የኦዴፓ እና ኦነግ ውዝግብ ሃገርን ሊበትን እንደሚችል ተገለጸ

"ኦሮሞ  ገር መምራት አይችልም በሚል ሴራ እየተሰራ ነው" ኦዴፓ "ራሳችንን እንከላከላለን እንጂ አንተኩስም" ኦነግ

ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ በኦሮሚያ ክልል በሚታዩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ውዝግባቸው ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል:: የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታህሣሥ 12/2011 ዓ.ም. በወቅታዊ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በኦሮሞ መካከል የሚደረግ የትጥቅ ትግል አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለው መሆኑን በማመን ሆደ ሰፊነት ማሳየቱን ገልጿል::

ኦዴፓ፣ በሰላማዊ መንገድ ትግል ለማድረግ የተገባው ቃል ፈርሶ፣ ትዕግስትን እንደ ፍራቻ በመመልከት ትናንት ሲዘርፉ፣ ሲያሰቃዩ እና ከስልጣን የተባረሩ ከህዝቡ በዘረፉት ገንዘብ ተላላኪዎችን በመግዛት፣ ኦሮሚያን እና ኦሮሞን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እየሰሩ ነው ብሏል::

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው፣ የመከላከያ ሰራዊት የኦነግ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ መስፈሩ፣ ግጭት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን በተመሳሳይ ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል:: በዚህ ምክንያት፣ ሰሞኑንም በምዕራብ ወለጋ በመከላከያ ሠራዊት እና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች መፈጠራቸውን አቶ ዳውድ ገልጸዋል:: ኦነግ፣ ‹‹ራሳችንን እንከላከላለን እንጂ አንተኩስም›› ብሏል:: የኦነግ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ፣ የቀድሞው የኦነግ አመራር አባል ጄኔራል ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ጉዳይ ኃላፊ ሆነው መሾማቸው ጥርጣሬ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል::

ኦዴፓ በበኩሉ፣ ‹‹ለህዝብ የተገባው ቃል እንዳይሳካ የውስጥና የውጭ የጥፋት ኃይሎች፣ ‹ኦሮሞ ሀገር መምራት አይችልም› በሚል ጋብቻ ፈፅመው፣ ሴራ ሸርበው ሌት ተቀን እየሰሩ ነው:: ጠላቶች በሸረቡልን ሴራ በቂ እውቀት የሌለው የእኛው ሰው፣ ደቦ በመውጣት በሰላማዊ ህዝብ ላይ ጭካኔ በተሞላበት የሽብር ጥቃት በፈንጂ ህይወታቸው እያለፈ፣ ሴቶች እየተደፈሩ፣ ንብረት እየወደመና የህዝቡ የመንቀሳቀስ መብት እየተገደበ ነው:: የኦዴፓ አመራሮችና የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትም በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እያለፈ ነው›› ብሏል::

በተለይም፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ትምህርት እንዲቋረጥ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ያለው አዴፓ፣ ግብይት ሙሉ በሙሉ በመቆሙ ባለሀብቶች የሚሰሩት ስራ እየተቋረጠ፣ ከባንክ የተበደሩትን መመለስ አቅቷቸው ንብረታቸው እየተወረሰ መሆኑን ገልጿል::

ኦነግ፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ የደህንነት አገልግሎት እና ፖሊስ አንድን ፓርቲ ሲያገለግል እንደነበር በመጥቀስ፣ የፀጥታ ኃይሉ ገለልተኛ እንዲሆን ከመንግስት ጋር ስምምነት እንደነበር አስታውቋል:: ‹‹የኦነግ ሰራዊት በፀጥታ መዋቅር እንዲካተትና፣ ይህንን የሚሰራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ከስምምነት ተደርሷል›› ብለዋል አቶ ዳውድ ኢብሳ:: ኦነግ፣ ከመንግስት የተገባው ስምምነት እየተጣሰ እንደሆነ ገልጿል:: በስልጠና ላይ ያሉ የኦነግ ሰራዊት አባላት ፣ በአመራር አባላት እንዲጎበኙ አለመፍቀድ አንዱ የአለመግባባት ምክንያት መሆኑንም አቶ ዳውድ ጠቁመዋል::

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች፣ የኦነግ ታጣቂዎች ናቸው በተባሉ አካላት በርካቶች መገደላቸው ተነግሯል:: ኦዴፓ፣ ‹‹የመንግስት መስሪያ ቤቶችን በመዝጋት፣ የጦር መሳሪያ በመዝረፍ፣ አመራር ደብድቦ በማባረር፣ ዜጎችን በመዝረፍ፣ በመግደል፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በክልሉ ያለውን እንቅሰቃሴ የማደናቀፍ ስራ ተሰርቷል›› ብሏል:: ‹‹እኛ ከተጋጨን በመሐል ህዝቡ ይጎዳል በሚል ታግሰን ነበር፤›› የሚለው ኦዴፓ፣ ‹‹ጥፋቱ ከቀጠለ የህዝብ እልቂትና የሀገር መበተንን ያስከትላል፤›› ብሏል::

ኦዴፓ፣ የጥፋት ኃይሎች ያላቸው አካላት በተቀናጀ መንገድ የሚሸርቡትን ሴራ አክሽፎ የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ፣ ማንኛውንም አይነት እርምጃ ለመውሰድ መወሰኑን አስታውቋል:: ለዚህም፣ የኦሮሞ ህዝብ፣ ወጣቶች፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ብሄራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል፣ “አባ ቶርቤ” በሚል ተደራጅተው ዜጎችን፣ የመንግስት ባለስልጣናትንና የፀጥታ ኃይሎችን ሲገድሉና ሲያስገድሉ ነበር በሚል የተጠረጠሩ ከ15 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል:: ተጠርጣሪዎቹ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸውና በደምቢዶሎ፣ ነቀምትና ሰሜን ሸዋ በዜጎች ላይ ግድያ ሲያቀነባብሩ የቆዩ ናቸው ተብሏል::

በተያያዘ ዜና፣ በኦሮሚያ ክልል ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር ተያይዞ 29 ንጹሃን ሰዎች እና ሁለት የዞን መምሪያ ኃላፊዎችን ጨምሮ፣ 12 የፖሊስ አባላት መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል:: በተጨማሪም፣ 77 የፖሊስ አባላትና 40 ሚሊሻዎች መቁስላቸው ተገልጿል:: በቄለም እና ምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች 2072 ክላሽንኮቭ መሳሪያዎች ከፖሊስ ተዘርፈዋል:: ኮሚሽኑ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ለተከሰቱት ችግሮች ተጠያቂዎች የኦነግ ታጣቂዎች ናቸው ብሏል::

በተያያዘ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የኦነግ ታጣቂዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ በተለይም አማራና ሌሎች ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች ላይ የከፋ በደል እየፈጸሙ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ለበረራ ገልጸዋል:: ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ ታጣቂዎቹ በቀረጥ መልክ ከአንድ ሰው እስከ 50 ሺህ ብር ያስከፍላሉ፤ ሴቶችን አስገድደው ይደፍራሉ::

በሌላ በኩል፣ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በአካባቢው የፌድራል ፀጥታ ኃይሎች እንዲገቡና ሰላም እንዲያረጋግጡ መወሰኑን ተከትሎ፣ የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ቢሰማራም በተደጋጋሚ መንገዶች መዘጋታቸው እንቅስቃሴውን አዳጋች እንዳደረገበት ለማወቅ ተችሏል::

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*