ዋጋ ሊያስከፍለን የሚችለው ዶ/ር ዐቢይን እንደ ነብይ የማየት አካሄድ – ጠበቃ ተማም አባቡልጉ

ለፈው ቅዳሜ የፖለቲካ ድርጅቶች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) አዳራሽ ውይይት አድርገዋል:: በውይይቱ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ አራት የፓርቲ መሪዎች የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል:: ውይይቱን መነሻ አድርጌ አንዳንድ ሀሳቦችን ማንሳት እፈልጋለሁ::

ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ አቋቁሞት የነበረው ሥርዓት ቅኝ አገዛዝ ነው ብዬ አምናለሁ:: ከምኒልክ ዘመን ጀምሮ እስከ ሕወሓት የነበሩት የሀገር ውስጥ አገዛዞች ነበሩ:: ብአዴን፣ ደኢህዴን፣ ኦህዴድ የሚባሉት የሕወሓት ቅኝ አገዛዝ አስፈፃሚዎች ነበሩ:: እነ ዐቢይ አህመድም የሕወሓት ቅኝ ግዛት አስፈፃሚዎች ነበሩ:: አጋር ድርጅቶች የሚባሉት የሕወሓት እንደራሴዎች ናቸው:: በኢትዮጵያ መደረግ የነበረበት አንድ ሀገር ከቅኝ አገዛዝ ሲወጣ እንደሚደረገው፣ ልክ ህንድ ሀገር እንደሆነው ነበር:: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ወይንም ሌሎች ጉዳዩ ያገባናል የሚሉ የሲቪክ፣ የኃይማኖትና ሌሎችም ተቋማት አንድ ላይ ሆነው፣ አንድ ቡድን ተመስርቶ ከእነ ዐቢይ አህመድ ሀገርን የመረከብ ስራ መሰራት ነበረበት:: እነዚህ በአንድ በኩል ሆነው አንድ ቡድን አቋቁመው፣ እነ ዐቢይ ደግሞ ሀገር አስረካቢ ሆነው ለኢትዮጵያ የሚሆን ሕገ መንግስት አበጅተው፣ ምርጫ የሚደረግበትና የኢትዮጵያ ሕዝብም የሀገሩ ባለቤት የሚሆንበት ሥርዓት የማበጀት ነገር ነው መሰራት የነበረበት::

አሁን እየሆነ ያለው እነ ዐቢይ ከውስጥ ገፍተው መጡ በሚል ሌሎቹም ለኢትዮጵያ ይሆናል የሚል ሀሳብ ስላልነበራቸው ወይንም ጉዳዩ ስለቀደማቸው እየተደረገ ያለ ነው:: በእርግጥ በኢትዮጵያ የተለመደ ነው:: ኢሕአፓ በኢትዮጵያ አብዮት ይካሄዳል ብላ ገምግማ የነበረው በ1976 ነበር:: አብዮቱ ግን በ1966 ተካሄደ:: ሌሎቹም በወቅቱ አብዮት አሁን ይመጣል ብለው ስላልጠበቁ እዛው ላይ የመዟዟር ነገር ነው የሚታየው:: ዐቢይን እንደ ነብይ የማየት ጉዳይም የሌሎቹ ዓላማ ቢስነትና ምን ማድረግ እንዳለባቸው የአለማወቅ ጉዳይ የፈጠረውና ዋጋ ሊያስከፍለን የሚችል ነው::

የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው አብዮት ተደናግጦ እየሸሸ የነበረው ሕወሓት ሰኔ 6/2010 ዓ.ም. ስብሰባ በማድረግ እነ ዐቢይን ተክቷል:: እሱም ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት በመሸጋገር ላይ ነው:: የጦር ኃይሉ እንዳለ ነው:: ገንዘቡ እንዳለ ነው:: በሀገር ውስጥ ያለው የበላይነት እንዳለ ነው:: የደሕንነት ሚስጥሮች በጌታቸው አሰፋ እጅ ነው ያሉት:: በሻዕቢያ መንፈስ ተሞልቶ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጣውና አገራችንን ሊያስረክበን ይገባል የተባለው ሕወሓት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ያስነሳበት ሕወሓት፣ አሁንም ከእነ ጉልበቱ እንዳለ በእነ ዐቢይ የተለየ ፍላጎት ስለተተወ፣ አሁን አቅም አበጅቶ ሁላችንንም ከአጥቂነት ወደ ተከላካይነት እየመለሰን ይገኛል:: እነ ዐቢይም የሀገሪቱን የጦር ኃይልና ሌላውን አቅም (ሀርድ ፓወር) ወደራሳቸው ሳያደርጉ፣ ሶፍት ፓወር ከሕዝቡ ተቀብለው ሕዝቡን ወደ ቤቱ መልሰውታል:: ዞሮ ዞሮ አብዮቱ ወደ መቀልበስ ደረጃ እየሄደ ነው ያለው:: ይህም ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለናል::

