ወልቃይት የአይቀሬው ጦርነት ግንባር? – በቴዎድሮስ ኀይሉ

የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አነሳስ፣ የህዝባዊ ተጋድሎ መጠን መጨመር እና በዛኛው ጽንፍ የታዩ አጸፋዊ ምላሾች በተጣራሽ መስመር መሄዳቸው፤ በማንነት ጥያቄው አፈታት ላይ ከተስፋ ይልቅ ጨለምተኝነትን አብዝቶ የሚያሸክም ‹ብሔራዊ አደጋ› ሆኖ መታየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በዚህ መጣጥፍ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን በመጠኑም ቢሆን በመዳሰስ ወልቃይት የአይቀሬው ጦርነት ግንባር ስለመሆኗ ማጠየቅ የጸሐፊው ቀዳሚ ዓላማ ነው፡፡ ከሆነለት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ከፍተኛ አመራሮች ስለጉዳዮ ክረትና አሳሳቢነትጎላ ያለ ክብደት እንዲሰጡት እና ከፖለቲካ እና ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች አኳያ ተጨማሪ የሁኔታ ትንተናዎችን እንዲሠሩ ጥቁምታ መስጠትን ያለመ ነው፡፡ የሁኔታዎችን አደገኛነት ለመማመላከት ጉዳዩን በአራት ንዑስ ርዕስ ከፋፍለን እንመልከተው፡፡

ወቅታዊ ሁኔታ!

“አማራን ከወልቃይት ምድር ማጽዳት” የሚል ድርጅታዊ መመሪያ ያነገበው የትግራይ ፋሽዝም አራማጁ ትህነግ፤ ዛሬም  እንደትላንቱ በዘር ማጥራት (Ethnic cleansing) የወንጀል ተግባሩ እንደተጠመደ ነው፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በወልቃይት  ምድር  ዳንሻ ከተማ እና በአካባቢው ላይ የተፈጸመው ግድያ እና የጅምላ እስር የቀደመው የዘር ማጥራት ተግባር ቅጥያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የትግራይ ልዩ ኀይል አማራ (‹አማ›) የሚል የሰሌዳ ቁጥር መላያ ያላቸው ተሸከርካሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል በመጀመሩ  የተነሳ፣ በዳንሻ ከተማ ቅሬታ ባቀረቡ የአማራ ወጣቶች ላይ ተኩስ የከፈተው የክልሉ ልዩ ኀይል ሁለት ታዳጊ ወጣቶችን ሲገድል፤ ሦስት ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ከሰማንያበላይ የሚሆኑ ወጣቶችም (ብዙዎቹ ታዳጊዎች ናቸው) በጅምላ ታፍሰው ወደሁመራ አስር ቤት ተግዘዋል፡፡

