አማርኛ የማይሰሙት የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች

ሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ እና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዲሞክራሲያ አንድነት እንዲመሠረት ያደርጋል በሚል ትርክት የተዋቀረው የአገራችን ፌደራላዊ ሥርዓት የሕዝቦችን መብት የሚደፈጥጥ ሆኗል:: በተለይ እንደ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሐረሪ ያሉት ክልሎች በሕገ- መንግሥት ደረጃ ሕዝቦችን ነባር/የክልሉ ባለቤት እና መጤ/ከሌላ ክልል የመጡ በሚል ደረጃ ከፍለው አስቀምጠዋል:: በዚህ ምክንያት የዜጎችን በራሳቸው ቋንቋ የመማር፣ የመዳኘት፣ የመሥራት እና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት ነፍገዋል:: ለአብነት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንመልከት::

በኦሮሚያ ክልል የሚታየውን ብዝሃነት እና የዐማራ ማንነት ለመዋጥ ክልሉን የሚመራው አካል የፍትሕና አስተዳደር ተቋማትን ተጠቅሟል:: ለአብነት ያህል የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች እንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 141/2000 እና በዚህ አዋጅ የተዋቀሩት የክልሉ ፍርድ ቤቶች የዜጎችን በመረጡት ቋንቋ የመዳኘት መብት የመከጨፈልቁና ከኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓት ጋር አብረው መሄድ የማይችሉ ናቸው:: ከላይ የተጠቀሰው አዋጅ በአንቀጽ 14 በግልጽ እንደደነገገው የክልሉ ፍርድ ቤቶች የሥራ ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ መሆኑን መረዳት ይቻላል:: በዚህ ረገድ የፌደራሉን የሥራ ቋንቋ በዚህ ክልል ላይ መጠቀም አይቻልም ማለት ነው:: የፌደራል ሥርዓትን የሚከተሉ ሌሎች ሀገራትን ልምድ ብንመለከት፣ የፌደራሉ የሥራ ቋንቋ በሁሉም ክልሎች የሥራ ቋንቋ ጎን ለጎን በሥራ ቋንቋነት ያገለግላል::

ነገር ግን ኦሮሚያ ክልል ያሉት ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ክርክር ዜጎች በሚፈልጉት ቋንቋ ሳይሆን ፍርድ ቤቶች በሚሰሙበት ቋንቋ ብቻ ይሰጣሉ:: ከሳሽና ተከሳሽ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ቢሆኑ እና ፍርድ ቤቱ የፍርድ ቤት ክርክራቸውን በአማርኛ ቋንቋ ማድረግ ቢፈልቡ የማይችሉ መሆኑ እና የክስ አቤቱታቸውን በጽሑፍ ቀርቦ የቃል ክርክርና ማስረጃዎች ተሰምተው ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በአስተርጓሚ ብቻ የሚደረግ ሲሆን፣ ይህም የፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማ እንዳይሆን ከማድረግም በላይ የዜጎችን በፈለጉት ቋንቋ የመዳኘት መብት ጨርሶ የሚንድ ነው::

በወንጀል ክርክሮች ላይም ተከሳሽ ሆኖ የሚቀርብ ወገን ከሚቀርቡት ክስ ጀምሮ እስከሚሰጠው ውሳኔ ድረስ በመረጠው ቋንቋ መዳኘት የሚችልበት አግባብ በክልሉ ቦታ የለውም:: በዚህ ረገድ የካናዳን ልምድ ብንመለከት፣ የካናዳ ፌደራል ሥርዓት ኪወቤክ የተባለችው ግዛት የሥራ ቋንቋዋ ፈረንሳይኛ ቢሆንም የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ከሆነው እንግሊዘኛ ጋር በግዛቷ እኩል ሥራ ላይ ይውላል:: በዚች ግዛት በማንኛውም ወንጀል ተጠርጥሮ የሚከሰስ ግለሰብ ከፖሊስ ጣቢያ ጀምሮ በሚኖረው ምርምራ ቋንቋ የመምረጥ መብቱ ተጠብቆ ፍርድ ቤት ሲቀርብም ክሱ የሚቀርብበት ቋንቋ የመምረጥ መብቱ ይሰጠዋል:: በመረጠው ቋንቋ መሠረት ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀርባል:: ማስረጃዎችም በመረጠው ቋንቋ መሠረት ይቀርባሉ:: ውሳኔውም የሚሰጠው ተከሳሽ በመረጠው ቋንቋ እንጅ ፍርድ ቤቱ በፈለገው ቋንቋ አይደለም:: ይህ የሚሆነው መሠረታዊ የሆነውን የተከሳሽ በመረጠው ቋንቋ የመዳኘት መብት ለማክበር ነው::

ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛ የፌደራል መንግሥቱ ቋንቋ በሆነበትና መንግሥት ባመነው እንኳ ከ10 ሚሊዮን በላይ አማርኛን በቋንቋነቱ የሚመርጥ የአማራ ሕዝብ በሚኖርበት ይህ መሠረታዊ የዜጎች በፈለጉት ቋንቋ የመዳኘት መብት አይበርም:: አማርኛ የፌደራሉ ቋንቋ በመሆኑና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማሮች በኦሮሚያ እንደመኖራቸው በጉልህ ምሳሌነት ተነሳ እንጅ የትኛውም ዜጋ በፈለገው ቋንቋ የመናገር መብቱ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ነው:: የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የአማራውን ብቻ ሳይሆን ከአማራው ቀጥሎ በንግድና መሰል የሥራ መስኮች ተሰማርቶና ለረዥም ጊዜ ለኖረው የጉራጌ፣ የትግራይ፣ የሶማሊና ሌሎችም ቋንቋዎች የሚናገር ሕዝብ ላይ ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥታዊ መብትን የደፈጠጡ ናቸው:: ዜጎች ክስም ሆነ መልስ ለማቅረብ ከገቢያቸው በላይ የሆነ ገንዘብ እየከፈሉ ከመገልገላቸውም በተጨማሪ ፍርድ ቤቶቹን የእኔ ናቸው እንዳይሉ ምክንያት ሆኗል:: የግድ ሆኖባቸው በትርጉም የፍርድ ሂደቱን የሚቀጥሉ ዜጎችም ቢሆን በትርጉም የሚሰጠው ፍትሕ እምነት የማይጣልበትና ጥራት የሌለው በመሆኑ ለፍትሕ መጓደል ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል::

ዜጎች በፈለጉት ቋንቋ እንዲዳኙ የተደነገገው ሕገ መንግሥታዊ መብት መከበር ካለበት የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የፌደራል ቋንቋ የሆነው አማርኛንም በአማራጭ ሊጠቀሙ ይገባል:: የዜጎችን መብት ለማስከበርም ሕገ መንግሥቱን የጣሰውና አሁን ፍርድ ቤቶች የሚጠቀሙበት አዋጅ ቁጥር 141/2000 ላይ የተደነገጉት አግላይና ከሕገ መንግሥቱ በተቃራኒ የሆኑ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ያሰፈልጋል:: በተጨማሪም በዚህ አዋጅ የፍርድ ቤቶቹ ቋንቋ ኦሮምኛ ብቻ እንዲሆን የተደነገገውን በማሻሻል ቢያንስ አማርኛም ተጨማሪ የፍርድ ቤት ቋንቋ ሊሆን ይገባል:: ይህን ማድረግ የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ሲሆን ይህን ሕገ መንግሥቱን የጣሰ፣ ከፌደራል ስርዓቱ ያፈነገጠ አሠራር የማይሻሻል ከሆነ ዜጎች ያላቸው አማራጭ በሚኖሩበት አካባቢ ልዩ አስተዳደር ተሰጥቷቸው የፍርድ ቤትን ጨምሮ ሌሎች ሁነቶችን በሚችሉት ቋንቋ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው:: ለአብነት ያህል በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን ተብሎ ዜጎች የፍርድ ቤት ሂደትንም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን በኦሮምኛ ቋንቋ እየተገለገሉ ነው:: የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት መሰረታዊ የሆነውን የዜጎች በቋንቋ የመጠቀም መብት መደፍጠጣቸውን ከቀጠሉ ዜጎች መብታቸውን የሚያስጠብቁበት አማራጭ የራስ አስተዳደር ሊሰጣቸው ይገባል::

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*