ይቅር ብንለው እንኳ የማንረሳው የሕወሓት የጥላቻ ፖለቲካ! – ጌታቸው ወንዲራድ

በቅርቡ አንደበተ ርትዑ የሕግ ምሁር ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ ‹፩ አፍታ› ከተሰኘ የኢንተርኔት ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ግንቦት 20ን በተመለከተ ድንቅ ቃለ-መጠይቅ አድርጎ ተመለከትኩ፡፡ የሕወሓት መሥራቾችን የግል ስብዕናና ግንቦት 20 እንደ ሥርዓት ያመጣብንን ብሔራዊ ውርደት በምሁራዊ ዕይታው ገላልጦ አሳይቶናል፡፡ ሕወሓትን በተመለከተ ከአመራሮቹ ኅሊናዊ ባሕሪ ጋር በተያያዘ በቀላል ቋንቋ አብራርቶ ለተመልካች አስረድቷል፡፡ ከፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ቀጥሎ ዶ/ር ደረጀ ሕወሓትን እና አፈንጋጭ ኅሊናዊ ባሕሪውን በመግለጽ ረገድ ቀልቤን የገዛው ምሁር ሆኖ አግኝቸዋለው፡፡ የሕግ ምሁር ገለጻ የሚከተለውን ጽሑፍ እንዳሰናዳ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ዶ/ር ደረጀ ዘለቀን ለትጋቱ እና ለምሁራዊ ትህትናው ባርኔጣየን ከፍ አድርጌ ወደ አጀንዳየ ተሻግሬለሁ፡፡

ሕወሓት የተጠነሰሰው በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ከለላ ሥር በመሆኑና መሥራቾቹ የእንቅስቃሴው አካል የነበሩ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ከያ ትውልድ የሚመዘዙ የወል ባሕሪያት መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ በተለይም የድርጅቱ መሥራቾች ችኩልነት፣ ግልብነት፣ ስሜታዊነትና ጀብደኝነት የጋራ መገለጫቸው ከመሆን አልፎ የድርጅታቸውን ባህል በእነዚህ መገለጫዎች ቀርፀውታል፡፡

የዚህ ድርጅታዊ ባህል ድምር ውጤት ከግማሽ ክፍል ዘመን በኋላም ፖለቲካችን በጥላቻ አየር የተበከለ፣ በመጠፋፋት የታጀበ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ለፖለቲካችን አለመዘመንና ኋላቀርነት ከያ ትውልድ ተሸጋጋሪ ፖለቲካዊ ዕዳዎች ጋር በተያያዘ በርካታ ተያያዥ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ የሕወሓት በጥላቻ ላይ የተመሠረተው ድርጅታዊ ዓላማና ግብ (በጥቅሉ ድርጅታዊ አቅጣጫ) የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደኋላ በመጎተት ፍፁም አቻ የለሽ የጥፋት መስመር ሆኖ አገልግሏል፡፡

ችኩልነት፣ ግልብነት፣ ስሜታዊነትና ጀብደኝነት የያ ትውልድ መገለጫዎች ቢሆኑም፣ እነዚህ ባሕሪያት ከመደብ ቅራኔ ትግል ተሻግረው ዘውግ ላይ እንዲያጠነጥኑ በማድረግ ሕወሓትን የሚቀድመውም ሆነ የሚበልጠው የፖለቲካ ኀይል የለም፡፡ ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥነት ፈርጀው የተነሱት አቻዎቹ ሻዕብያና ኦነግ በሕወሓት ልክ ዘውጋዊ የጥላቻ ፖለቲካ አላናፈሱም ቢባል ከእውነታው መራቅ አይሆንም፡፡

ስለ ሕወሓት ዘውጋዊ የጥላቻ ፖለቲካ መሐንዲስነት ለመረዳት የድርጅቱን ማኒፌስቶና የጫካ ቆይታ ጊዜ (በተለይም ኪነ-ጥበብና ፕሮፓጋንዳውን) መመርመር ተገቢ ነው፡፡ የትግራይ ዘውጌ ብሔርተኝነትን መሠረታዊ ባሕሪያትንና የታሪክ ጭብጦች በወፍ በረር መፈተሹ የሕወሓትን ድርጅታዊ ተፈጥሯዊ ባሕሪ ለመረዳት ድልድይ ይሆነናል፡፡

