የዐቢይ አስተዳደር – የደከመ ወይስ የለገመ? በላይነው አሻግሬ (ጠበቃና የሕግ አማካሪ)

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ ዙሪያ-ገባዋን በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በማኅበራዊውም መስክ ያለችበትን ሁኔታ ውጥንቅጥ ብሎ መግለጽ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁላቸውም እርስ በርስ የተሳሰሩ በመሆናቸው የአንዱ መበላሸት ሌሎቹንም ጉዳዮች አብሮ ማበላሸቱ አይቀርም፡፡

የኢትዮጵያን ታሪክ ከዘመናት በፊትም እንዳስተዋልነው አዲስ መሪ ሲነግሥ (ሲሾም) ብዙ ጊዜ የሚያስቸግረው ንግሥናውን ወይም ሹመቱን አልቀበልም ብሎ ሸፍቶ፣ ጦር ሰብቆ ወይም አልገብርም (አልገዛም) ብሎ የሚያስቸግር ጉልበተኛ ነው፡፡ ከዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ብንነሳ እንኳ ከዐፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ያሉትን ተከታታይ ነገሥታት ጉልበታም ተቀናቃኞች እጅጉን አስቸግረዋቸው ነበር፡፡ እንደሚታወቀው በዐፄ ቴዎድሮስ ላይ ሁሉም የጠቅላይ ግዛት ባላባቶች አንገዛም ብለው አመጽ አድርገው ነበር፡፡ ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዐፄ ዮሐንስ፣ ዐፄ ዮሐንስን ዐፄ ምኒልክ፣ ዐፄ ምኒልክን ራስ መንገሻና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ዐፄ ኃይለ ሥላሴን ደግሞ እነ ራስ ጉግሳ እና ሌሎችም መሣፍንቶች አስቸግረዋቸው ነበር፡፡ ደርግ ንጉሠ ነገሥቱን ገልብጦ ሥልጣን እንደያዘ የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የቀድሞ የጦር መሪዎች፣ የተማሪው አመጽ የወለዳቸው ድርጅቶችና፣ ሌሎች ለቁጥር የሚያታክቱ የብሔር አቀንቃኝ ድርጅቶች ጦር ሰብቀው ጫካ ገብተው ነበር፡፡

እንደ ቀድሞዎቹ አገዛዞች ሁሉ ኢሕአዴግም የመንግሥትን ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እሰከ 2010 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ከጦር ሰባቂ ተቃዋሚ ድርጅቶች አላመለጠም፡፡ ይህ ክስተት የሁሉም የሀገራችን አገዛዞች የመጀመሪያ የአገዛዝ ዓመታት ተመሳሳይ ገጽታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በሕዝባዊ ትግል ቆስቋሽነትና ፊታውራሪነት የተፈተነው ኢሕአዴግ፣ በቀጣይነትም በአባል ድርጅቶቹ መካከል የተደረገው የውስጥ ትግል እና ስውር መፈነቃቀል ዐቢይ አሕመድን የሀገሪቱ ቁንጮ እንዲሆን አደርጎታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከላይ ባጭሩ ያተቀመጠውን፣ ቀደምት ነገሥታትና አገዛዞች ያጋጠማቸውን ዓይነት ጦር የሰበቀ ተቃዋሚ ድርጅት አልገጠማቸውም፡፡ ምክንያቱም ጦር ሰብቀው በኤርትራና በሌሎችም የጎረቤት ሀገራት መሽገው የነበሩትን ተቃዋሚ ድርጅቶች ይቅርታ ተደርጎላችኋል፤ ወደ ሀገር ገብታችሁ በሰላማዊ መንገድ ታገሉ የሚል ጥሪ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ጥሪ መሠረት ሁሉም ታጣቂ ድርጅቶች፣ በግልም በቡድንም ሲታገሉ የነበሩትም  የሀገራቸው በር ወለል ብሎ ስለተከፈተላቸው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር  ገብተዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉትን የአብዛኞቹን ተቃዋሚዎች የሚቃወሙበትን አብዛኞቹን ጉዳዮች ሁሉ በመውሰድ፣ የተቃውሞ ምክንያታቸውን ሁሉ አጠፋባቸው ተብሎ እስኪነገር ድረስ ግስጋሴ አድርጎ ነበር፡፡

ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ያለው ሰላማዊ አጀማመር እና በተለይም ደግሞ ታጣቂ ድርጅቶችን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ ካደረገላቸው በኋላ ወደ ሀገር ቤት መግባታቸው የመንግሥትን ሐሳብ ቀንሶለታልና፣ ከአሁን በፊት ያሉት መሪዎች ያላገኙት አጋጣሚ ነበር፡፡ ቅድመ-ዐቢይ የነበሩት አገዛዞች በተለይ ከታጣቂ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ትግል ብዙ ሕግጋት በማውጣት፣ ብዙ ሀብት እና ጉልበት በማፍሰስ፣ በዚህ ምክንያትም ከሕዝብ ጋር ከባድ ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸው ነበር፡፡ እነዚህን የሀገራችን አገዛዞች ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲወገዱ በማድረግ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያገኙት ዕድል መቼም ቢሆን ዳግመኛ ለማግኘትም የማይታሰብ ነበር፤ የትኛውም መሪ ሊያገኘው ያልቻለው ዕድል ነው፡፡

ነገር ግን፣ ከሚታሰበው በላይ የአብዛኛውን ሕዝብ ድጋፍ ያገኘ የሚመስለው የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ይህን በጎ ዕድል በአግባቡ ሊይዘው አልቻለም፡፡ ተቃዋሚዎችን ሁሉ የሚናገሩትን አሳጥቷቸው የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አንደበት እንዳጀማመሩ ሊሆን አልቻለም፡፡ ከሹመቱ ወዲህ የተከሰቱት ግጭቶች ከሥልጣን የተገፋው የሕወሓት ሴራዎች ይሆናሉ በማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን አስተዳደር ሲታገስ ነበር፡፡ ይልቁንም ችግሮች እየተደራረቡ እንጅ እየተሻሻሉ አለመምጣታቸው ከዛሬ ነገ ይስተካከል ይሆናል ብሎ ተስፋ ሲያደርግ ለነበረው ሕዝብ ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ አልቀረም፡፡

ከዶ/ር ዐቢይ መሾም ወዲህ እጅግ በርክቶ እና ቀደም ሲል ከነበረበት በእጥፍ ጨምሮ የታየው ዋነኛ ጉዳይ የሕዝቦች በማንነታቸው ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀል ነው፡፡ የንፁሐን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል፣ የተፈናቃዮች ጎስቋላ ሕይወት፣ ግጭቶች በየቦታው መቆስቆሳቸው፣ የሕዝብ ሰላምና ደህንነት ለጥቃት ተጋላጭ መሆን፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ መጥፋት፣ እና ሌሎችም በስፋት ታይተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደርም ለነዚህ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ሲሰጥ ወይም ችግሮች እንዳይፈጠሩ ቀድሞ ሲከላከል አይታይም፡፡ ለነዚህ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ወይም ተሥፋዎች እጅግ ሲበዛ ዘገምተኛ ሲሆን ታይቷል፡፡

አስተዳደሩ የክልል መንግሥታት ደከም ብለው ሲታዩ እንዳንድ ጊዜ ደግሞ የፌዴራል መንግሥት ተግባራት በሆኑት ጉዳዮች ላይ እንኳ የሚገባውን ሚና ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ በዚህ ምክንያት የፌዴራል መንግሥቱ ደክሟል፤ የክልል መንግሥታት ደግሞ ጠንክረዋል የሚል ሐሳብ ጎልቶ ይሰማል፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት “እንደሌለ” ነው የሚቆጠረው የሚሉ አስተያየቶችም ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደለም፡፡ በርግጥም የመንግሥት ዋና እና ተቀዳሚ ተግባር የሆነውን የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ያላረጋገጠ መንግሥት፣ በሕዝብ ዘንድ ደክሟል ወይም የለም ቢባል የሚበዛበት አይመስለኝም፡፡

የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር እውን ደካማ በመሆኑ ምክንያት ነው ወይስ በሌላ ምክንያት ነው የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ያልቻለው? የሚለው ጉዳይ በትኩረት ሊመረመር ይገባዋል፡፡ እንደዚህ ጸሐፊ እይታ ግን አሁን የምናያቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ምክንያት የመንግሥት አስተዳደርና መዋቅር ደካማ በመሆኑ ሳይሆን መንግሥት መውሰድ ያለበት እርምጃ ባለመውሰዱ ወይም ራሱ መንግሥት ችግር እንዲፈጠር ምክንያት በመሆኑ ነው፡፡ ይህን አባባል ሊያስረዱ የሚችሉ አንዳንድ ሐሳቦችን እንመልከት፡፡

የሕዝቦች መፈናቀል

ዜጎች በተለያዩ ተፈጥሯዊ (ለምሳሌ በጎርፍ፣ በድርቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ) እና ሰው ሰራሽ (ለምሳሌ ግጭቶች) ምክንያቶች በጊዜያዊነትም ሆነ በቋሚነት የመኖሪያ ቀያቸውን ለቅቀው ሊሰደዱ ወይም ሊፈናቀሉ ይችላሉ፡፡ ብዙ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በተለይ ግጭቶችና የእርስ በርስ ጦርነቶች ሕዝብ እንዲፈናቀል ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት (Norwegian Refugee Council – NRC) የተባለው ዓለም ዐቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት እ.ኤ.አ. በታኅሣሥ 2017 (ታኅሣሥ 2010 ዓ.ም) በአፍሪካ ያለውን የሀገር ውስጥ መፈናቀል አስመልክቶ ሪፖርት አውጥቶ ነበር፡፡ በዚህ ሪፖርት መሠረት እ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ በአፍሪካ ውስጥ በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት 2.8 ሚሊዮን ሕዝብ ሲፈናቀል፣ በተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀለው ሕዝብ ቁጥር ደግሞ 1.1 ሚሊዮን ነበር፡፡ ይህ ማለት ግጭቶችና ጦርነቶች ሕዝብ ከቦታው እንዲፈናቀል የሚያደርጉ ዋና ምክንያቶች ናቸው ማለት ነው፡፡

በዚሁ ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2016 በተከሰቱ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች የሀገር ውስጥ መፈናቀል በድምሩ 643,000 ተፈናቃይ በመያዝ ከአፍሪካ ሁለተኛ ከፍተኛ ተፈናቃይ ያለባት ሀገር አድርጓታል፡፡ ይህ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቶ፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ብዛት ከዓለም ቀዳሚ ሀገር ሆና ትገኛለች፡፡ በጣም የሚያስገርመው ጉዳይ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው የውስጥ ተፈናቃይ ብዛት በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች የምትገኘውና ሕዝቦቿ በስደት አውሮፓን ያጥለቀለቁትን ሶርያን የሚበልጥ መሆኑ ነው፡፡

የሕዝቦች መፈናቀል በኢትዮጵያ አዲስ ክስተት ሳይሆን በተለይ ኢህአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ይበልጥ የተበራከተ፣ እስከዛሬም ድረስ የቀጠለ ድርጊት ነው፤ እንዲያውም ሕዝብን ማፈናቀል የአገዛዙ መገለጫ መስሏል፡፡ በተለይ ደግሞ ብሔር ተኮር ግጭቶች በኢሕአዴግ አገዛዝ ወቅቱን ጠብቆ የሚነሳ በመሆኑ ለሕዝቦች መፈናቀል ዋነኛ ምክንያት አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ቦታ ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የሕዝቦች መፈናቀል ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህን በቁጥር ስንገልጸው፣ ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት (ማለትም እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም ድረስ) የነበረው አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ቁጥር 1.3 ሚሊዮን አካባቢ ነው፡፡ ከዐቢይ አሕመድ ሹመት ወዲህ ግን ይህ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቦ 3.2 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ደርሷል፡፡

