አማራነት እና ኢትዮጵያዊነት – በሲሳይ ታምራት (በባ/ዳር ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)

የአማራ ሕዝብ ዘውጋዊ ማንነቱን መሠረት አድርጎ በመደራጀት መንቀሳቀስ እንዳለበት ተገንዝቦ በልዩ ልዩ መንገድ በመደራጀት ላይ ይገኛል፡፡ የአማራው መደራጀት ያልተዋጠላቸው አካላት በበኩላቸው በዚህ ሕዝብ እና ሕዝቡን እንወክላለን በሚሉት ድርጅቶች (አመራሮች) ላይ መጠነ-ሰፊ የስም ማጥፋትና የማሸማቀቅ  ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ምንም ዓይነት የሥነ-አመክንዮ ሕግን ያልተከተለ እና የሐሳብ ልዩነትንና ብዝሃነትን የሚቃረን ከመሆኑ አንጻር የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ወደ ጽንፈኝነት ጥግ የሚገፋ በመሆኑ ከወዲሁ መልክ መያዝ ይገባዋል፡፡

ማንኛውም ኹነት የሚከናወነው በቦታ እና ጊዜ ተወስኖ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች ማለትም ቦታ እና ጊዜ የማይገዙት ኹነት በምድራችን ላይ ፈልጎ ማግኘት በጣም የሚከብድ ብቻም ሳይሆን፣ የሚቻልም አይደለም፡፡ በመሆኑም ማንኛዉም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ወዘተ ኹነቶች የሚተነተኑት እነዚህን ማለትም ቦታ እና ጊዜን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በርግጥ፣ ትናንት የነበረ ኹነት ዛሬ ላይ ላይኖር ይችላል፤ ትናንት ላይ ያልነበረ ነገርም ዛሬ ላይ ሊኖር ይችላል፤ በተመሳሳይ ዛሬ ላይ የነበረ/ያልነበረ ኹነት ነገ ላይ ሊኖር/ላይኖር ይችላል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኹነቶች በቦታና ጊዜ (space and time) የተገደቡ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲሁም በተከታታይ የለውጥ ጉዞ (continuous flux) ውስጥ መሆናቸውንም ነው፡፡ ማንኛውም ቁስ አካል ከመሬት ስበት ሕግ (the law of gravity) ነጻ እንደማይሆን ሁሉ፣ በተመሳሳይ ማንኛውም ክስተት ወይም ክንዋኔ ከዚህ ተፈጥሯዊ ከሆነው የለውጥ ሕግ ነጻ መሆን አይቻለውም፡፡ ለውጥ አዲስ ነገር (ጠቃሚ ወይም ጎጂ) ይዞ የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊም ነው፡፡ ዴሞክራሲ ደግሞ የተለያዩ ምርጫዎችንና (choices ) እነዚህን ምርጫዎች  የመምረጥንም መብት ይዞ ብቅ ይላል፡፡ በዚህ የተነሳ የለውጥን መኖር አብዛኛው የሰዉ ልጅ በአወንታዊ ጎኑ ይቀበለዋል፡፡

እንደሚታወቀው የአማራ ሕዝብ በተለይ ለባለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት  እስከ አሁን ድረስ በየትኛዉም ግለሰብ ወይም ቡድን  ከዚህም ከዚያም እየተነሳ እንደ ኳስ ሲጠለዝ የነበረ፣ አመድ አፋሽ ሆኖ የቆየ ሕዝብ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ትናንት እና ከትላንት በፊት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ የኢትዮጵያ አንድነትን ሲሰብክ፣ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያልክ በቀን ሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ሃያ አራት ጊዜ የምትለፈልፈው፣ ኢትዮጵያን የፈጠርኳት እኔ ብቻ ነኝ ለማለት ነው፤” ሲባል፣ “የአማራና ትግሬ ለማኝ አብረው መለመን እንኳን አይችሉም፤”፣ “የአያትና ቅድመ አያቶችህን እናት ጡት የቆረጠልህ አማራው ነው፤” ዓይነት የበሬ-ወለደ ትርክቶችን በመስበክ የአማራ ሕዝብ በሌሎች ወንድሞች እና እህቶች እንዲጠላ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም አማራው ቀድሞ ከተቀመጠበት የቀኝ ጠርዝ ወደ ግራ እንደ ኳስ ሲጠልዙት “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ፤” በሚለው የአበው ብሂል በመመራት ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አይቶ እንዳላየ ሆኖ እና የውስጥ ሕመሙን ዋጥ አድርጎ በሆደ-ሰፊነት ብዙ ዘመናትን አሳልፏል፡፡