በተለየ ሁኔታ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዩች ኮሚሽን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ ከተቋቋመ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ወልቃይት ውስጥ በሚኖሩ አማሮች ላይ የሚፈጸመው ሥርዓታዊ በደል ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በተለይም እንደ ዳንሻ፣ ከተማ ንጉሥ (ማክሰኞ ገበያ)፣ ማይካድራ፣ ቃፍቲያ፣ አዲጋባ፣ ብላንባ፣ ወፍ አርግፍ፣… በተባሉ የከተማ እና የወረዳ ገጠር ቀበሌዎች የሚኖሩ አማሮች መደበኛ ሕይወታቸውን መምራት በማይችሉበት የደህንነት ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ የኢኮኖሚም ሆነ የማህበራዊ ግንኙነታቸው ተገድቦ ያሉት የወልቃይት አማሮች፣ የሚይዟቸው ተሸከርካሪዎች የሰሌዳ ቁጥር ‹አማ› የሚል ከሆነ በወልቃይት ምድር ማሽከርከር እንዳማይችሉ የሚያመለክት የእስር ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል፡፡ በዚህ በትግራይ ልዮ ኀይል እና በክልሉ ትራፊክ ፖሊስ አባላት በጋራ ቅንጅት በከፈቱት ዘመቻ፣ የሰሌዳ ቁጥራቸው ‹አማ› የሚል በርካታ ተሸከርካሪዎች በዳንሻ ከተማ ታስረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአማርኛ ቋንቋ የንግድ ድርጅቶቻቸውን የሰየሙና የጻፉ ነጋዴዎች ወደትግረኛ ቋንቋ እንዲቀይሩ ጫና ሲደረግባቸው የቆየ ሲሆን፤ አሁን ላይ ሁኔታዎች የፋሽስት ድርጊት ተላብሰው ወደንግድ ፈቃድ ነጠቃ (ስረዛ) እንዲሁም ንብረታቸው የአማራ (‹አማ›) የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ያለአንዳች የሕግ አግባብ ወደ ማሰር ደርሷል፡፡ እነዚህ ተግባራት የፋሽዝም ወካይ ምልክቶች ናቸው፡፡ በእስካሁኑ ሥርዓታዊ በደል የወልቃይት አማሮች ልጆቻቸው በቋንቋቸው እንዳይማሩ በመደበኛ ትምህርት ቆይታቸው በግድ ትግረኛ እንዲማሩ መደረጉ፣ በየትኛውም የክልሉ መስሪያ ቤት በትግረኛ የሥራ ቋንቋ በግድ እንዲናገሩ መደረጋቸው፣ የአማራን ባህል ከሚያንጸባርቁ ማኅበራዊ መለዮዎች ይልቅ የትግራይ ባህል በላያቸው ላይ ሲጫንባቸው መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ፋሽዝም ሥርዓታዊ በደል ውስጥ የኖሩትን የወልቃይት አማሮች፣ ከሞት እና ከስደት የተረፉትን በኢኮኖሚ ለማዳከም ከመሬት ነጠቃ ጀምሮ በርካታ ወንጀሎች ተፈጽሞባቸዋል፡፡ የትሕነግ ፋሽዝም ድርጊት ቅጥያ የሆነው የአማራ ሰሌዳ ቁጥር ያላቸው ተሸከርካሪዎች በወልቃይት ምድር እንዳይንቀሳቀሱ የማገድ እና የማሰር ዘመቻው በዳንሻ እና አካባቢው ከፍተኛ ውጥረት አስነስቷል፡፡

ከሁለቱ ታዳጊ ወጣቶች የአደባባይ ግድያ እና ከሦስት ንጹሃን ሰዎች መቁሰል በኃላም የጅምላ እስሩ በመጠናከሩ የከተማዋ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተገትቷል፡፡ ነዋሪነታቸው በዳንሻ ከተማ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች፣ በክልሉ ልዩ ኀይል አባላት ታጅበው የቤት ቁሳቁሶቻቸውን በመያዝ በካንቮይ እና አይሱዙ የጭነትመኪኖች ወደ ሁመራ ከተማ በመሄዳቸው፤ ይህን ተከትሎ ከዳንሻ ከተማ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው ‹‹ዲቪዥን›› ከተሰኘው አካባቢ የቀድሞ የትሕነግ ታጋዮች ከሰፈሩበት ቦታ በመንቀሳቀስ ወደዳንሻ ከተማ መግባታቸው በከተማው ውስጥ በሚኖሩ አማሮች ላይ ስጋት  ፈጥሯል፡፡ “ትሕነግ በከተማው ላይ በሚኖሩ አማሮች ላይ ጭፍጨፋ ሊፈጽም ነው” በሚል ስጋት በርካታ የወልቃይት አማሮች ወደአማራ “ክልል” ጠገዴ ወረዳ-ሶረቃ ከተማ ተሰደዋል፡፡ ይኼ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በዳንሻ ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴዎች አይታዩም፡፡

ወደወልቃይት የሚሄዱ ተሸከርካሪዎች ‹አማ› የሚል የሰሌዳ ቁጥር ካላቸው ማለፍ የማይችሉ በመሆኑ እንቅስቃሴው ተገትቷል፡፡ የሰሞኑን የትሕነግ ፋሽስታዊ ድርጊት ከቀደመው የተለየ የሚያደርገው በትግራይ ልዩ ኀይል እና የትራፊክ ፖሊስ አባላት ጥምረት በዘመቻ መልኩ የአማራ ተሸከርካሪዎች ላይ እቀባ እና እስር መፈጸማቸው ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ በተነሳው ውጥረት በርካታ የትግራይ ተወላጆች ከዳንሻ ከተማ ለቀው መውጣታቸውና በምትኩ የቀድሞ ታጋዮች ከልዩ ኀይሉ እና ሚሊሻ ጎን መሰለፋቸው ትሕነግ በአካባቢው ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም ያለመ አስመስሎታል፡፡

ወታደራዊ እንቅስቃሴ!