የዚህ ሁሉ የሕዝቦች መፈናቀል ዋና ምክንያት ደግሞ “ከክልላችን ወይም ዞናችን ወይም ወረዳችን ውጡልን” የሚል መገለጫ ያላቸው ብሔር ተኮር ግጭቶች ናቸው፡፡ የተፈናቃዩን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር ያደረገውም ይኸው ምክንያት ነው፡፡ በርግጥ ከዚህ ላይ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ የእነዚህ ሁሉ ብሔር ተኮር ግጭቶች ሥረ-መሠረት  ኢሕአዴግ ሕግና ሥርዓት አውጥቶለት እስካሁን ድረስ ሲሰብከው የኖረው ዘረኛውና አግላዩ የብሔር ፌዴራሊዝም እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ የአሁኑ ብሔር ተኮር ግጭቶች ያስከተለው ሕዝብ ማፈናቀል ምክንያቱ የብሔር ፌዴራሊዝሙ ያሰቀመጠው እርሾ መሆኑ ቢታወቅም፣ ይህ መፈናቀል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሹመት ወዲህ እንዴት ሊጨምር ቻለ ብሎ መጠየቅ ተገቢነት አለው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተረከቧት ኢትዮጵያ፣ በተለይ ነፍጥ አንስተው በሚዋጉ ተቃዋሚዎች የምትሰጋ ብትሆነም ነገር ግን ከእርሱ መሾም ወዲህ ይህ ስጋት ፈጽሞ የተወገደ መሆኑንና ከጎረቤት ሀገራት በተለይም ከኤርትራ ጋር የነበረው ፍጥጫ እንደተወገደ ከላይ ተጠቅሷል፡፡ ስለዚህም ለሕዝቦች መፈናቀል ምክንያት የሆኑት ውስጣዊ ችግሮች ናቸው ማለት ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በብሔር ተኮር ግጭቶችና መፈናቀሎች ላይ የሚተነፍሰው ወይም መግለጫ የሚሰጠው ግጭቶቹ እና መፈናቀሎቹ ከተከሰቱ በኋላ መሆኑን በተደጋጋሚ አስተውለናል፡፡ በሱማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራ፣ በትግራይ ክልሎች ልዩ ልዩ ሥፍራዎች መፈናቀል ከተከሰተ በኋላ መንግሥት መግለጫ ሲሰጥ፣ አጣሪ ኮሚቴ ሲያዋቅር፣ ወይም የሐዘን መግለጫ ሲያወጣ እንጅ የሕዝብ ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ቀድሞ የመከላከል፣ ወይም ግጭቶችን የማክሸፍ ሥራ ሲሠራ አይታይም፡፡ ከዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር በነዚህ ክልሎች የደረሰው መፈናቀል መንግሥት ከፌዴራል አንስቶ እስከ ታችኛው ቀበሌ ድረስ ሙሉ የሆነ የጸጥታ መዋቅር ባለበት ሁኔታ ነው፡፡ ታዲያ መንግሥት ይህን ሁሉ መፈናቀል ያስከተለውን ግጭት መቆጣጠር ወይም ማስወገድ የተሳነው አስተዳደሩ ስለደከመ ነው የሚያስብል ምክንያት ይኖር ይሆን? ይልቁንስ የመንግሥት ደካማነት ሳይሆን ልግመት ነው ተብሎ ቢገለጽ ይበልጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህን ሐሳብ የሚያጠናክርልን በለገጣፎ ከተማ የተደረገውን ማፈናቀል እና ከጉጂ የተፈናቀሉትን ጌዴኦዎች ጉዳዮች ማንሳት ይቻላል፡፡

በየካቲት ወር፣ 2011 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ኩታ-ገጠም በሆነችው ለገጣፎ ከተማ ላይ የተደረገውን ቤት የማፍረስ እና ነዋሪዎችን የመፈናቀል ጉዳይ መቼም ቢሆን የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰጡት ምላሽ ደግሞ ይባስ ብሎ በተፈናቃዮቹ ቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሀገር የሚያስተዳድር፣ የግለሰቦችን ማኅበራዊ ትስስር ሲቆጣጠር፣ ሲጠልፍና ሲያዘጋ የሚታይ መንግሥት፣ ከዋና ከተማዋ በጥቂት ደቂቃዎች የጉዞ ርቀት ያለውን የቤቶች መፍረስና የሕዝብ መፈናቀል አልሰማሁም ማለት መለገም እንጅ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ያውም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሊቀመንበርነት የሚመራው ድርጅት በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ የተፈፀመን ግዙፍ ድርጊት!