ይሁን እንጅ ውስጣዊ ሕመሙን ሌሎች ወንድሞችና እህቶቹ ሊረዱለትና ከሕመሙ ሊታደጉት አልቻሉም፡፡ በዚህ ወቅት ይህ ሕዝብ ቆም ብሎ ራሱን በራሱ ፈተሸ፤ የት ላይ ነበር የተሳሳትኩት ብሎ ራሱን በጥልቀት ጠየቀ፤ ውሳኔ ላይም ደረሰ፡፡ የራሴ ማረፊያ ቦታ (ጎጆ) ያስፈልገኛል የሚል፡፡ ይህንንም የራስ ማረፊያ ቦታ አማራዊ ማንነት ወይም የአማራነት መንፈስ (the Amhara spirit) ብሎ ጠራው፡፡ በዚህ መሠረት፣ ይህ ሕዝብ በአማራነት ማንነቴ ላይ ቆሜ፣ ለምወዳት ሀገሬ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊን የድርሻየን መወጣት እችላለሁ በማለት ተንቀሳቀሰ፡፡ በአማራነት መንፈስ ተደራጅቼና ጠንክሬ፣ የተደራጀች ኢትዮጵያን ከሌሎች ወንድምና እህቶቼ ጋር ተባብሬ እገነባለሁ ብሎ ወሰነ፡፡ ነገር ግን ይህ ውሳኔው በአንዳንድ ወገኖች በበጎ ጎኑ አልታየም፡፡

አማራውን ትናንት ከነበረበት ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት በኀይል ገፍትረው የአማራ ብሔረተኝነት ላይ አስቀመጡት፡፡ ዛሬ ደግሞ ከግራ ጠርዝ ወደ ቀኝ ጠርዝ እንደለመዱት እንገፍትርህ (በእግር ኳስ ቋንቋ አገላለፅ እንጠልዝህ)፣ ወይም የጊዜን መለወጥ ባላገናዘበ መልኩ፣ በነበርክበት ጠርዝ ላይ ቆይ አሉት፡፡

የሰው ልጅ እጣ-ፈንታውን (destiny) ያለምንም ውጫዊ ጣልቃ-ገብነት በራሱ ፈቃድና አቅም ሊያረጋግጥ የሚችል ፍጡር ነው፡፡ ምክንያቱም የሰዉ ልጅ ብቸኛው የአእምሮ ባለቤት በመሆኑና ማሰብና ማሰላሰል በመቻሉ፣ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን የሚያውቅ፣ ልዩ ፍጡር እንጅ የሰው ልጅ የአእምሮ ውጤት እንደሆነችው ኳስ ባለመሆኑ፣ ማንኛውም ያላዋቂ እግር ስላለው ብቻ ከዚያም ከዚህም እየተነሳ ሊጠልዘው የሚገባ ባለመሆኑ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ እውነታም ከዚህ  የተለየ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ኳስ እግር ባለው ሁሉ ስትጠለዝ ለምን? ብላ መጠየቅ አትችልም? ቢሉ፣ ልክ እንደ ሰው ልጅ አታስብም፣ አታሰላስልም፡፡ በተቃራኒው የሰዉ ልጅ (በትክክል ከተጠቀመበት) ይህንን ለማድረግ  የሚያስችል አእምሮ የሚባል ውድ የሆነ ሀብት ስላለው፣ ለምን? ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ የሰው ልጅ ይህን ተግባር ማድረግ ካልቻለ፣ ከሌሎች እንስሶች የተለየ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ የለም፡፡