ትሕነግ በወልቃይት ደጋማው እና ከፊል ቆላማው ክፍል (ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች) በሚሊሻ እና በልዩ ኀይል አባላት (በተጨማሪነትም በቀድሞ ታጋዮች ተደራቢነት) የታጀበ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደቆየ የሚታወስ ነው፡፡ከዚህ ቀደም ወደ ሁመራ በሚወስደው መንገድ፤ ማይደሌ፣ ዳንሻ፣ በአከር፣ ራዊያን የተባሉ ቦታዎች ላይ የነበሩ የፍተሻ ጣቢያዎች በአቅራቢያቸው ወደካምፕነት በማሳደግ፣ በዚሁ መስመር ላይ ሁለት ተጨማሪ የፍተሸ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል፡፡ በሁሉም የፍተሻ ጣቢያዎች በክልል ደረጃ ይኖራሉ ተብሎ የማይገመቱ የቡድን  የጦር መሳሪዎች እና የወታደራዊ መገናኛዎች (ራዲዩ) አሉ፡፡ በሌላ በኩል ከአማራ “ክልል” ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ያሰፈረው የልዩ ኀይል እና የሚሊሻ ቁጥር መገመት የሚያዳግት ቢሆንም፣ መጠኑን በካምፖቹ እና በቆፈራቸው ምሽጎች ብዛት መረዳት ይቻላል፡፡

ለአብነት የሚጠቀሱት የትህነግ ምሽጎች የሚከተሉት ናቸው፡-

  1. ካዛ ወንዝ አካባቢ
  2. ደብረሃርያ ማይደሌ (ሹመሪ ጀርባ)
  3. ጎቤ
  4. ግጨው
  5. ዳራ
  6. ከተማ ንጉሥ (ማክሰኞ ገበያ) አቅራቢያ
  7. እንዳማርያም፣…

በተለይም በተራ ቁጥር አንድ እና ሁለት ላይ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ የተሰሩ ምሽጎች፣ በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ጊዜ ኢትዮጵያ ሠርታው የነበረ ዓይነት ዲዛይን አላቸው፡፡ በነገራችን ላይ ከወራት በፊት በምዕራብ ጎንደር “የቅማንት ኮሚቴ” እየተባለ ለሚጠራው አካል እና በሥሩ ለተደራጁት  ተወርዋሪ አሸባሪ የቡድኑ አባላት የጦርነት ሎጀስቲክስ ሲያቀርብ የነበረው ሱር ኮንስትራክሽን፣ በከተማ ንጉሥ አቅራቢያ “ሸሐግኔ” በተባለ ቦታ ባለው ካምፕ አማካኝነት በምሽግ ቁፋሮው ጊዜ  አይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

ከዚህ በላይ በተመለከቱት አካባቢዎች ያለው የሚሊሻ ስምሪት አንደአካባቢው ስፋት የጋንታው ብዛት የሚለያይ ቢሆንም በአንድ ጋንታ (እስከ ዐሥራ ስድት የሰው ኀይል) ይመደባል፡፡ የልዩ ኀይሉ እንቅስቃሴ ደግሞ በሻለቃ ደረጃ እንደሆነ፤ በተጨማሪነትም በዋናነት ‹‹ዲቪዥን›› አካባቢ ሰፍረው መደበኛ ሕይወት የሚኖሩ የቀድሞ ታጋዮች እንደአስፈላጊነቱ ተወርውረው የሚደርሱበት (የሚደረቡበት) የኀይል አደረጃጀት እንዳለ የአጠቃላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴቸው (በአካባቢው ታዛቢ እይታ) ግምገማ ያመለከታል፡፡