ከጉጂ ዞን የተፈናቀሉትን የጌዲኦ ተወላጆች ጉዳይም እንመልከት፡፡ እንደሚታወሰው በሰኔ 2010 ዓ.ም. ከጉጂ እና ጌድኦ አካባቢ በርካታ ሕዝብ ተፈናቅሎ ነበር፡፡ ወደ ስምንት መቶ ሺሕ የሚጠጉ ጌዴኦዎች እንደተፈናቀሉም ሪፖርት ሲደረግ ነበር፡፡ በወቅቱም ለሁሉም ተፈናቃዮች ከ118 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ተገልጾ ነበር፡፡ በሂደት ላይ የጉጂ ኦሮሞ ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት እንደተመለሱ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ጌዴኦዎች እንደተፈናቀሉ እና ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ እንዳሉ ከስምንት ወራት በላይ በብዙ ችግርና ሰቆቃ አሳልፈዋል፡፡ በኋላም በማኅበራዊ ትስስሮች በተደረገው ዘመቻ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ አስተዳደር የጌዴኦ ተፈናቃዮችን እንዲጎበኝ እና ጊዜያዊ እርዳታ እንዲያደርግላቸው ተገድዷል፡፡ በወቅቱ በመንግሥት የተሰጠው መግለጫ እስከ መጋት 2011 ዓ.ም ድረስ ምንም ዓይነት የእርዳታ ጥሪ አልቀረበልንም የሚል አሳዛኝ መግለጫ ነበር፡፡ የደቡብ ክልል በጌዴኦ ተፈናቃዮች ላይ ያሳየው ልግመት ከዚህ ላይ አብሮ ሊነሳ ይገባዋል፡፡ እንግዲህ በመቶ ሺ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ አላውቅም የሚል አስተዳደር የለገመ አስተዳደር እንጅ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

የአዲስ አበባ ጉዳይ

እንደዚሁ የአዲስ አበባ ጉዳይ በተለይ ከኦሮሚያ ክልል አካበቢ የሚወጡ መግለጫዎች የከተማዋን ሕዝብና ሌሎችንም የሀገሪቱን ሕዝቦች በእጅጉ ያስቆጣ ድርጊት ነበር፡፡ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ከሕግ ውጭ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት እንዲሾም መደረጉ አንደኛው ሕዝብን ያስቆጣ ድርጊት ነበር፡፡ በመቀጠልም የኦሮሚያ ክልል በተለይም እነ አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ አዲሱ አረጋ አዲስ አበባን በተመለከተ በተለያየ ወቅት ያደረጓቸው ንግግሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እንደ አቶ ለማ ንግግር የአዲስ አበባን የሕዝብ ስብጥር ለመቀየር እየሠራን ነው ማለታቸው፣ አቶ አዲሱ ደግሞ የአዲስ አበባን ባለቤትነት የኦሮሚያ ለማድረግ እየሠሩ መሆናቸው መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ አቋሞች ከሕግ አንጻር ፍፁም ተገቢ እንዳልሆኑ፣ አዲስ አበባ የራሷ የሆነ አስተዳደር ያላት እንጅ ማንም በባለቤትነት የኔ ናት ሊላት እንደማይገባ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ዶ/ር ዐቢይ የሚመሩት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከሕግ ባፈነገጠ መልኩ በአዲስ አበባ ላይ ያሳየው ማንዣበብ የሕዝብን ሰላማዊ ኑሮ የሚያውክ ነበር፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የታየው ከሕግ እና ከአሠራር ውጭ፣ የኦሮሚያ ክልል ጣልቃ ገብነት ደግሞ ሌላው በአዲስ አበባ ላይ የተደረገው ሁከት ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ አዲስ አበባ ከተማን አስመልክቶ በኦዴፓ የተሰጡ መግለጫዎች እና ንግግሮች ሕገ መንግሥታዊ ድርድሮች የሚያስፈልጋቸው ሆነው እያለ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ምን ያህል ከሕግ ያፈነገጡ አካሄዶችን እየተጓዘ እንዳለ የሚያሳይ እንጅ ደካማ ስለሆነ የተፈጠረ ክስተት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአዲስ አበባን ጉዳይ ለማወሳሰብ ጥረት የሚያደረገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ድርጅት በመሆኑ ነው፡፡

