ትሕነግ መቼም ቢሆን የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ ረፍት እንዲያገኝ አይፈልግም! (ሲሳይ መንግሥቴ – ዶ/ር)

የትግርይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትሕነግ) ከግንቦት አጋማሽ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ብሔር-ብሔረሰብ ሕዝቦች ነጻ የወጡበትና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን ዕድል ያገኙበት ቀን በመሆኑ በድምቀት ሊከበር ይገባዋል በማለት፣ በክልሉ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ሲለፍፍ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡ የራሱን ወንድም በጠላትነት ፈርጆ በመግደል የሚፎክር፣ የነጻነትን ትርጉም የሚያዛባና ነጻነት የማያውቅ ነጻ አውጭ እንደ ትሕነግ ያለ ቀጣፊና አጭበርባሪ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት በሕይወቴ አይቼ አላውቅም፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተሰጠውን የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እየደፈረና በዕብሪት ተነሳስተው ሰብአዊ መብት የጣሱ፣ እንዲሁም የሀገሪቱን ሀብትና ንብረት በጠራራ ፀሐይ በመዝረፋቸው ምክንያት በሕግ የሚፈለጉ የአመራር አባላቱን ለፌዴራል ፖሊስ አሳልፌ አልሰጥም ባለበት አንደበቱ “ሕገ መንግሥት ይከበር!” ሲል ይሰማል፡፡ ከዚያም አልፎ ራሱ የማያከብረውን የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት በማለትም በአደባባይ ሲያቅራራና ሲፎክር ምንም ዓይነት የሃፍረት ስሜት እንኳ ሲታይበት አይስተዋልም፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው ተከብሮ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚያደርግ “የተዋጣለት ሕገ መንግሥት” ባለቤት ለመሆን የትግራይ ሕዝብ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ልጆቹን ገብሮ ነጻ አውጥቷቸዋል የሚለው ደፋሩና አታላዩ የትሕነግ አመራር፣ የራያና የወልቃይት ሕዝብ ወደ አማራ ክልል መመለስ እንፈልጋለን የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው ምክንያት በጉልበት አፍኖና በሚኖሩበት ቀየ መፈናፈኛ አሳጥቶ ልጆቹንም ሲፈልግ በግፍ እያሰረና ሲያሻውም በጠራራ ፀሐይ እየገደለ ይገኛል፡፡

ይህም የሆነበት ምክንያት ከላይ በአጭሩ እንደተጠቀሰው እነዚህ ሕዝቦች እኛ ትግሬዎች አይደለንም እናም ወደ ሚመስለን ወገናችን አማራ ክልል እንመለስ የሚል ሕጋዊ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በማቅረባቸው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በእጅጉ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” እንደሚባለው ትግራይ ውስጥ በአጠቃላይና ራያና ወልቃይት አካባቢ ደግሞ በተለይ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የትግራይ ልዩ ኀይል በሚወስደው አፋኝ እርምጃ ሳቢያ ሰላም ከጠፋ ዓመታት ተቆጥረው እያለና የግል ፕሬስ ውጤቶችም ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ ተከልክለው ባለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ያለው በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ነው በማለት የትግራይን ሕዝብ በማደናገር ለማታለል ጥረት ሲያደርግ ማስተዋላችን ነው፡፡

የትግራይ መገናኛ ብዙሃንም በትሕነግ ሳንባ ስለሚተነፍሱ በሌለኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች የሚፈጠረውን መለስተኛ ግጭትና ረብሻ በማነፍነፍ አጋነውና አግዝፈው የሚዘግቡትን ያህል ትግራይ ውስጥ በየቀኑ የሚካሄድን የተቃውሞ እንቅስቃሴንም ሆነ በክልሉ ልዩ ኀይል አማካኝነት የሚፈፅመውን አፈናና ግድያ አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተውም እንዳልሰሙ ሆነው ለማለፍ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከመቀሌ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኲሓ ከተማ የእንደርታ ሕዝብ በአንድ በኩል ባለፉት 28 ዓመታት ራሴን በራሴ እንዳስተዳድር አልተፈቀደልኝምና ይኽ ሁኔታ ይብቃ ብሎ በመጠየቅ፣ በሌላ በኩል የመቀሌ ከተማን በማስፋፋት ሽፋን፣ የአካባቢው ተወላጆች በቂ ካሳ ሳይከፈለን ያለአግባብ እየተገፋን ነው በሚል ምሬት የተቃውሞ ሰልፍ ቢወጡምና ችግራቸውን ለሁሉም አካላት ለማስገንዘብ ቢሞክሩም የዜና ሽፋን እንኳ ሊሰጧቸው አልፈቀዱም፡፡