በአንድ አካባቢ (የገጠር ቀበሌም ሆነ ከተማ) በጋንታ ደረጃ የተደራጀው ሚሊሻ ቁጠሩ ሊጨምርም ሊቀንስም ይችላል፡፡ ለአብነት እንደ ማይደሌ፣ ካዛ፣ ግጨው፣… ባሉ አካባቢዎች በእያንዳንዱ አካባቢ ከአርባ እስከ ሐምሳ አምስት የሚደርስ የጋንታ ብዛት ይኖራል፡፡ በአንድ ጋንታ ሥር ከሚጠቃለሉ (እስከ 16) ሚሊሻዎች ውስጥ አንድ ስናይፐር፣ አንድ የእጅ መትረየስ እና የነፍስ ወከፍ አውቶማቲክ ክላሽኮቭ ከነሙሉ  ትጥቁ (አራት ካርታ ጥይት፣ አራት የእጅ ቦምብ፣ የእጅ ባትሪ፣ ገመድ፣…) በተሟላ ሁኔታ ይዘው ይታያሉ፡፡ በልዩ ኀይሉ በኩል ያለው ትጥቅ በቡድን ደረጃ የጸረ-ታንክ፣ ፀረ-ተሸከርካተሪ መሣሪያዎችን ጨምሮ ሮኬት፣ ሞርታር፣ ብሬል፣ አር.ፒ. ጂ.፣ … በየደረጃው በተዋቀሩ የኀይል አደረጃጀቶች ታጥቀዋል፡፡

የሚሊሻ እና የልዩ ኀይል አደረጃጀት በየራሱ መዋቅር ሽሬ ላይ ላሉ የምዕራብ ትግራይ የኮር አመራሮች የጸጥታ ጉዳዮችን የተመለከቱ ነገሮችን ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ከቀበሌ ገበሬ ማኀበር እስከ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር ድረስ ያለው የሲቪል አስተዳደሩ ሕዝብን መሰብሰብ ጨምሮ የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ ያለጸጥታ መዋቅሩ ይሁንታ አይከናወንም፡፡ ይፋዊ ባልሆነ መልኩ ምዕራብ ትግራይ በክልል ኮማንድ ፖስት ሥር እንደሚመራ ሲቪል ቢሮክራሲው በጽጥታ ኀይሉ መዋቅር ሥር መያዙን እንደማሳያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሃይማኖታዊ ክበረ-በዓላት ሳይቀር “የትግራይ ሕዝብ ራሱን ከታሪካዊ ጠላቶቹ እንዲከላከል”፣ “የትግራይን ዳር ድንበር እንዲያስከብር” ወታደራዊ መመሪያ  ይሰጠዋል፡፡ ይህን ሁኔታ የተከታተሉት የአማራ ክልል ልዩ ኀይል ኀላፊ ብ/ጀኔራል ተፈራ ማሞ ባለፈው ሳምንት ከኢሳት ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ-ምልልስ “ሕወሓት የጦርነት ዝግጅት አድርጓል፡፡ የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት ለመማገድ እየሠራ ነው፤” በማለት እጃቸው ላይ ያለውን መረጃ ይፋ አድርገውታል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ግብዓት ከተደረገው የመረጃ ልውውጥ መጠን አኳያ የሌ/ጀኔራሉ መረጃ  መሬት ላይ ያለውን የትሕነግ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በትክከል ግምት ውስጥ ያስገባ  ነው፡፡

በአጠቃላይ በምዕራብ ትግራ በተለየ ሁኔታ ከአማራ “ክልል” ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከጎረቤት ክልል ጋር ሊካሄድ ይችላል የሚባል ታሳቢ ግጭት ሳይሆን ከአንዲት ሉዓላዊት አገር ጋር ለሚካሄድ መደበኛ ጦርነት የሚደረግ ቅድመ ዘግጅት አስመስሎታል፡፡