የትግራይ ዘውጌ ብሔርተኝነት መነሻ ጫፎች

የኢትዮጵያን ታሪክ በቅጡ የመረመረ ሁሉ እንደሚረዳው የትግራይ ዘውጌ ብሔርተኝነት የታሪክ መሠረቶችን የተንተራሰ ነው፡፡ የብሔርተኝነቱ ማጠንጠኛም ቀዳሚነትን (Seniority) እና የበላይነት (Superiority) የሚያቀነቅን ነው፡፡ የሳባ ተረክን መነሻው አድርጎ፣የአክሱም ሥልጣኔን በብቸኛ ባለቤትነት ይበይናል፡፡ ብዙዎቹ የትግራይ ብሔርተኛ ልሂቃን ራሳቸውን  ብቸኛ የአክሱም ሥልጣኔ ገንቢና ወራሽ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ብሔርተኝነቱንም በዚህ መንገድ (ቀዳሚነትንና የበላይነትን ማጠንጠኛ በማድረግ) ለመገንባት ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡

ከደቡባዊ ዐረብ እስከ ታችኛው የኩሽ ምድር ድረስ በማኅበረ-ኢኮኖሚ ትስስሮሽ ያጠቃልል የነበረውን የአክሱም ሥልጣኔን በብቸኝነት “የእኛ ነው” ከማለታቸው ባሻገር፣ እንደ ስብሐት ነጋ ያሉ ወፈፌ የብሔርተኝነቱ ጠጋኝ መሐንዲሶች የአክሱም ሥልጣኔን “የአንድ ከተማ ሥልጣኔ  -A city of civilization” አድርገው ያቀርቡታል፡፡

የአክሱም ዘመንን ከግዕዝ ሥልጣኔ ጋር የሚያዛምዱት እንደ ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡ ያሉ የታሪክ ባለሙያዎች ‘The trinity of the Geez civilization’ (የግዕዝ ሥልጣኔ ሦስቱ ሥላሴዎች) በሚል አማራ፣ ትግሬ እና አገው የሥልጣኔው መሠረት እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡

በአንጻሩ የትግራይ ብሔርተኛ ሊሂቃን የአክሱም ሥልጣኔን በብቸኝነት ጠቅልለው  ይወርሱታል፡፡ የአማራና የአገው ዘውጎች በሥልጣኔው ላይ የነበራቸውን አሻራ ጨርሶ ሲክዱ ይስተዋላል፡፡ ይህን የክህደት መስመር መነሻ ባደረገ መልኩ የ1967ቱ የሕወሓት ቀዳሚ ማኒፌስቶ እንዲህ ይላል፤ “ትግራይ በጥንቱ ዘመን የአክሱም መንግሥት በመባል ይጠራ የነበረው ሲሆን፤ ያ ግዛት ከወደቀ በኋላ ግን በተለያዩ መጠሪያዎች ሲታወቅ የኖረ ቢሆንም፤ [በዚህ ሁሉ ዘመን ውስጥ] ራሱን የቻለ ነጻ ግዛት (ኦቶኖመስ) ሆኖ ኖሯል፤” የማኒፌስቶው ማዕከላዊ ጭብጥ ትግራይ የአክሱም ሥልጣኔ ብቸኛ ወራሽና ከሥልጣኔው በኋላ በነበሩ ረዥም ዘመናት ራሷን ችላ የኖረች ሀገር መሆኗን በመግለጽ “የትግራይ ሪፐብሊክ” ሐሳብ ታሪካዊ መሠረት ያለው እንደሆነ ማሳመን ላይ ያተኩራል፡፡

ማኒፌስቶው ከመገንጠል በመለስ ያሉ የፖለቲካ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ ታምኖ ከተሻሻለ በኋላም ከአክሱም ዘመን እስከ ዐፄ ዮሐንስ ፍፃሜ መንግሥት ድረስ ትግራይ ነጻ ሀገር ሆና እንደቆየችና በምኒልክ እንደተወረረች ድርጅታዊ ብቻ ሳይሆን ዘውጋዊ በሚመስል ሁኔታ (የልሂቁ ክፍል) አቋም ሆኖ ኑሯል፡፡