በመሆኑም አማራው ለምን? ብሎ የሚጠይቀው፣ እነዚህ የጠርዘኛ አሳቢዎች ጥያቄየን ይመልሱልኛል በሚል የሞኛሞኝ ፍላጎት አድሮበት ሳይሆን፣ ይልቁንም ለምን? ብሎ የሚጠይቅ የሰው ልጅ ብቻ እንጂ፣ ነገር ግን በሰው ልጅ ፍላጎት የተሠራ ኳስ አለመሆኑን በሚገባ ለማሳየት ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ የአማራ ሕዝብ ሌላው ኢትዮጵያዊ በፍላጎቱ ልክ እንደ ኳስ የሰራውና በፈለገው ቦታና ጊዜ የሚጠልዘው ኳስ አይደለም ለማለት ነው፡፡ ዕውቁ ጀርመናዊ ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት “የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ሊከበር የሚገባ ልዩ ፍጡር እንጅ የሌሎች መጠቀሚያ ወይም ግብ ማሳኪያነት የሚያገለግል የጥሬ ዕቃ አይደለም፤” ሲል እንዳስገነዘበው፣ የአማራ ልጆችም የአማራ ሕዝብ የማንም ቀቢፀ-ተስፋ ግብ ማስፈፀሚያ ጥሬ-እቃ አይደለም ብለው ተነስተዋል፡፡

ትናንት ላይ አማራነትህን በትክክል ሳትረዳ፣ ደጋግመህ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የምትል፣ “ትምክህተኛ”፣ “ነፍጠኛ”፣ “የድሮው ሥርዓት ናፋቂ” ወዘተ፣ ሲባል፣ ዛሬ ደግሞ የአማራነት ማንነቴን በሚገባ ተረድቼና አጥብቄ ይዤ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ ጋር በመተባበር እገነባለሁ ብሎ ሲል “ጽንፈኛ”፣ “ጨቋኝ”፣ “የኢትዮጵያ ጠላት”፣ “አክራሪ”፣ ወዘተ፣ የሚል ያላዋቂ ምክር አይሉት ማወናበጃ ይወርድበታል፡፡ እንዲያው እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አማራው ዘውጌ ብሔርተኛ መሆኑና በብሔር መደራጀቱ ትክክል አይደለም ቢባል እንኳን፣ የተሳሳተው የአማራ ሕዝብና የአማራ ብሔረተኝነት አቀንቃኞች ሳይሆኑ፣ ይልቁንም ወደ አማራ ብሔረተኝነት ገፍትሮ የጣለው፣ አማራውን ቢቻል ከኢትዮጵያ ምድር ማጥፋት፣ ካልተቻለ ደግሞ በተከታታይ ማዳከምና ማመናመን የሚፈልግ ወገን አይደለምን?

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ማወቅና ፖለቲከኛ መሆን ብሎም ሥልጣን ለመያዝ ሲባል፣ የአማራውን ጭንቅላት እንደተናዳፊ እባብ መቀጥቀጥ ግዴታ ነው ያለው ማን ይሆን? የአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥትን ለመቆናጠጥ ከሁሉም የዓለም ክፍል በአራቱም አቅጣጫ ስትመጣ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግለው የአማራ ሕዝብ ብቻ ነው ያለውስ ማን ነው? ለምን ይሆን ግን የአማራው ጥጋብና ብልጽግና እንጂ፣ ድህነቱ፣ ረኀቡ እና ስቃዩ ለሌሎቹ የማይታየው? ምን ዓይነት ሰው ይሆን በአማራ ደምና አጥንት ብሎም መቃብር ላይ ዘላለማዊ የሆነ ቤቱን መገንባት የሚፈልገዉ? አማራው ሲሰባሰብና ሲደራጅ፣ ሌላው የሚበታተን የሚመስለውስ ለምን ይሆን? አማራው በአንድ ድምጽ እኔ ኢትዮጵያዊ አማራ ነኝ ብሎ  ሳይጨርስ፣ አርባ አጋንንት እንደሰፈረበት ሕመምተኛ መጮህ ምን ይባላል? ቀደም ብየ እንደገለጽሁት ይህንን ሁሉ ጥያቄ የምጠይቀው አንድም ታላቁ የሥነ-ምግባር አባት ሶቅራጠስ the unexamined life is not worth living እንዳለው፣ እኔም በዚሁ አተያይ በጽኑ ማመኔ፤ ሁለትም እንደዚህ ዓይነት ጠያቂ አእምሮ ያለው ሰው፣ የማንም ሰው ልዩ ምክር ወይም እርዳታ ሳያስፈልገው የራሱን ዕድል በራሱ ኀይል መወሰን እንደሚችል ለማስታወስ ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ሲቀመጥ የአማራ ሕዝብ የራሱን ዕጣ-ፈንታ በራሱ በተባበረ ክንድና የራሱን አእምሮ ተጠቅሞ ይወስናል ለማለት ነው፡፡