የተቃዋሚ ኃይሉ ሚና ምን መሆን ነበረበት?

ተቃዋሚ ኃይሉ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ኢትዮጵያን ከቅኝ ገዥው ሕወሓት መረከብ በሚለው ላይ አንድ አቋም መያዝ ነበረበት:: ሕገ መንግስት በማበጀት፣ ተቋማትን በማቆም፣ ለመጀመር አንድ የሽግግር ተቋም ፈጥረው ሀገሪቱን ከሕወሓት በመረከብ ነበር ስራ መጀመር የነበረባቸው:: ይህን ስራ አልሰሩም:: እርስ በእርሳቸው አልተነጋገሩም:: ለሀገርም ይህ ነገር አለን አላሉም:: ‹‹የሕወሓት ቅኝ አገዛዝና አዲሲቷ ኢትዮጵያ›› በሚለው መፅሐፌ የመጨረሻ ክፍል (ምዕራፍ 8) ላይ አቅርቤዋለሁ፣ ምን መደረግ እንዳለበት:: በዚያ መሠረትም አልተሰራም:: የራሳቸውን አዲስ ነገር አላደረጉም:: አሁንም ከዐቢይ አህመድ ስር እየሄዱ ነው:: ይህ ትልቅ ስህተት ነው:: በመሆኑም፣ ሕወሓትና እነ ዐቢይ ወደነበረው ቦታቸው እየተመለሱ ነው:: ይህ ተግባር ኢትዮጵያን ዋጋ ያስከፍላል:: አብዮቱን ይቀለብሳል::

በግሌ፣ ከ1960ው ትውልድ ጋር ችግር የለብኝም:: ሀገር ወዳድ ትውልድ ነው:: የተከተለው ሥርዓት የተበላሸ ሊሆን ይችላል:: በሀገር ፍቅር ግን ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም:: በዓላማቸው ጥያቄ አይነሳባቸውም:: እነ ዐቢይም የ1960ውን ትውልድ ሊወቅሱ አይችሉም:: የ1960ዎቹ ትውልድ ቀጣይ ናቸው:: እነ መለስ የ60ዎቹ ትውልድ ቅራሪ ናቸው:: እነ ዐቢይ በእነ መለስ የተሰሩ ናቸው:: ሶሻሊዝም ለኢትዮጵያ ላይበጅ ይችላል:: ሰዎቹንና መርሃቸውን ለይተን ማየት አለብን:: ማንም ሰው ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መገለል የለበትም:: ሲቀርቡ የነበሩ ሀሳቦች ግን አስደንጋጭ ናቸው:: የትምህርት ቤት ሌክቼር ነበር የሚመስለው:: እነሱ የሚናገሩትን ጉዳይ ከመፅሐፍ ልናነበው እንችላለን:: አሁንም ምን መደረግ አለበት፣ ቀጥሎስ ምን መደረግ አለበት የሚለው ላይ ነው ተቃዋሚዎቹ ስራቸውን ሰርተው እነ ዐቢይንም ማስገደድ ያለባቸው:: እኛ ሀገራችንን ሳንቀበል እንደተለመደው ጥቂት ኤሊቶች ተነጋግረው የሚያደርጉት አይደለም:: የኢትዮጵያ ታሪክ የኢሊቶች ታሪክ ነው:: አሁንም እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ነው:: እነ ዐቢይም ተቃዋሚዎችም ማሰብ ያለባቸው በተለየ መልክ ነው:: አሁን የሚደረገው የእነ ዐቢይ አካሄድ የሕወሓትን ሌላ መልክ የማስቀጠል አካሄድ ነው:: የእነ ዐቢይን አካሄድ አሮጌውን ወይን በአዲስ አቁማዳ ልንለው እንችላለን::