ከዚህ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ለጸጥታ መዋቅሩ መጋቢ የሆነ የመረጃ ግብዓት የሚሰጡ፤ ለመረጃ እና የደህንነት ስለላ ሥራ የተመረጡ ቄሶች እና ሴቶች ተመልምለው ወደአማራ ክልል በነጻነት ይገባሉ፤ ይወጣሉ፡፡ ከሴቶቹ ውስጥ “የርቀት ትምህትር ፈተና ለመፈተን፣ ሞጅውል ለመውሰድ፣ ቲቶር፣…” ወዘተ በሚሉ ማኅበራዊ ምክንያቶች ከምዕራብ ትግራይ ተነስተው ጎንደር ድረስ በመግባት የሚፈልጉትን የስለላ ሥራ አከናውነው እንደሚመለሱ ዘግይተውም ቢሆን መረጃዎች መውጣት ጀምረዋል፡፡ በጎንደር አርማጭሆ  እና ጠገዴ (በእርግጥ በመላ አማራ) ባህል ለሃይማኖት አባቶች እና ለሴቶች በመታመን ደረጃ ክብር እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ ይህን አማራዊ ማኅበራዊ እሴት ጠንቅቀው የሚያውቁት የትሕነግ የኮር አመራሮች ለተልዕኮ ሲያሰማሯቸው የነበሩ የሃይማኖት አባቶች እና ሴቶቸ  ያለእንከን ተልዕኳቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ግብዓት መረጃዎችን በመሰብሰብ ሂደት የታየው ተጨባጭ እውነታ በአካባቢው ያሉ የአማራ ክልል የዞንም ሆነ የወረዳ አመራሮች ለዚህ መሰል የጸጥታና ደህንነት የመረጃ ክትትል ትኩረት ሲሰጡ አይስተዋልም፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማደስና ማጠናከር እንደተጠበቀ ሆኖ በየትኛውም ማህበራዊ መለዮ ለእኩይ ዓላማ ሰርገው የሚገቡ አካላትን መንጥሮ ማውጣት የአመራሩ የቅድሚያ ትኩረት ጉዳይ  ሊሆን  ይገባል፡፡ ከጠገዴ ቅራቅር እስከ “ጸገዴ ከተማ ንጉሥ” ድረስ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት፤ ከጠገዴ-ሶረቃ እስከ ዳንሻ ከሃያ ስድስት ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ርቀት አለው፡፡ በእነዚህ መስመሮች በመኪናም ይሁን በእግር በመጓዝ የሚፈልጉትን የመረጃ ስለላ ለማድረግ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የትሕነግ ‹ነጭ ለባሾች› አንድም ጊዜ ሳይያዙ ቆይተዋል፡፡ በአንጻሩ ከአማራ “ክልል” ወደ ትግራይ የሚሄዱ የአማራ ተወላጆች ቀርቶ እዛው ተወልደው ያደጉ የወልቃይት አማሮች መደበኛ ሕይወታቸውን መምራት በማይችሉበት የደህንነት ስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ከየካቲት 21 ምሽት ጀምሮ በዳንሻ እና አካባቢው የታየው የትግራ ልዩ ኀይል ፋሽስታዊ ድርጊት በርካቶችን ከዳንሻ ከተማ ወደ ሶረቃ እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል፡፡ በ24/06/2011 ዓ.ም. ምሽት ላይ ሽመሪ (በዳንሻ እና በሶረቃ [በትግራይና አማራ] መካካል የምትገኝ) ንዑስ ወረዳ ላይ በትግራይ ልዩ ኀይል እና በወልቃይት አማሮች መካከል ጠንከር ያለ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱ በአካባቢው ላለው ውጥረት ተጨማሪ ማሳያ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ትሕነግ በምዕራብ  በኩል ትግራይን ለጦርነት እንዳዘጋጃት የተቆፈሩ ምሽጎች እና በአካባቢው የሚስተዋለው ወታደራዊ እንቅስቃሴና ትንኮሳዎቹ ጩኸው ይመሰክራሉ፡፡

የመከላከያ “ሚና”?

ከመነሻውም ቢሆንም የሕዝባዊ ቅቡልነት እጦት ያለበት የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት፣ በሰሜን ምዕራብ በኩልም ለትሕነግ ወገንተኝነቱ አይሎ ታይቷል፡፡ በአዲሱ የመከላከያ ሠራዊት አወቃቀር መሠረት የምዕራብ ዕዝ እየተባለ የሚጠራው እና ሰፊውን የኢትዮጵያ ክፍል ያካለለው ዕዝ አካል የሆነው 33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር ለአካባቢው ከተመደበ አራት ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ክፍለ ጦሩ ከጎንደር እስከ መተማ እና ከጎንደር-ኹመራ መስመር ድረስ ያለውን ሰፊ ቀጣና እንዲሸፍን ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም በ24ኛ ክፍለ ጦር ሲሠራ የነበረውን ወታደራዊ ሸፍጥ ተከትሎ በቀረበው ሕዝባዊ ቀሬታና ግፊት መሠረት በቦታው የተተካው አዲሱ ክፍለ ጦር በሁለቱ ክልሎች ያለው ሚና የተለያየ ሆኖ ታይቷል፡፡