ሐቁን እንነጋገር ከተባለ በመጀመሪያ የአማራነቴን እውነታ ዕውቅና ለመስጠት ያልፈለገ (በርግጥ የእኔን ማንነት ማንም ሊሰጠኝና ሊነፍገኝ ፈጽሞ አይችልም፤ አልፈቅድለትምም) ግለሰብ ወይም ቡድን የኢትዮጵያዊነቴን ዕውቅና ሊሰጠኝ ፈጽሞ አይችልም፡፡ ጠንካራና የተከበረች ኢትዮጵያም ካለጠንካራና የተከበረ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ሶማሊ፣ ወዘተ ስብስብ እና ትብብር ልትገነባ አትችልም፡፡ በመሆኑም አማራው ሲደራጅና ሲሰባሰብ ሌላው የሚበረግግ ከሆነ፣ የዚህ ዋናው ችግር የአማራው መደራጀት ሳይሆን የተመልካቹ ሌሎችን ከመጠን በላይ መፍራት (extereme pranoia) አባዜ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊና ግዴታም ነው፡፡

በአጠቃላይ እኛ ልደራጅ አንተ ግን ድርቅ እንደጎዳው በቆሎ ተተብናችሁ ኑሩ ወይም ሰነፍ እረኛ እንደሚጠብቃቸው በጎች ተበታትናችሁ እግር የጣለው ተኩላ ሁሉ ይብላችሁ ዓይነት የብልጣብልጥ ምክር በዚህ ሰዓት ምንም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ሁሉም ነገር ተከታታይ በሆነ ለውጥ (all things are in a continuous flux) ውስጥ ነው እንዳለው ሄራክሊተስ፣ ነገሮች ሁሌም ባሉበት አይቀጥሉም፡፡ በመሆኑም የትናንት ኢትዮጵያ በስም ብቻ ካልሆነ በስተቀር ዛሬ ላይ የለችም፡፡ ነገም ላይ አትኖርም፡፡ የሕዝቦቿ ብዛት፣ የምትከተለው የመንግሥት አስተዳደር፣ የትምህርት ደረጃቸው፣ ወዘተ ሁሌም ተለዋዋጭ ነው፡፡  በተመሳሳይ የትናንቱ አማራና የዛሬዉ አማራ በስም ብቻ ካልሆነ በስተቀር አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ እንዲሆንም አይጠበቅበትም፡፡ ለአማራ ሕዝብ “ባለህበት ሂድ!” የሚል ምክር በዚህ ሰዓት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፤ አይገባምም፡፡ ትናንት ተበታትኖ በመኖሩ ለዘርፈ-ብዙ የጥቃት ሰለባ ሆኖ የቆየው አማራ ዛሬ ላይ በመሰባሰብ ለጋራ መብቶቹ መከበር በጋራ ቢሠራ ኹነቱ የተፈጥሮ ሕግን የተከተለ እንጂ፣ ተቃርኖ የለውም፡፡ የአማራ ሕዝብ ባሁኑ ጊዜ ፊቱ ላይ ተደቅነውበት ያሉትን መሠረታዊ የመኖር አለመኖር ችግሮች ለመፍታት መፍትሔው ዶ/ር እሸቱ ጮሌ እንዳሉት  “አንደኛ መደራጀት፣ ሁለተኛ መደራጀት እና ሦስተኛ መደራጀት!” ብቻ ነው፡፡

ይህን ምልከታየን ለማጠናከር አንድ የሉላዊነት (globalization) አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳያ ሆኖ የሚያገለግል አባባልን ከፈረንጆች ልዋስ፡፡ አሜሪካን ሲያስላት መላውን ዓለም ያስነጥሰዋል (When the United States cough, the whole world sneezes) ይላል፡፡ ይህ የሚያሳየው አሁን ላይ በአንድ የዓለም ክፍል የሚከሰት ማንኛውም ችግር፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተቀረው የዓለም ክፍል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር መሆኑን ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያን ሲያስላት በመላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖረውን አማራ ያስነጥሰዋል የሚል ጽኑ አቋም አለኝ፡፡ ምክንያቱም ካለፈው ታሪካችን በተለይም ለባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እንዳየነው አንድ ችግር በአንድ የተወሰነ የኢትዮጵያ ክፍል ከተከሰተ፣ የዚህ ችግር መዘዙ (ገፈታ) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመላው የአገሪቱ ክፍል ከሚኖረው አንድ አማራ ላይ ያርፋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ታዲያ ይህ የሁለገብ ጥቃት ሰለባ የሆነው አማራ ተደራጅቶ ከገጠሙት ችግሮች ራሱን ካልታደገና የዜግነት መብቶቹን ማስከበር ካልቻለ ሌላ ማን ይደራጅ? ማንም!