የስሜንና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች ቃጠሎ

ባለፉት ወራት በተፈጥሮ ሀብቶቻችን ላይ ከደረሱት ጥፋቶች መካከል በቅድሚያ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በመቀጠል በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደረሰው ቃጠሎ ነው፡፡ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎን አስመልክቶ በተሰጠ አንድ መግለጫ ሆን ብለው ቃጠሎ እንዲነሳ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ የስሜን ተራራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎም ቢሆን ደኖች በተፈጥሮ የሚያጋጥማቸው የተለመደው ዓይነት ቃጠሎ እንዳልሆነ ሲጠቀስ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

 ያም ሆነ ይህ በደኖች ላይ የሚደርሰው ቃጠሎ በሀገራችን ባሉት ጥብቅ ደኖችና ገዳማት ላይ ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ከዚህ ላይ ላነሳው የፈለግሁት ሐሳብ ግን በተለይ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተመለከተ ነው፡፡ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርትና፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት (UNESCO) የተመዘገበ፣ በውስጡ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት እንስሳት እንደ ቀይ ቀበሮ፣ ዋልያ እና ጭላዳ ዝንጀሮ የሚገኙበት፣ ብዙ አእዋፋት እና ዕጽዋትን የያዘ፣ ሥነ ምኅዳር ተጠብቆ እንዲኖር ያደረገ እና ለብዙ ጅረቶች ምንጭ የሆነ ፓርክ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ብርቅዬ ፓርክ እየተቃጠለ በነበረበት ወቅት ፓርኩን የሚያስተዳድረው የፌዴራል መንግሥት ያሳያውን ልግመኛነት ከዚህ ላይ ሊነሳ ይገባዋል፡፡ይኸውም ቃጠሎውን እንዲያጠፉ ከደቡብ አፍሪካ ወይም ከኬንያ ሀገራት ጋር እየተነጋገርን ነው የሚሉት የመንግሥት ማዘናጊያዎች ናቸው፡፡ እንዲያውም ቃጠሎ የሚያጠፉ ሄሊኮፕተሮች መጥተዋል ተብሎ በመንግሥት በኩል መገለጹም አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን የሆነው ሁሉ መንግሥት እንደሰጠው ቃል ሳይሆን፣ የፓርኩ ተቆርቋሪ በሆኑ የአካባቢው ግለሰቦች ጥረት ከእስራኤል እና ከኬንያ የመጡ እሳት አጥፊ ልዑካን ቃጠሎውን አጥፍተው ተመልሰዋል፡፡

በርግጥ ኢትዮጵያ አንድ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር የሌላት መሆኗ አሳዛኝ ቢሆንም፣ ነገር ግን ቃጠሎው ብዙ ጉዳት ሳያስከትል እርዳት ለመጠየቅ በመንግሥት በኩል የተሄደበት መንገድ አጭር መሆኑ ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎ ወቅት የተስተዋለው ጉዳይም የመንግሥት አቅመ-ደካማነት ሳይሆን ለፓርኩ ያሳየው ግዴለሽነትና ልግመኛነት ነው፡፡

የኦነግ ትንኮሳዎችና ዘረፋ

 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በ1984 ዓ.ም. ከሀገር እንዲወጣ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ በኤርትራ እንዲሁም በኬንያ ፍርኩታዎች ቁጥቋጦዎች ተቀርቅሮ ይኖር ነበር፡፡ በመንግሥት በተደረገለት ይቅርታ ምክንያት ከነበረበት የስደት ዓለም ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን አስተዳደር እየፈተነ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ በተለይ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ብዙ እሰጥ-አገባ ከማድረጉ ባሻገር በአንዳድ አካበባዎች በተለይም በወለጋ የኀይል እርምጃዎችን ሲወስድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በኋላም በኦሮሞ አባ ገዳዎች አሸማጋይነት አምቦ ላይ በተደረገ ዝግጅት ታረቁ ተባለ፡፡ ተስማምቶ መሥራትን ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን ኦነግ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ተወላጆችንና የክልሉን አዋሳኝ አካባቢዎች የኀይል ትንኮሳ ሲያደርግባቸው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

