LTV እና አንዳንድ ፖለቲከኞች – ጌታቸው ሽፈራው

LTV የአንዱዓለም አራጌን ቃለ መጠይቅ እንዳይተላለፍ አግዷል ተብሎ እየተወራ ነው። ለእገዳው ምክንያት ነው ተብሎ እየተወራ ያለው ደግሞ የጠ/ሚ ዐቢይ ሀሳብን የሚደግፍን ሰው ማቅረብ እንደማይፈልጉ ነው። ይህ ምክንያት ውሃ የሚቋጥር አይመስለኝም።

ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ የዶክተር አብይ አድናቂ ስለሆነ አይደለም ቃለመጠይቁ ላይ ሌላ ቪዲዮ የተደረተበት። በቅርቡ LTV ኢንጅነር ይልቃልን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። 15 ጊዜ፣ ነገ፣ ከነገ ወዲያ እያሉ ከደወሉለት በኋላ በመጨረሻው ቀን ጋዜጠኛዋ ስልኳን ዘግታ ጠፍታለች።

አቶ አንዱዓለም አራጌም ለጠ/ሚ ዐቢይ የሚያጨበጭብ ሰው አይመስለኝም። የሚተቸውን የሚተች፣ የሚደገፈውን የሚደግፍ ይመስለኛል። በዐቢይ ጉዳይ።

ጉዳዩ ሌላ ይመስለኛል። LTV አሁንም “ነፍጠኛ” ቅብጥጥስ ፍረጃ ውስጥ ያልወጣ ጣቢያ ስለሆነ እንጅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳይ አይደለም። ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፣ ኢንጅነር ይልቃልና አቶ አንዱዓለም አራጌ የሚለያዩባቸው አቋሞች ይኖራሉ። ሆኖም ለ LTV ሁሉም ነፍጠኞች ተብለው የሚፈረጁ ናቸው። ምንም አቋም ልዩነት ቢኖራቸው በአንድ ቋት ያስቀምጧቸዋል።

ከአንዱዓለም በላይ አቶ ሌንጮ ለታ የጠ/ሚ ዐቢይ ደጋፊ ነው። ቴሌቪዥን ጣቢያው ቤታቸው ከሆነው የኦሮሞ ፖለቲከኞች በላይ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔና ኢንጅነር ይልቃል ጠ/ሚ ዐቢይን ይተቻሉ።

የLTV ማስታወቂያዎች የኦፌኮና የኦነግ ፖለቲከኞች ናቸው። ጣቢያው እገዳ የሚያደርገው በዐቢይ ደጋፊና ተቃዋሚነት ሳይሆን ከዛ ባለፈ “የእኛ” እና “የእነሱ” በሚል የኦነግ ፍረጃ ነው!

ቴሌቪዥን ጣቢያው እገዳ የሚያደርገው በኦነጋዊ ትርክቱ ሆኖ እያለ ከጠ/ሚ ዐቢይ ጋር መያያዙ ትክክል አይደለም። እነ ሌንጮ የእነ ኢንጅነር ይልቃልን ያህል ነጥብ በነጥብ ዐቢይን አይተቹም፣ እንዲያው መቃወም ብቻ ካልሆነ በስተቀር። እነ ጃዋር የእነ ዶክተር ደሳለኝና አንዱዓለምን ያህል አይተቹም። ለኦሮሞ ሕዝብ ከፍ ያለ ጥቅም ካልጠየቁ በስተቀር።

በጣቢያው የተገፉትን ሶስቱ ፖለቲከኞች ከኦነግና ከጠ/ሚ ዐቢይ በተለየ ሕገ መንግስቱን፣ ፌደራል ስርዓቱን የሚተቹ ናቸው። በአዲስ አበባ ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም የያዙ ናቸው። በታሪክ ላይ ተመሳሳይ አረዳድ ያላቸው ናቸው። በኢትዮጵያ ጉዳይ ግባቸው የተለየ አይደለም። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም ጣቢያው በተደጋጋሚ ከሚያቀርባቸው ፖለቲከኞች ጋር ይቀራረባል፣ በዚህ አቋም ከሶስቱም ፖለቲከኞች አመለካከት ይርቃል!

ዋናው የዐቢይ ጉዳይ አይደለም! ሌላ ዐቢይ ጉዳይ አለው። የትርክት ልዩነት ነው።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*