የዚህ ዘመን የትግራይ ብሔርተኝነት ወራሾች የሆኑ ወጣቶች ደግሞ ብሔርተኝነቱን ከሳባ ተረክ ጋር ለማስተሳሰር በየማኅበራዊ ድረ-ገጹ (ፓልቶክ፣ ዌብሳይት፣ ፌስቡክ) ሲጥሩ ይታያል፡፡ “እዚኦም ባል መንዩም? (እነዚህ እነማን ይባላሉ?)” ብለው የሚንቋቸውን ኤርትራዊያንን ለመሳብ “እኛ ሁለታችንም አግኣዚያን ነን፤” በሚል ብሔርተኝነቱን ከሳባ (ማክዳ፣ አዜብ) ትርክት ጋር ለመስፋት ይታትራሉ፡፡ “ምኒልክ የትግራይን ማኅበራዊ መሠረት ለማጥበብ ሁለት ወንድማማቾችን ሆን ብሎ ለያየ፤” በሚል ፖለቲካዊ እርግማን የተጠመዱት የብሔርተኝነቱ ወራሾች፣ ኤርትራዊያንና ትግራዊያን አግኣዚያን (ነጻ ሕዝብ) ነን ማለት ከጀምሩ ከራርመዋል፡፡

በሕወሓት ዘላቂ የበላይነት እና በትግራዋያን ዕጣ ፈንታ ዙሪያ ስጋት የገባቸው የትግራይ አክራሪ ብሔርተኞች እና በኢሳያስ አፈወርቂ ቅጥ ያጣ አምባገነናዊ አገዛዝ ተማርረው ስደትን ከመረጡ ኤርትራዊያን ውስጥ በግለሰብ ደረጃ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ተሳትፎ ማድረግ የጀመሩበት ይኸው እንቅስቃሴ፣ (አግኣዝያን ነጻ ሕዝብ፣ ነጻ ሀገር) “የልጆች ምኞት” ተብሎ ቢታለፍም፤ ስለትግራይ ብሔርተኝነት ስሜት ግን የሚነግረን እውነት አለ፡፡

ብሔርተኝነቱ ቀዳሚነትንና የበላይነትን ላለማጣት ስታሊናዊ ባሕሪውን ተሻግሮ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለውን የሳባን ተረክ እስከመመዘዝ እንደሚደርስ መረዳት ይቻላል፡፡ የብሔርተኝነቱ መነሻ ጫፍም ሃይማኖታዊ ታሪክን መነሻ ያደረገ ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ በሕወሓት በኩል ጽዮናዊ ባሕሪ ፈጽሞ ባይስተዋልም፣ ከፓርቲው ውጭ ባሉ አሠራሮች የትግራይ ብሔርተኝነት ማዋቀሪያ ሃይማኖታዊ ደርዝ አለው፡፡

የሴኩላሪዝም አለመከበር በመላ ሀገሪቱ ያለ ችግር ቢሆንም በትግራይ ክልል የባሰ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የዜግነት መብታቸውን ተነፍገው አክሱም ከተማ ላይ መስጊድ አትገነቡም የተባሉበት ምክንያት ከታሪካዊ  ምንነቱ ይልቅ ከሕወሓት የእብሪት ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የብሔርተኝነቱን መነሻ ጫፎች እያሰበ ለአመጽ የተነሳው ቀዳማይ ወያኔ እንደዘመኑ መንፈስ ሃይማኖታዊ ርዕዮተ አንግቦ ተነስቶ ነበር፡፡ አመጹ በዐፄው የበዛ የቅጣት በትር ቢከሽፍም ይህን ታሪካዊ እዳ እሸከማለሁ የሚል ተከታይ ትውልድ በማርክሳዊ መነጽር በስታሊናው ቅኝት የትግራይ ተማሪዎች ማኅበርን አስታኮ ሕወሓትን አዋለደ፡፡

ሁለተኛው ትውልድ ታሪካዊ እዳ ተሸከምኩ ቢልም፣ የጥላቻ ፖለቲካ መሐንዲሶች ስብስብ መሆኑን ከድርጅቱ ሚነፌስቶ እስከ ስትራቴጂያዊ ሰነዶች ይዘት፣ ከባህል ኪነት ሥራው እስከ ፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎች ድረስ በገሃድ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ ‹ወያኔ› የሚለው የትግሪኛ ቃል እምቢተኝነትን፣ አለመቀበልን፣ የሚያቅፍ የትርጉም ይዘት አለው፡፡