ቆም ተብሎ መታሰብ ያለበት አሁን ነው:: ምክንያቱም እስካሁን የሄድንበት መንገድ ትክክል አይደለም:: ወደምንፈልገው ግብ ሊያደርሰን አይችልም:: በተጨማሪም፣ እስካሁን ሲቀርቡ የነበሩ ሀሳቦች አሉ:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረገው አብዮት አለ:: ሀገርን የመረከብ አብዮት ነው የተደረገው:: ተቃዋሚዎች በዚህ መሰረት ነበር መስራት የነበረባቸው:: አሁን ሊወድቅ ያለውን የሕወሓት አገዛዝ እንዲያንሰራራ የሚያደርግ እንቅስቃሴ መቆም አለበት:: አሁን የሚታየው የተወሰኑ ሰዎችን ስልጣን ላይ ለማቆየት የሚደረግ አካሄድ ነው:: ቆም ተብሎ ከዜሮ ነው መጀመር ያለበት:: ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን የመመለስ አካሄድ እንዴት ነው መሆን ያለበት የሚለው ላይ ታስቦ፣ ሁሉም ተነጋግሮበት በዚያ መሰረት እነ ዐቢይ ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያዊያ አስረክበው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈቅድላቸው ከሆነ ከዜሮ ጀምረው ነው መስራት ያለባቸው:: በፈለገው ስም ሊጠራ ይችላል:: ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር አንድ አካል መቋቋም አለበት:: ይህ አካል ኢትዮጵያን ቅኝ ገዥ ከነበረው ሕወሓትና ከአሻንጉሊቱ መረከብ አለበት ብየ አምናለሁ:: የኢትዮጵያ ሕዝብ መፍትሔም ይህ ነው:: ካለበለዚያ ግን አብዮት ባካሄድን ቁጥር ሂደቱ እየተበላሸ ችግራችን እየባሰ ነው የሚመጣብን::

በዚህ ሂደት ውስጥ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብና የፖለቲካ ቡድኖች ተጠያቂዎች ነን:: ሀገሩ የእኛ ነው:: አንድ መታወቅ ያለበት ግን ፖለቲከኞች አጋጣሚዎችን የሚቃኙት በራሳቸው መንገድ ነው:: ኢትዮጵያዊያን ግን ይህ ሀገር ዘር፣ ብሔር፣ ቋንቋ ሳይለይ አንድ መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለቤት መሆን አለበት:: የሐገር ባለቤት መሆን አለበት ብለን ስንፅፍ፣ ስንናገር ነው የከረምነው:: ብዙ ሰው ሞቶበታል:: ይህ ሳይሳካ ነገሮችን ከመሃል ቆርጠው ሲቀጥሉ ዝም ያልነው ተጠያቂዎቹ እኛው ነን::

አሁን ባለው አካሄድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠያቂ ነው:: እነዐቢይ ዋናውን የሥልጣን መሠረት በሕወሓት እጅ አስቀምጠው የሕዝብን ሶፍት ፓወር ቀምተው ሕዝብ እንዳይሰማን እያደረጉ ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ትጥቅ እየፈታ ነው:: ይህ ሲደረግ ዝም ያልነው ነን ተጠያቂ፤ ሌሎቹማ በሚመቻቸው እየሄዱ ነው:: አሁንም ኃላፊነቱን ወስደን፣ ጉዳዩ ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ አለበት፣ ሀገር ለሕዝብ መመለስ አለበት፣ አንዱ ከሌላው የተሻለ ጥቅም አግኝቶ መደራጀቱ መቆም አለበት ብለን በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገውን መሞዳሞድ ካላስቆምን በስተቀር፣ ሌላ ኃይል አቅም አግኝቶ ይቀለብሳል:: ስለዚህ ሕዝብ ኃላፊነት ወስዶ መንቀሳቀስ አለበት::

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*