በረራ – በተድላ መላኩ

ዐሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን እስከ ዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መንግሥት ማዕከል፣ ቤተ አምሓራ በሚባለው ጥንታዊ ክፍለ ሀገር (ደቡብ ወሎ) እና ሸዋ ላይ ነበር። በእነዚህ ክፍለ ዘመናት፣ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ዋና ከተማውን በሸዋ የተለያዩ ቦታዎች አድርጓል። አፄ ይኩኖ አምላክ (ንጉሠ ነገሥት፣ 1270-1285) እና የልጅ ልጁ አፄ ዐምደጽዮን በተጉለት ነግሠው እንደነበር ይታወቃል፡፡ እነሱን ተከትለው የነገሡ ታላላቅ ነገሥታት በበኩላቸው፣ በዛሬዋ አዲስ አበባ ምድር ነግሠው ነበር።

በረራ የተሰኘችው ጥንታዊት ንጉሣዊ ከተማ፣ ግራኝ አሕመድ ከልብነ ድንግል ጋር በከፈተው ጦርነት እስኪያፈርሳት ድረስ፣ ለመቶ ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማዕከል ሆና አገልግላለች፡፡ በኋላ ከደቡብ ወደ ሸዋ በፈለሱ ኦሮሞዎች የፈራረሰችው ከተማ ላይ፣ በዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ፈልሰው እንደሰፈሩ ሪቻርድ ፓንክረስትን ጨምሮ የተለያዩ የታሪክ ሊቃውንት ጽፈዋል። በዚህም ምክንያት፣ በረራ እና ሌሎች በሸዋ አካባቢ የነበሩ የአምሐራ ታሪካዊ ቦታዎች ጠፍተዋል።

በረራ ወጨጫ፣ አቃቂ ወንዝ፣ የረር ተራራ፣ ዝቋላ ተራራ፣ ደብረ ዘይትና አዋሽ ወንዝን ጨምሮ፣ ሌሎች ቦታዎችን ያጠቃልል እንደነበር በታሪክ እና አርኪዮሎጂ አጥኚዎች ተረጋግጧል። እነዚህ ማስረጃ የተገኘባቸው ቦታዎች በዛሬዋ አዲስ አበባ ደቡብ ምሥራቅ ክፍል የሚገኙ ናቸው። የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ አምሐራ ነገሥታት ይነግሡ የነበረው፣ ከወጨጫ ወደ ሰሜን በኩል ባለው በመናገሻ ተራራ ላይ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። በዚህም፣ ዙሪያ በመካከለኛው ዘመን የተገነቡ ገዳሞች (ለምሳሌ ዝቋላ) እንዲሁም ንጉሣዊ አብያተ- ክርስቲያናት (እንደ ሰላሌ፣ ጊንቢ፣ ወዘተ.) ይገኛሉ።

በዐሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ፍራንቼስኮ ሱሪያኖ (1445-1481) የሚባል ኢጣሊያዊ ጎብኚ፣ ከካይሮ ተነስቶ የታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከተማ ወደነበረችው በረራ መሄዱን ጽፏል። የአፄ ልብነ ድንግል ቤተ መንግሥትና ዋና ከተማ የነበረችው በረራ፣ አሌሳንድሮ ዞርዚ በሚባል ሌላ አውሮፓዊ ጸሐፊ በዚያን ዘመን ባሰባሰበው መረጃ ላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዙፋን ያለባት ከተማ እንደነበረች ተዘግቧል። ‹ፍራ ማውሮ› የሚባለው ኢጣሊያዊ ካርቶግራፈር በረራን፣ አምባ ነገሥትን፣ ዝቋላን እንዲሁም በጊዜው ሸዋ የነበሩ ዋነኛ ንጉሣዊ ከተማዎችና ቦታዎች ከእነ ቤተመንግሥቶቹ ከአምስት መቶ ዓመት በፊት ካርታው ላይ አስፍሯቸዋል።

ግራኝ አሕመድ መጀመሪያ ካጠፋቸው ከተማዎች አንድዋ በረራ ነበርች። የመናዊው የግራኝ አሕመድ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ዐረብ ፋቂሕ ‹ፈቱሕ አል ሐበሻ› በተሰኘው መጽሐፉ እንደዘገበው፤ አሕመድ ግራኝ በረራ ሲደርስ የአፄ ልብነ ድንግል አባት አፄ ናኦድ ያሠራትን ታላቅ ቤተክርስቲያን እንዳገኘ፤ በውስጧ የነበረውን የወርቅና የብር ክምር ለማውጣትም ሃያ ቀን ያህል እንደፈጀበት፤ የግራኝ አሕመድ ሠራዊት ከትንሽ እስከ ትልቅ ባንዴ ተዝቆ የማያልቅ ሐብት እንዳከማቸ፤ ቀጥሎም በወጨጫ የነበረውን ታላቅ ሕንጻ እንዳቃጠለ እና እንዳወደመ ተጽፏል። ከዚያ ወዲህ አፄ ልብነ ድንግል በረራን መልሶ አልያዛትም፤ ዋና ከተማነትዋ ያበቃው ግራኝ ያጠቃት ጊዜ ነው። እርሱን ተከትሎ፣ ደቡብ ላይ በዋቢና ጁባ ሸለቆዎች በኩል የፈለሱ ኦሮሞዎች ሸዋ ደርሰው የጠፋቸው ከተማ ባለችበት ምድር ላይ ሰፈሩ።