የቀዳማይ ወያኔ ተከታይ ትውልድ ራሱን እንደ ታሪካዊ እዳ ተሸካሚ አድርጎ ሲያቀርብም ‹ወያኔ› የምትለዋን ቃል በድርጅት ስያሜው ውስጥ ለትርጉም አስማምቶ እንዲገባ አደረጓል፡፡ ቀዳማይ ወያኔ መነሻውን ወጅራት ላይ ያድርግ እንጅ እንቅስቃሴው እንደርታን ፣ ራያን፣ ተንተቤንና ክለተ አውላዕሎን በጊዜ ሂደት አሳትፏል፡፡

‹ወያኔ› የሚለው ቃል ከደርጅቱ ስያሜ ጋር ሲተሳሰስርም ታሪካዊ መሠረት እንዲኖረው ተፈልጎ ይመስላል፡፡ ዛሬ ላይ ድርጅቱን በግላጭ የሚቃወሙ ኀይሎች ሕወሓት ብሎ ከመጥራት ‹ወያኔ› የሚለውን ቃል እንደ ስድብ ጭምር የሚጠቀሙበት በርካቶች ናቸው፡፡ እውነታው ግን ‹ወያኔ› የሚለው ስያሜ ለነዚህ ሰዎች ስድብ ከመሆን በተቃራኒው ሞገስ የሆነ መጠሪያ ነው፡፡

አሁን ላለው የህወሓት ስብስብ ‹አገዛዝ› የሚለው ስያሜ ራሱ ይበዛበታል፡፡ ይልቁንስ ‹ቋሚ ሽፍታ› (stationary bandit) የሚለው ስያሜ ይመጥነዋል፡፡ የሆነው ሆኖ የትግራይን ታሪካዊ መሠረቶች መነሻ አደረገን የሚሉት የሕወሓት መሥራቾች ላመኑበት የጥላቻ ፖለቲካ መስመር ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡ ዛሬ የሚስተዋለው ዘውጋዊ ቅራኔ ዘመን ያበቀለው አረም ሳይሆን ሕወሓት ከበረሃ ጀምሮ ኮትኩቶ ያሳደገው የጥላቻ ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡

በዘውጐች መካከል  የተዘራው የእርስ በርስ ጥላቻ የሚረግብበት ዕድል መንምኗል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከመሃል ሀገሩ ኢትዮጵያዊ ጋር ለረዥም ዓመታት የነበረውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነትን ክዶ የተነሳው የሕወሓት የጥላቻ ፖለቲካ መስመር የኢትዮያን መጻኢ ዕድል አጨልሞታል፡፡

መንግሥታዊ ኀላፊነት ካለባቸው የፖለቲካ መሪዎች የማይጠበቅ የጥላቻ ንግግር በየዘመኑ ስንሰማው የኖርነው ጉዳይ ነው፡፡ የሕወሓት ሰዎች ባልተገራ አንደበታቸው የተናገሯቸው የጥላቻ ንግግሮች ይዘት በአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በርግጥ የጥላቻው ንግግር ዒላማውን አስፍቶ ኦሮሞን ጨምሯል፡፡ በስመ ኦነግ ካለቀው የኦሮሞ ወጣት ቁጥር በላይ ‹ጠባቦች› የሚለው የህወሓት የፍረጃ ቃል ብዙሃኑን የኦሮሞ ልጆች ያስቆጣ ነገር ነው፡፡

  • “አማራ እንዳያንሰራራ አድርገን ወደታች አርቀን ቀብረነዋል፤” ሳሞራ የኑስ
  • “አማራን እንደሲጋራ ረግጠን ጥለነዋል፤” ስዬ አብርሃ
  • “አማራው እና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የዴሞክራሲ ጠላት ናቸው፤” ስበሐት ነጋ

ወዘተ የሚሉ የጥላቻና የንቀት ንግግሮች መነሻ ምንጫቸው የሕወሓት ድርጅታዊ ቁመና ከተዋቀረበት የጥላቻ ፖለቲካ መስመር የተቀዱ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ውስጥ ያሉትም ሆነ ከድርጅቱ መስመር የወጡ አንዳንድ የቀድሞ ታጋዮች ዛሬም ከጥላቻ ፖለቲካ መስመራቸው አልወጡም፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ የሀገሪቱን ፓርላማ የስድብ መድረክ፣የጥላቻ ፖለቲካ ሸቀጥ ማራገፊያ ያደረገበት ሁነት በአጋጣሚ ወይም በአፍ-ወለምታ አይደለም፡፡ ከበረሃ ጀምሮ ይታመንለት የነበረው የጥላቻ ፖለቲካን መስመር ጠብቆ መጓዝ ግዴታው ስለነበር ነው፡፡ ሕወሓት ጠላት አልባ  ሆኖ መኖር የማይችል ድርጅት መሆኑን ያጤኗል፡፡