በአጠቃላይ የትሕነግ ነገር በጣም ግራ ያጋባል፡፡ እኛ ትግሬ ስላልሆን በአማራ ክልል ሥር ነው መተዳደር የምንፈለገው በማለታቸው ብቻ እንደጠላት የተቆጥሩት የራያና የወልቃይት ወጣቶች በልዩ ኀይሉ አባላት አማካኝነት ራሱ ገድሎ እርስ በርስ ተጣልተው ነው በእነዚህ አካባቢዎች ሰው የሞተው ሲል ዐይኔን ግንባር ያድርገው ይላል፡፡ የእነዚህን ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ ዕውቅና ላለመስጠት ሲባል መነሻቸው ከባሕር ዳር ነው እንጂ የዚህ ዓይነት ጥያቄ በክልሌ ውስጥ የለም በማለትም ለማጣጣል ይሞክራል፡፡ ለእሱ ታዛዥ የማይሆኑትን ሚሊሻዎች ባንዳና የጠላት ተላላኪ በማለት ከመፈረጅ ጀምሮ ትጥቅ እስከ ማስፈታት የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡ ለምን? ብለው ከጠየቁና በሕግ አምላክ በማለት ከተከራከሩ ደግሞ በጠራራ ፀሐይ ይገድላል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በራያው ተወላጅ መንገሻ በላይ ላይ የተፈፀመው የግድያ ሁኔታም ከዚሁ እውነታ ጋር የተያያዘ ነው፣ ልዩ ኀይሉን በራያና በወልቃይት አካባቢ በብዛት አሰማርቶ የራያንና የወልቃይትን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ይደግፋሉ የሚላቸውን ወጣቶችና ታዋቂ ሰዎች በጅምላ ያስራል፡፡ በጥርጣሬ የሚመለከታቸውን የአካባቢው ተወላጅ ሚሊሻዎችን ትጥቅ ያስፈታል፣ ለምን ብለው ከጠየቁም ያለ ርህራሄ ጥይት ተኩሶ ይገድላቸዋል፣ይኸ ሕገ-ወጥ ሁኔታ ለምን ይፈፀማል? ብለው የጠየቁ ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሽብር በመፍጠር ወንጀል ተወንጅለው በግፍ ይታሰራሉ፡፡ ከሥራም ይታገዳሉ፡፡ ከሁሉም የከፋው ድርጊት ደግሞ የልዩ ኀይል አባላቱ በወሰዱት ሕገ-ወጥ የኀይል እርምጃ ሳቢያ በዚህ ጽሑፍ ላይ በቀረበው ፎቶ ግራፍ የምታዩት መንገሻ በላይ በዚህ አረመኔያዊ ድርጊታቸው ነው ሕይወቱን እንዲያጣ የተደረገው፡፡

የልዩ ኀይሉ አባላት መንገሻ በላይን ጥይት ተኩሰው በግፍ ከገደሉ በኋላ ሬሳው በሥርዓቱ እንዳይነሳ ከመከልከላቸውም በላይ፣ የዋጃ ከተማ ሕዝብ ግር ብሎ በሚወጣበት ወቅት እየረገጠው ሲያልፍ እንዲፈነዳና ተጨማሪ ሰው እንዲሞት ለማድረግ ቦንቦችን በወረቀት በመጠቅለል መንገድ ላይ ጥለው መሄዳቸው ነው፡፡ ይህንንም እውነታ በወቅቱ በቦታው የደረሱት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ማረጋገጣቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ እንዲሁም የትሕነግ ክፋትና ፍጹም አድሏዊነት በሚገባ የሚገለጸው በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የተገደሉ የትግራይ ተወላጆችን፣ ለምሳሌ አምና ነቀምቴና ጣና በለስ ሰሞኑን ደግሞ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተገድሎ የተገኘውን ወጣት መነሻ በማድረግ ፈጥኖ ድርጊቱን የሚያወግዝ መግለጫ ከማውጣቱም በላይ፣ ሬሳቸው በትገግራይ መሬት ሲያልፍ የጀግና አቀባበል እንዲደረግለት በማድረግ የትግራይን ሕዝብ ለማታለልና ለማደናገር የፖለቲካ ንግዱን ሲያጧጧፍ በግልጽ መታየቱ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የራያና የወልቃይት ሕዝብ የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በማንሳትና በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥም እንደግፋለን በማለት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ወጣቶችን እስከ አፍንጫቸው አስታጥቆ ባሰማራቸው የልዩ ኀይል አባላት አማካኝነት ሲገድል ግን ድምጹን ማሰማት አለመፈለጉ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ በግልጽ የሚያሳየው ነገር ለም መሬታቸውን ለራሱ ለማድረግ ፈልጎ የራያና የወልቃይት ሕዝብ የሚገኙበትን አካባቢ የነበረውን የሥልጣን የበላይነት በመጠቀም የትግራይ ክልል አካል እንዲሆኑ ቢያደርግም ከሌላው የትግራይ ብሔር ሕዝብ ጋር በእኩል አይን ለመመልከት ግን ፈቃደኛ አለመሆኑን ነው፡፡

በሌላ አነጋገር፣ ትሕነግ የራያና የወልቃይት ሕዝብ ትግሬ አለመሆኑን ከማረጋገጡም በላይ፣ በእነዚህ ሕዝቦች ላይ በየዕለቱ የሚፈጸመው አፈናና ግድያ መሬታቸውን ለመውሰድ እስካስቻለው ድረስ ሕጋዊና ተገቢ ነው ብሎ እንደሚያምን ከድርጊቱ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ቀደም ሲል የተፈፀመውን ግፍና በደል ትተን ከጥቅምት 11 ቀን፣ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ራያ አካባቢ ብቻ በላማዊ ሰልፍ መብታችን ይከበር ያሉ ከ15 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በትግራይ ልዩ ኀይል ጥይት ተደብድበው ሲገደሉ ከ1000 በላይ የሚሆኑ የራያ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የመንግሥት ሰራተኞች በሽብር መፍጠር ወንጀል ተከሰው ወህኒ እንዲወረወሩ ተደርጓል፡፡

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*