እንደሚታወቀው በየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት በሁለቱም መስመሮች (ከጎንደር-መተማ እና ከጎንደር-ኹመራ) ዋና መንገድ ወደ ጎን በኩል አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ (ገባ ብሎ) “ቀይ መስመር” በሚል ከተፈቀደላቸው የጸጥታ አካላት ውጭ የጦር ማሣሪያ መያዝ እንደማይቻል መመሪያ ተላልፏል፡፡ መመሪያውን ተከትሎ መከላከያ ሠራዊት በሁለቱም መስመሮች አልፎ አልፎ በተተከሉ ጊዜዊ ካምፖች እና የቅኝት ማዕከሎች ቁጥጥር ሲያደረግ ቢስተዋልም፣ በሦስት ሳምንት ቆይታው አፈጻጸሙ የታዛባ ሆኖ ታይቷል፡፡ በአማራ “ክልል” በኩል በተለየ ሁኔታ ከጎንደር-ኹመራ ባለው መስመር እስከ ጠገዴ እና ምዕራብ አርማጭሆ (አዋሳኝ ድንበር) ድረስ መመሪያው ከሞላ ጎደል ተግባራዊ ቢደረግም በትግራይ ክልል ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ባሉበት ቀጥለዋል፡፡

በመመሪያው መሠረት የጦር ማሳሪያ የሚይዙት አካላት “የተወሰኑ የክልል የተፈቀደላቸው የጸጥታ ኀይሎች” የሚል ቢሆንም፣ መመሪያው ተሸሮ በጋንታ በጋንታ የተደራጁ የትግራይ ሚሊሻዎች፣ በሻለቃ ደረጃ ስምሪት ላይ ያሉት የክልሉ ልዩ ኀይል አባላት እና የቀድሞ ታጋዮች በዋናው መንገድ ዳር እና በከተሞች በስፋት ይታያሉ (ከምሽጎች እና ከካምፖቻቸው ውጭ ያሉ ተወርዋሪ ኀይሎች መሆናቸውን ልብ ይሏል)

‹አማ› የሚል የሰሌዳ ቁጥር ያላቸው ተሸከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ሲታገዱና ከነአሽከርካሪዎቻቸው ሲታሠሩ በአካባቢው ለቅኝት የተሰማሩት የመከላከያ ሠራዊት የመስመር መኮንኖች እና አባላቱ ሁኔታውን እያዩ በዝምታ አልፈዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ የካቲት 22/2011ዓ.ም የትግራይ ልዩ ኀይል ተሸርካሪዎችን በማሰር ቅሬታ ያቀረቡ የወልቃይት አማሮች ላይ ተኩስ ሲከፍት፣ የመከላከያ ሠራዊት ዳር ይዞ ሲመለከት ነበር፡፡ የሁለቱን ሟቾች እና ሦስቱን ቁስለኞች ያናሷቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት መሆናቸው ደግሞ የሠራዊቱን “ሚና” እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት ጣልቃ በመግባት ማስቆም እየተቻለ፣ ሟቾችን እና ቁስለኞችን ለማንሳት መረባረብ ምን የሚሉት የግዳጅ አፈጻጸም እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡

በርካታ ታዳጊ ወጣቶች በአማራነታቸው እና ባሰሙት ድምጽ ከዳንሻ ከተማ በጅምላ ታፍሰው ወደሁመራ እስር ቤቶች ሲጋዙ ዝምታን የመረጠው መከላከያ ሰራዊት፣ ሁለት ታንኮችን በማሰለፍ ከሶረቃ ወደ ዳንሻ የሚወስደውን መንገድ ብቻ ሲጠብቅ ታይቷል፡፡ አካባቢው “ቀይ መስመር” በሚል ወታደራዊ ቃል የተለየ በመሆኑ፣ በዋናው መንገድ አቅራቢያ በሚታዩ የጽጥታ ችግሮች ዙሪያ ጣልቃ በመግባት ግጭቶችን ማብረድ የምድብተኛ ሠራዊቱ ኣባላት ሚና ነው፡፡ ይሁን እንጅ “ትዕዛዝ አልተሰጠንም” በሚል ሰበብ የትግራይ ልዩ ኀይል እና ሚሊሻ በወልቃይት አማሮች ላይ የሚያደረሰውን ጥቃት በቸልታ ማለፍ ከሞራል ተጠያቂነት አያስጥልም፡፡