ከድርጅት አመለካከት ተሻግሮ እንደአገር የተገነባው የጥላቻ ፖለቲካ መርዙን እየረጨ ከዳር እስከ ዳር ተዳርሷል፡፡ የዛሬ ፖለቲካቻን የኢትዮጵያን ነገ አቅጣጫ የሚወስን ቢሆንም ቅያሱ በጥላቻ መስመር የተቃኘ በመሆኑ አገሪቱ ወደ ገደል እየተገፋች ትገኛለች፡፡ ሀገሪቱ ለገባችበት ቅርቃር በቀዳሚነት የሕወሓት የጥላቻ ፖለቲካ መስመር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡

በሃያ ሰባት ዓመታት የአገዛዝ ተሞክሮ ውስጥ ከሲቪል አመራር ጋር መላመድ ሳይችሉ ቀርተው ባሳፋሪ ሽንፈት ወደ መቀሌ ያፈገፈጉት የሕወሓት ሰዎች ፖለቲካውን የመጠፋፋት መድረክ አድርገውታል፡፡ ቀዳሚነትንና የበላይነትን የሚያጠነጥነውን የትግራይ ብሔርተኝነት በጥላቻ ፖለቲካ መስመር ገርተው የተነሱት የሕወሓት ልሂቃን በዋናነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሦስት አሉታዊ (ተያያዥ) ነገሮችን አጉልተው አውጥተዋል፡፡

1ኛ. ከፖለቲካ ተፎካካሪነት ይልቅ የፖለቲካ ጠላትነትን መፍጠር፣

2ኛ. የፖለቲካ ጠላትን ማጥፋት (መደምሰስ)፣

3ኛ. የሥልጣን/የበላይነት አምልኮ (ሥልጣን ወይም ሞት)፡፡

እነዚህ ችግሮች ከያ-ትውልድ የተሻገሩ ሀገራዊ የፖለቲካ እዳዎች ቢሆኑም ሕወሓት ‹ሕግ› ሴራና ኀይልን አንድም ሦስትም አድርጎ እያቀላቀለ የሀገሪቱን ፖለቲካ በዘውጋዊ ጥላቻ በክሎታል፡፡ በተቃውሞው ጎራ ያሉት የፖለቲካ ኀይሎች ከሕወሓት በመለስ በራሳቸው ችግር የተተበተቡ ቢሆንም፣ በሕዝብ ዘንድ ተስፋ የተጣለባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጎልተው እንዳይወጡ፣ ከቶውንም እንዲከስሙ በማድረግ ረገድ የሕወሓት ድርሻ ከፍ ብሎ ሲታይ ነበር፡፡

ፖለቲካው ከተፎካካሪነት ይልቅ ጠላትነት ያመዘነበት አብይ ምክንያት ከሕወሓት የጥላቻ ፖለቲካ መስመር ጋር በቀጥታ ይዛመዳል፡፡ የድርጅቱ የጥላቻ ፖለቲካ የታሪክ ቅራኔን የተንተራሰ ነው፡፡ የታሪክ ቅራኔው ደግሞ ቀዳሚነትንና የበላይነትን ከሚያጠነጥነው የትግራይ ዘውጌ ብሔርተኝነት ጋር ይተሳሰራል፡፡ የቀድሞውን የታሪክ ቅራኔ ከመደባዊነት በተሻገር ዘውጋዊነትን ያላበሱት የሕወሓት ሰዎች ፖለቲካውን በቅራኔ ሞልተውታል፡፡