ባደቄ ተብላ የምትጠራ ሌላ ሸዋ ውስጥ ከበረራ ጎን የነበረች ንጉሣዊ ከተማም ነበርች፤ እሷም ከየረር ተራራ በምሥራቅ በኩል ትገኝ ነበር። በባደቄ ንጉሣዊ ከተማ የአፄ ልብነ ድንግል መኖሪያ ቤተመንግሥትና፣ ባልተቤታቸው እቴጌ ሰብለ ወንጌል ያስገነባችው ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ነበር። ይህ ሕንጻ በወርቅ ያሸበረቀ ልዩ ሕንጻ እና ከላይ ያለው መስቀል በቀይ ወርቅ የታነጸ ነበር። የግራኝ ጦር እንዳቃጠለው ‹ፉቱሕ አል ሐበሻ› ላይ ተጽፏል። የአፄ ልብነ ድንግል ሌላው ዋና ቤተ መንግሥት የነበረው አንዱትና በሚባል ቦታ ነበር። ይህም፣ እንጦጦ እንደሆነ ይታመናል። ዐረብ ፋቂሕ እንደጻፈው፣ ይህ የልብነ ድንግል ቤተ መንግሥት የአንበሳ፣ የሰው፣ የንስር ሥዕል በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ፣ ነጭና ሌሎች ቀለማት የተሳሉበት ነበር። ረቂቅ ሥዕላት የነበሩበት ታላቅ ግርማ የነበረው ሰሎሞናዊ ቤተመንግሥት ነበር። የግራኝ ጦር ውስጡ ሲገባ ባየው ነገር እጅግ በጣም መደነቁን ዘግቧል። በመጨረሻም፣ በእሳት አቃጥለውታል። ባደቄም እንደ በረራ በአምሐራው መንግሥት ዳግም ሳትያዝ፤ በፈረሰችው ከተማ ላይ ኦሮሞዎች ሰፍረዋል።

በሸዋ የነበረው የአምሓራ መንግሥት ታሪክ በመካከለኛው ዘመን ዳግም ተጠናክሮ እስከ ግራኝ አሕመድ ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያን ቢመራም፣ መነሻው ግን ከአክሱም ዘመነ መንግሥት የሚጀምር ነው። ለምሳሌ፣ ዋሻ ሚካኤል በኢትዮጵያ ታሪክ ከንጉሥ ኤዛና ዘመን ጀምሮ የነበረ እንደሆነ ይተረካል። በየካ፣ አዲስ አበባ የሚገኝና ከአንድ አለት ተፈልፍሎ በታላቅ የሥነ ሕንጻ ጥበብ የተቀረጸው ጥንታዊ ቅርስ ዋሻ ሚካኤል እስከ አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ዓመት ዘመን እንዳስቆጠረ ይነገራል። ይህን የገነቡት በሸዋ የሚገኘው አማራ ሕዝብ የጥንት አያቶች የነበሩ፣ በደቡባዊ የግዛት ክፍሉ ማዕከል በሸዋ የነበረው የአክሱም መንግሥት ዜጎች ነበሩ። በዋሻ ሚካኤል ውስጥና በዙሪያው የሚገኙ አንዳንድ መዋቅሮች በንጉሥ ኤዛና የአክሱም መንግሥት ሠራዊትና ፈረሰኞች ይሰለጥኑበት የነበረ ስፍራ ነበር፡፡

በሰሜን በአክሱም ከተማ ዙሪያና፣ በደብረ ዳሞ የነበሩ የአክሱም ልዑላን በጠላት ሲጠቁና የአክሱም ማዕከላዊ መንግሥት ሲፈርስ፣ ከእነሱ ውስጥ የተረፉ ልዑላን ወደ ሸዋ ሸሽተው ይኖሩ ነበር። ለምሳሌ፣ አንበሳ ውድም የሚባል የአክሱም ንጉሥ ከዮዲት ጉዲት የጦር ኃይል ጋር ሲዋጋ የነበረው ምሽጉን በእንጦጦ አድርጎ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ከአክሱም ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ በረራ ከተማ ዘመን ድረስ፣ በሸዋ ትልቅ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማዕከል የነበረውና፣ ከዛጔ ሥርወ መንግሥትና ከይኩኖ አምላክ ዘመን ጀምሮ ለስምንት መቶ ዓመት ይፋዊ የኢትዮጵያን መንግሥታዊ ቋንቋ አማርኛ አድርጎ በልሳነ ንጉሥነት ተጠቅሞበታል።

እስከ ዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ፣ ሸዋ ላይ በአምሐራው መንግሥት የምትመራው ኢትዮጵያ ትላልቅ ቤተ መንግሥቶችን ገንብታና ታላቅ ኢኮኖሚያዊ ኃይል አከማችታ ነበር። በግራኝ ጦርነት መንግሥት ከጠፋ በኋላ በኦሮሞ ኃይሎች ሙሉውን ተይዞ ቆይቶ፣ ከነጋሢ ክርስቶስና ልጆች ታላቅ ተጋድሎ ወደ አምሓራ ግዛትነት ተመልሶ ነበር። የነጋሢ ክርስቶስ ሐረግ ያላቸው የሸዋ ንጉሥ (በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት) አፄ ምኒልክ ሙሉ ሸዋን ባስመለሱበት ጊዜ፣ በጥንቱ ዋሻ ሚካኤል ላይ እንደገና ታቦት ገብቶበት ሥራ ላይ ውሎ ነበር።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*