የአዴፓ አቅጣጫ…

በፖለቲካ ውሳኔዎች መዘግየትና ቁርጠኝነት መጥፋት የተነሳ በርካታ ወቀሴታዎች እየቀረበበት ያለው አዴፓ፣ በወልቃይት ላይ ያለው አቋም የታሪክ ዳራን መሠረት ባደረገ መልኩ በአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ይፈታል የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጅ የትሕነግ አቋም ከሕግ እና ከመርሆች ጋር የሚቃረን በመሆኑ የወልቃይትን ጉዳይ በተለየ የፖለቲካ አቅጣጫ ማየት ተገቢ ነው፡፡ ወልቃይት ወስጥ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መንት ጥሰቶችን ለአገር ውስጥ እና ለዓለም ዐቀፉ ማኅበራሰብ ማጋለጥ ለማንነት አስመላሹ ኮሚቴ ብቻ የሚተው ተግባራት ባለመሆናቸው አዴፓ ጉዳዩን ለፌዴራሉ መንግሥት ከማሳወቅ አልፎ ተቀማጭነታቸውን አገር ውስጥ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አባላት እና ለሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ማድረስ፣ ስለችግሩ አሳሳቢነት ማስረዳት ይኖርበታል፡፡

በአካባቢው የሚስተዋሉ ተንኳሽ ባሕርያት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ከተለዋዋጭ አገራዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች ጋር የሚያስተውል የዕለት ከዕለት ክትትል ማድረግ የሚችል ንቁ ካድሬ እና የጸጥታ ባለሙያ በምዕራብ አርማጭሆ እና በጠገዴ ወረዳ ሊመደቡ ይገባል፡፡ የመረጃ ልውውጦች አሁን እንዳለው በስልክ ከመሆን ተሻግሮ በዕለታዊ የጸጥታ ተግባራት ላይ ባተኮረ መልኩ በጽሑፍ እና በፎቶ ግራፍ ማስረጃዎች የተደገፈ ሊሆን ይገባል፡፡ ከጎረቤት አገር ሱዳን እና ኤርትራ ጋር ያሉ ግንኙነቶች አገራዊ መልካቸው እንደተጠበቀ ሆኖ እንደክልል የሚመለከቱ ጉዳዮች በመኖራቸው የሱዳን እና የኤርትራን ፖለቲካ በቅርብ ርቀት መከታተል፣ የመረጃ ልልውውጥ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ የአዴፓ ሊቀመንበር እና የአገሪቱ ምክልት ጠቅላይ ሚኒስትር ሁለት ጊዜ ሱዳንን ጎብኝታዋል፡፡ በጉብኝታቸውም ከአልበሽር ጋር ተገናነኝተዋል፡፡ በቀድመው ጊዜ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበረው አባዲ ዘሙ እና የትግል ጓዶቹ ሁለት ጊዜወደ ሱዳን እንዳቀኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከሰሞኑ ለሕወሓት የ44ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በካርቱም ከተገኙበት ጉዞ ጋር ሲደመር ደግሞ በሁለት ወር ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ወደሱዳን አቅንተዋል፡፡ ከሱዳን ወታደራዊ መኮንኖች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ይፋዊ ያልሆነና በምሥጢር የሚያዝ መሆኑ በሚቀጥሉት ጊዜያት የወልቃይት ጉዳይ ይበልጥ እየተወሳሰበ እንደሚሄድ አመላካች ነው፡፡ በመንግሥታዊ መዋቀውሩ በኩል (በአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን)የሚደረጉ ጥረቶች እንደተጠበቁ ሆኖ በፓርቲ ደረጃ ጠንካራ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር እና ከጎረቤት አገራት ጋር ማካሄድ ይገባል፡፡ በተረፈ ጦርነቱ አይቀሬ በሆነበት ሁኔታ ‹ዕቅድ – ለ›ን ማሰብ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*