ፖለቲካው ቅራኔ ተኮር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ጠላት እንጅ ተፎካካሪ እንዳይኖር አደርጎታል፡፡ ቅራኔ ላይ የተሞረከዘው የፖለቲካ አስተላለፍ የፖለቲካ አቻ አይቀበልም፡፡ የሕወሓት የጥላቻ ፖለቲካ መስመር የሐሳብ ብዝሃነትን በአንድ ሜዳ (ሰላማዊ) ትግል ላይ ማስተናገድ አይችልም፡፡ በዚህ የተነሳ የፖለቲካ  ጠላትን ወደ ማጥፋት (መደምስስ) ይሸጋገራል፡፡ ሲያመች ‹ሕግ›፣ ካልተመቸ ሴራን፣ ካልተሳካም ኀይልን እንደ አማራጭ በመውሰድ የፖለቲካ ጠላትን ማጥፋት የሕወሓት ድርጅታዊ መስመር ነው፡፡ ማረፊያውም የሥልጣን (የበላይነት) አምልኮ ነው፡፡

መስመሩን ‹ሥልጣን ወይም ሞት› ብለን ብንበይነው ከእውነታው መራቅ አይሆንም፡፡ የድርጅቱ የአቋም አዕማድም የተቃኘው ከዚህ መስመር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ያሳለፍናቸውን 27 ዓመታት መለስ ብለን ብንቃኝ የድርጅቱን መስመር በግልፅ መለየት እንችላለን፡፡ የሕወሓት የጥላቻ ፖለቲካ መስመር የተቃውሞ ፖለቲካ ኀይሎችን ድርጅታዊ ህልውና ከመደምሰስ አልፎ በአካል እስከ ማጥፋት ደርሷል፡፡

የጉዳዩ አሳሳቢነት ፖለቲካችን በዘውጋዊ ቅርጽ የተቀነበበ መሆኑና ዘውጋዊ ቅራኔው ወደለየለት ግጭት እንደሚመራ ምልክቶቹ መታየታቸው ነው፡፡ የሕወሓት ልሂቃን የገነቡት የጥላቻ ግንብና የያዙት የማን አህሎን ስሜት ከደርግም የከፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ሁሉ አውዳሚ የፖለቲካ መስመር ውስጥ የትግራይ ተወላጆች የሕወሓትን ጥፋት ‹በቃ!› በማለት ራሳቸውን የችግሩ መፍትሔ አካል ለማድረግ አለመሞከራቸው ሁኔታዎች ይበልጥ እንዲወሳሰቡ አድርጓል፡፡

በከባድ የሰብአዊ መብት ጥፋት እና በስርቆት ወንጀል የተጠረጠሩትን እነ ጌታቸው አሰፋን አሳልፌ አልሰጥም ያለው ሕወሓት፣ ከሕዝቡ ያገኘው ፖለቲካዊ ድጋፍ ድርጅቱን በጥፋት መስመሩ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያን ህልውና አየፈተነ ያለው ሀገራዊ ችግር ደደቢት በረሃ ላይ የተዘራው፣ በግንቦት 20 ማግስት መዋቅራዊ ድጋፍ ያገኘው የዘውጋዊ ጥላቻ ፖለቲካ መርዛማ ፍሬ ውጤት ነው፡፡

እኔ ካልገዛሁ ሀገሪቱ ትፍረስ የሚለው ሕወሓት፣ የዘንድሮውን ግንቦት 20 በጥልቅ የተሸናፊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ አክሱም ላይ ከፍተኛ አመራሮቹ የናቋትን ቤተ ክርስትያን ካባ ደርበው አክብረውታል፡፡

ከማዕከላዊ መንግሥቱ ተነጥሎ ብቻውን አንደ ደሴት ተከልሎ ያለው ሕወሓት የዘንድሮውን ግንቦት 20 ከእስካሁኑ በተለየ መልኩ በአክሱም ከተማ ከጳጳሳት፣ ቀሳውስት እና ዲያቆናት ጋር በመሆን ማክበሩን የታዘቡ አስተያየት ሰጪዎች የበዓል አከባበሩ ሃይማኖታዊ ሴራ አለበት ብለዋል፡፡  የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል እና የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ዓለም ገብረ ዋሕድ እንዲሁም አንጋፋ የድርጅቱ አመራሮች በተገኙበት በአክሱም ከተማ የተከበረው ግንቦት 20 ለብዙዎቻችን ማነጋገሩን እንደቀጠለ ነው፡፡

ሕወሓት እንደ ድርጅት ‹‹ጠላት››  ሲል የፈረጃት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን አሁን በቸገረው ጊዜ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደረጋት መሞከሩ የድርጅቱን ሃፍረተ ቢስነት ያሳያል፡፡ ከበዓሉ አከባበር ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ሙሉ ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን አውግዞ መግለጫ አለማውጣቱ በግሌ አሳስቦኛል፡፡ መቼም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ፈርዶባታል፡፡ ድርጅቱ የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖናና ትውፊት እያፈረሰ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል።

