40-40-20 አሰራር በድሬዳዋ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው

የድሬዳዋ ከተማን ደህንነት ለማረጋገጥና የሁለት ብሄር ተወካይ ድርጅቶችን የስልጣን ሽኩቻ ለማቻቻል በሚል በሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ስምምነት በ2000
ዓ.ም. እንደወጣ የሚነገርለት የ40-40-20 መመሪያ፣ በወጣቶች የሥራ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ ተገልጿል::
መመሪያው ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ እንደዋለ  የከተማዋ ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ በከተማዋ በሚኖሩ የአማራ እና ሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ
ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል:: ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት በህግ ደረጃ የወጣ ነገር ባይኖርም፣ ኢህአዴግ እና ሶህዴፓ (ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ
ፓርቲ) ያደረጉት ስምምነት በቃለ-ጉባኤ ተፅፎ እንደሚገኝ ታውቋል::

በስምምነቱ መሠረት፣ 60 በመቶው ለኢህአዴግ፣ እንዲሁም 40 በመቶው ለሶህዴፓ በሚል የስልጣን ክፍፍል እንደተደረገ የተገለጸ ሲሆን፣ ለኢህአዴግ
ከተሰጠው የ60 በመቶ ድርሻ ላይ 40 በመቶ ያህሉን ኦህዴድ/ኦዴፓ እንደሚወስድና ቀሪውን 20 በመቶ ስልጣን፣ የቀሩት እህት ድርጅቶች (ህወሓት፣ ዴኢህዴን
እና ብአዴን) ይወስዳሉ:: በዚህ አሰራር መሠረት አብላጫ የምክር ቤት መቀመጫዎች የሚያዙት ሁለቱን ብሄሮች (ኦሮሞ እና ሶማሌ) በሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሆናል::
የአስፈፃሚው አካላት ቦታዎችም በዚሁ 40-40-20 መመዘኛ ይከፋፈላሉ:: በየትኛውም የስልጣን ክፍፍልም ሆነ የስራ ዘርፍ መቀጠር ለሚፈልጉ ነዋሪዎች ከፍተኛውን
ድርሻ ለኦሮሞ እና ለሶማሌ ተወላጆች ቅድሚያ ይሰጣል:: ይህም በብቃት ተወዳድሮ ሥራ የማግኘትና የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው
እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል:: ይህ መመሪያ ቅሬታ ያሳደረባቸው ነዋሪዎቹ ልጆቻችን በማንነታቸው ምክንያት እየተገለሉ፣ ተምረው ስራ ማግኘት አልቻሉም ሲሉ ተናግረዋል:: ‹‹አሰራሩ
ልጆቻችንን ወደ አልተፈለገ የሱስ ተግባር ውስጥ እያስገባቸው ነው፤›› ብለዋል::

1996 ዓ.ም. ላይ በቻርተር ደረጃ ከተመሰረቱት ሁለት የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ድሬዳዋ አንዷ ስትሆን፣ በዘጠኝ የከተማ ቀበሌዎች እና በ38 የገጠር ቀበሌዎች የተዋቀረች ናት:: በ1999 ዓ.ም. የሀገር ዐቀፍ
የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን ባጠናቀረው የህዝብ ቆጠራ መረጃ መሰረት፣ የድሬዳዋ ህዝብ ብዛት 341 ̦834 እንደሆነ ተመዝግቧል:: ከተማዋ ኢትዮ-ጂቡቲን በኢኮኖሚና ማህበራዊ በማስተሳሰር፣ የወጪ እና የገቢ ንግድ መተላለፊያ
እንደሆነች ይነገርላታል:: ሆኖም፣ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የሚሰራበት የ40-40-20 መመሪያ ነዋሪዎች ላይ ቅሬታ ከማሳደሩም በላይ የከተማዋን ዕድገት ወደ ኋላ እያስቀረው እንደሆነ የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልፃሉ::
ስለ ጉዳዩ ለማጣራት በስልክ ልናነጋግራቸው የደወልንላቸው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን፣ ‹‹አሁን በከተማችን በተስተዋሉ ችግሮች ምክንያት ስብሰባ ላይ ስለሆንን ልናነጋግራችሁ አንችልም፤›› የሚል መልስ ሰጥተውናል::

– ረቂቅ ተሠራ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*