ለአብነት የሚጠቀሰውም በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልሎች ላይ ያደረጋቸው የኀይል ትንኮሳዎች ናቸው፡፡ በቤንሻንጉል በደረሰው የኦነግ ትንኮሳ ለብዙ ዜጎች መፈናቀልና መገደል ምክንያት መሆኑም አይዘነጋም፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ በምንጃር አካባቢ፣ በመቀጠልም በከሚሴ፣ አጣዬ እና ማጀቴ አካባቢዎች የኀይል ትንኮሳዎችን አድርጓል፡፡ ኦነግ እነዚህን የተጠቀሱትን ትንኮሳዎች ሲፈፅም፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሽፋን ሲያደርግለት እንደነበርም የሚረሳ አይደለም፡፡ ከዚህ ላይ ልናነሳው የምንችለው ጥያቄ እውን ኦነግ ይህን ሁሉ ትንኮሳ በሌሎች በክልሎች ላይ ለማድረግ የሚያስችል አቅም አለው? ከሌለውስ ይህን ሁሉ ትንኮሳ እንዴት ሊፈፅም ቻለ?

ሌላው ኦነግ የፈፀመው ድርጊት በወለጋ አካባቢ ባሉ የንግድ ባንኮች ላይ የፈፀመው ዘረፋ ነው፡፡ ይህ ዘረፋ በግልጽ የተደረገ ሆኖ፣ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ይህ በባንክ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሕዝብ ላይ የተፈፀመ ዘረፋ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ የዐቢይ አስተዳደር እስከዛሬ ድረስ አንዳችም ያለው ነገር የለም፡፡ ምን ዓይነት አስተዳደር ነው ግን?

ኦነግ በኦሮሚያ ክልል አካባቢ በአብዛኛው ኦሮሞ ዘንድ ከየትኛውም ድርጅት የተሻለ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከሕወሓት ጋር ደግሞ በስትራቴጅ ጉዳዮች ላይ በተለይም በአማራው ላይ ከያዙት አቋም አንጻር ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ኦነግ በየትኛውም አካባቢ ቅቡልነት ያለው ድርጅት ሆኖ አይታይም፤ በርግጥ ድርጅቱ በሌሎች አካባቢዎች ተቀባይነት እንዲኖረው ዓላማውም የለውም፤ ድርጅቱም ይህን አይፈልግም፡፡ ታዲያ የኦነግ አቅም ውስን ከሆነ፣ በሰው ኀይል፣ በመረጃም፣ በሎጅስቲክስም፣ ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የበለጠ አቅም ላይ የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ለምን ኦነግን ማረቅ አቃተው? ወደ ሀገር ጎትቶ እንዲገባ ያደረገውን ድርጅት እንዴት መቆጣጠር ያቅተዋል? የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ለኦነግ ሽፋን የሚሰጠው (ለምሳሌ በከሚሴና አጣዬ የኦነግ ትንኮሳ) በርግጥም አስተዳደሩ ደካማ ስለሆነ ሳይሆነ ነገር ግን ከኦነግ ጋር የሚጋሩት የጋራ አጀንዳ በመኖሩ ነው ብለን ለመናገር እንደፍራለን፡፡ ግለሰቦችን የሚቆጣጠር መንግሥት ነገር ግን የሕዝብ ባንክ በጠራራ ፀሐይ የዘረፈውን ኦነግ አንዳች ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ያሳየው ምንም ዓይነት ተነሳሽነት የለም፡፡ ይኸውም የዐቢይ አስተዳደር ቢለግም ነው እንጅ ስለደከመ አይደለም፡፡

እንግዲህ ከላይ ለአብነት ባነሳኋቸው አራት ማሳያዎች መረዳት እንደሚቻለው አሁን በሀገራችን ያለው ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ቀውስ ምክንያቱ የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ደካማ ስለሆነ ሳይሆን ይልቁንም አስተዳደሩ ባሳየው ልግመኛነት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ያውም በብዙ ችግሮች የተተበችን ሀገር ሕዝብ ከሚያስተዳድር መንግሥት የማይጠበቅ ድርጊት ነው፡፡

 

(ጸሐፊውን በኢ-ሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡)

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*