በበኩሌ የቤተ ክርስቲያኗን ውስጣዊ አንድነት ለመከፋፈል ያለመ ፖለቲካዊ ሴራ እንደሆነ  ይሰማኛል፡፡ በዕለቱ ዶ/ር ደብረ ጽዮን እንደ ንጉሠ-ነገሥት ተክሊል ደፍቶ፣ ካባ ደርቦ፣ ድባብ ተይዞለት ሲታይ፣ በአንጻሩ ጳጳሱ ልብሰ ተክህኗቸውን ብቻ ለብሰው ጸሐይ እየመታቸው መታየቱ፣ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኗ ሰዎችም ከሕወሓት ፖለቲከኞች ዝቅ ብለው ጸሐይ ላይ ተሰጥተው መታየታቸው  ብዙዎችን ያሳዘነ ድርጊት ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጋር ለሀገር መረጋጋት እና የሰላም ግንባት ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው እንዲሁም የሙስሊሙን ማኅበረሰብ የዘመናት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ጠረት እያደጉ በመሆናቸው በርካታ ሙስሊሞች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ደስተኞች ሆነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ያገኙት ድጋፍ እንቅልፍ የነሳው ሕወሓት፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ እስላማዊ መንግሥት ሊመሠርቱ የሚፈልጉ ኀይሎች ጉልበት አግኝተዋል፤” የሚል ፕሮፖጋንዳ ውስጥ ለውስጥ ሲያስወራ ሰንብቷል፡፡ የሕወሓት አዲሱ ሃይማኖታዊ ሴራም “ትግራይን እንደ ክርስቲያን ደሴት” አድርጎ  በመሳል፣ ሕወሓትን እየጠላ የመጣውን የትግራይ ሕዝብ “ሃይማኖትህን አድን!” በሚል ሰበብ የድጋፍ መሠረቱን ለማስጠበቅ በማለም፤ ግንቦት ሃያን ከካህናት ጋር  ለማክበር የተገደደ መስሏል፡፡ አንባቢ ሆይ እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ላነሳ እወዳለሁ! ስብሓት ነጋ ሲረግማት ከኖረችው ቤተክርስቲያን ጋር ግንቦት 20ን ማክበሩ የንሰሐ ጊዜ ነው ወይስ ሌላ የሃይማኖት ሴራ ?…

ዶ/ር ደብረ ጽዮን በአክሱም ከተማ በተከበረው ግንቦት 20 ሃይማኖትን የተመለከተ ንግግር ባያደርግም፣ በምልክት ደረጃ ያሳየው አለባበስ እና በመድረኩ ላይ የተገኙ እንግዶች የአንድ ሃይማኖት መሪዎች ብቻ ሆነው መታየታቸው የሕወሓት ከፋፋይ ባሕሪን አጉልቶ አሳይቷል፡፡ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት “መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም፤” ቢልም ሕወሓት ከቀደመ የሴራ ፖለቲካ አመሉ ያልተላቀቀ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያኗ እና ካህናቱ ላይ መቆመሩን እንደቀጠለ የዘንድሮ ግንቦት 20 በዓል አከባበር ማሳያ ነው፡፡

የዕብሪት ፖለቲካውም ወደተራ አሸባሪነት አውርዶታል፡፡ በሕግም ሆነ በታሪክ ከተጠያቂነት የማያመልጠው ሕወሓት፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እጅግ የተጠላው እኩይ ድርጅት ሆኗል፡፡ ሕወሓት ግንቦት 20ን በድል አድራጊነት ስሜት ለማክበር የሚያስችል የሞራል ልዕልና የለውም፡፡ ይልቁንስ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እንደ ሀገር ላጠፋው ጥፋት እና ለዘረፈው የሀገር ሀብት በዚህ ቀን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ቢጠይቅ ይሻለው ነበር፡፡ ለይቅርታ ጊዜው እየረፈደ ነው፡፡ ትውልድና ታሪክ ግን የራሱ ፍርድ አለው፡፡ ቅን ሆነን ይቅር ብንለው እንኳ እንደአገር የፈፀመውን ክፋቱን መቼም ቢሆን አንረሳውም፡፡

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*