የትናንቱ አማራ ይከተለው የነበረው ርዕዮተ-ዓለም ዛሬ ወይም ነገ ላይ የግድ እንዲኖር አይጠበቅም፡፡ እንዲሁም ትናንት ላይ አማራውን የገጠሙት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው፣ ዛሬ ወይም ነገ ላይ እንዲኖሩ የግድ አይደለም፡፡ በዚህ መነሻ ሐሳብ ተስማማን ብንል፣ ትናንት የአማራ ሕዝብ ይከተለው የነበረው የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ዛሬ ላይ ቢቀየር፣ ይህ የተፈጥሮ ሕግ ኃጢያት ወይም እብደት ሊሆን አይችልም፡፡ ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ይህ ርዕዮተ-ዓለም አሁን ላይ ይህ ሕዝብ የገጠሙትን ቸግሮች በትክክል እና በተሻለ መልኩ ሊፈታለት ይችላል ወይ የሚለው ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአማራ ሕዝብ ሊከተል የሚገባውን የመታገያ ስልት መምረጥ የሚገባው ችግሮችን በተግባር የተጋፈጠው ማኅበረሰብ እንጅ ሌላ ውጫዊ አካል ሊሆን አይገባም፡፡ ሕመሙን የታመመው ራሱ በመሆኑ፣ ከዚህ ሕመሙ ሊፈወስበት የሚችልበትን መንገድ ወይም የሕክምና ዘዴ በትክክል የሚያውቀው የሕመሙ ሰለባ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ ያዋጣኛል የሚለውን የመታገያ ስልት ሲመርጥ፣ ከውጭ ቆሞ፣ የታመምከውን ሕመም የማውቀው እኔ ስለሆንኩ፣ ሕክምናውንም የማዝዝልህ እኔ ነኝ ማለት፣ ልክ የራስ ምታት ለታመመ በሽተኛ የኩላሊት ቀዶ-ጥገና ማካሄድ አለብህ  ብሎ ማዘዝን ያስከትላል፡፡

ሲጠቃለል አሁን ላይ እየታየ ያለው የአማራ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያን ያፈርሳል፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ብቸኛው መዳኛ የዜግነት ፖለቲካ ነው የሚለው የገደል አፋፍ ፖለቲካ ትርፉ አሁን ላይ ያለውን የተለሳለሰ ወይም ጤናማ የሆነ የአማራ ብሔርተኛ አቀንቃኞችን ሳይፈልጉ ገፍቶ፣ ጽንፍ ላይ እንዲወድቁ ማድረግ ነዉ፡፡ የጽንፈኝነትን አደገኝነት ደግሞ ሩቅ ሳንሄድ ከሕወሓትና ኦነግ መማር እንችላለን፡፡ በዜግነት ፖለቲካ ጽንፍ (ጫፍ) ላይ ቆመን የማንነት ፖለቲካ ኢትዮጵያን ያፈራርሳል ለሚለው የጠርዘኛ አተያይ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው ከጽንፈኝነት ጠርዝ ወደ መሃል ተጉዞ፣ በተቃራነው ጽንፍ ላይ የቆሙትን  የሥነ-አመክንዮ ሕግን በተከተለ መልኩ በመሞገት መሳሳታቸውን ለማሳየት መሞክር፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ባሉበት ጽንፍ ላይ ቆመው በተቃራኒ ጽንፍ ላይ ያሉትን መብት ባከበረ መልኩ ሊያቀራርቡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ውይይትና ክርክር ማካሄድ ነዉ፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ እየታየ ያለውን የዜሮ ድምር ገመድ ጉተታ ፖለቲካ ወደጎን በመተውና ይልቁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን በማስፈን፣ በማንነትና የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች መካከል የሰለጠነ ውይይትና ክርክር በማካሄድ፣ እነዚህን ተጻራሪ ትርክቶች እንዴት አድርገን አቻችለን መሄድ እንዳለብን ማሰቡ ለኢትዮጵያ አገራችን የተሻለ መፍትሔ ነው፡፡

ሲሳይ ታምራት – በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር

 

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*