡ እውነታው ግን መንግሥት ሕግን ማስከበር ካልቻለና ካቃተው፣ የአማራ ሕዝብ ኅልውናውን የማስከበር ተፈጥሯዊ መብቱን ለመጠቀም
የሚገደድ መሆኑ ነው፡፡ አብንም ሕዝባችን ተፈጥሯዊ ኅልውናውን የማስቀጠል መብቱን እንዲያስከብር ጥሪ ከማድረግ አልፎ፣ ይህን መብቱን የማስከበር እንቅስቃሴ፣
መምራትና ማስተባበር ውስጥ ተገዶ ሊገባ የሚችል መሆኑ፣ በሁሉም ዘንድ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይህ መሆኑ አማራውን በተለየ ተጎጂ የማያደርግ ቢሆንም፣ ሁሉንም
ሕዝብ የሚጎዳ፤ የአገር አንድነትንም የሚፈታተን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል›› ሲል አስታውቋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመግለጫው አንስቷል፡፡ እነዚህም፡-
1. የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የመከላከያ ሚኒስትሯና ኤታማዦር ሹሙ በተፈጠረው ጉዳይ ላይ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጡ፤
2. ከሰሞኑ ገንዳ ውሃና ኮኪትን ጨምሮ፣ ራሳቸውን የቅማንት ኮሚቴ ነን ብለው የሚጠሩ የሕወሓት አሽከሮች ውንብድና ወቅት መከላከያ ሰራዊቱ ከሕግ ውጭ ወደ ፀጥታ ማስከበር በመግባት
ላደረሰው ግድያ ይቅርታ እንዲጠይቅና ለተጎጂ ቤተሰቦችም ካሳ እንዲከፍል፤
3. በሁለቱም አጋጣሚዎች ትዕዛዝ ያስተላለፉ፣ በወንጀሉ የተሳተፉና ወንጀሉን ለመሸፋፈን በሕዝባችን ላይ ተጨማሪ ቁጣን የቀሰቀሱ የመከላከያ አመራሮችና አባላት ለሕግ እንዲቀርቡ፤
4. መከላከያ ሰራዊቱ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ መዋቅሮች ሳይጠይቁት ወደ መደበኛ የፀጥታ ማስከበር ስምሪት እንዳይገባና የአገር ዳር ድንበርን የመጠበቅ ዋነኛ ተልዕኮው ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤
5. የመካላከያ መዋቅሩና ሰራዊቱ ከህውሓት አማራጠል አስተምህሮ ዛሬም ድረስ እንዳልተላቀቀ በፈፀማቸው ፀረ-ሕዝብ ድርጊቶች የተረጋገጠ ስለሆነ፣ እንዳዲስ ኢንዶክትሪኔሽን እንዲሰራለትና ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩል ዓይን ወደ ማየት
እንዲሸጋገር ጠይቋል፡፡ አብን፣ ‹‹መንግሥት ለጥያቄዎቻችን በአስቸኳይ ምላሽ በመስጠት ፍትኅን ማስፈን ካልቻለ፣ አልያም ፍትኅን ለማስፈን ፍላጎት ካላሳየ፣ መላውን አማራ በማንቀሳቀስ ተፈጥሯዊ መብቱን እንዲያስከብር የሚያስተባብር መሆኑን እናሳውቃለን፤›› ብሏል፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የአብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ ም/ሊቀመንበር በለጠ ሞላ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ ጋሻው መርሻ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ከጋዜጠኞች
ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም፣ ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጋር በሰላምና ደህንነት፣ ፀጥታና ልማት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው መገለጹን ተከትሎ፣ ማብራሪያ
ተጠይቀዋል፡፡ አመራሮቹ፣ ከአዴፓ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ማናቸውም በአማራ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎቶች ዙሪያ ከሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ኃይል ጋር ለመስራት አብን በመርህ ደረጃ የያዘው አቋም መሆኑን በመግለጽ፣
ከአዴፓ ጋር ያለው ግንኙነት በዚህ አግባብ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ በምዕራብ ጎንደር ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ፣ በመግለጫው የተጠቀሱት አማራ-ጠል ተቋማት ሲባል እነማንን ለማለት እንደሆነ የተጠየቁት አመራሮቹ፣ በአጠቃላይ የህወሓት ድርጅቶች አማራጠል ናቸው ብለው እንደሚያምኑ፣ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ያልተደረገበት መከላከያ ሠራዊትም የህወሓት የእጅ ሥራ በመሆኑ አማራ-ጠልነቱን እያዩ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በምዕራብ ጎንደር ለተፈጸመው ግድያ መነሻ የሆነው ሱር ኮንስትራክሽን የተባለው ተቋም አማራ-ጠል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*